1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሊ ሙዚቀኞችና አስቸጋሪዉ ግዜ

ሐሙስ፣ ሰኔ 27 2005

በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ በምዕራባዊትዋ አፍሪቃ አገር በማሊ ሚታየዉን ዉጥረት ለማርገብ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ኒኑስማ «MINUSMA»የተሰኘዉ የተመድ አረጋጊ ቡድን 12,600 ወታደሮቹን እንዳሰለፈ ተነግሮአል።

https://p.dw.com/p/19210
Der Musiker Bassekou Kouyaté aus Mali mit Sängerin Amy Sacko auf der offenen Bühne des Festivals DW/Aude Gensbittel (30.05-2.06.13) in Würzburg
ምስል DW/A. Gensbittel

በማሊ የሚታየዉ ቀዉስ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን በኤኮኖሚ እና በማህበረሰብም ላይ ከባድ ጫናን አሳድሮአል። በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ላይ የሚገኙ የማሊ ተወላጆች በተለይ ሙዚቀኞች ትልቅ ችግር ላይ ወድቀዋል። የፈረንሳይ ጦር በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2013 ዓ,ም ጥር 11 በሰሚናዊ ማሊ እስላማዊ አማጽያንን መዉጋት እንደጀመረ፤ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ ደንብን መጣሉ ይታወሳል። የዚህ የአስቸኳይ ግዜ ደንብ እገዳዎች፤ የተቃዉሞ ሰልፍን፤ በብዛት በአንድ ላይ መሰብሰብን እንዲሁም ማንኛዉንም አይነት የሙዚቃ ድግስ ማሳየትን ይከለክላል። በዓለም አቀፍ የሙዚቃ መድረክ በጣዕመ ዜማዋ የምትታወቀዉ ማሊ፤ በአሁኑ ወቅት አብዛኞች ከያኒዎችዋ የአገሪቱን ሙዚቃ ዳግም ህያዉ ለማድረግና ህልዉናቸዉን ለማስከበር ትግል ላይ ናቸዉ። በማሊ በቅርቡ እስከ ሰኔ 5 ዳግም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለሶስተኛ ግዜ ተደንግጎአል። ይህን ተከትሎም ሐምሌ 28 በማሊ ፕሪዝደንታዊ ምርጫ እንደሚጀመር ይፋ ሆንዋል። የዶቼ ቬለዋ አዉደ ጄንስትል በማሊ ሙዚቀኞችን አግኝታ ፤ በአገሪትዋ የኪነ-ጥበቡ ዘርፍ የገጠመዉን ችግር በማስመልከት ዘገባ አጠናክራለች። በዛሪዉ ዝግጅታችን የማሊን ሙዚቃ ይዘን ፤ በማሊ በተቀሰቀሰዉ ዉጥረት ምክንያት በከያኒዎች ላይ የደረሰዉን ችግር እንቃኛለን መልካም ቆይታ።

Balafon-Spieler Aly Keita aus Mali
ምስል Daniela Incoronato

በምዕራብ አፍሪቃ በሚታወቀዉ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያ « ንጎኒ» እና ከዘመናዊ የሙዚቃ መሳርያ ጋር የተቀናበረን ሙዚቃ ነበር ያደመጥነዉ። ንጎኒ ሶስት ወይም አራት ክር የተወጠረ ክራር መሰል የሙዚቃ መሳርያ ሲሆን በተለይ በምዕራብ አፍሪቃ አገራት በብዛት ይዘወተራል። እዚህ በጀርመን በቮልዝ ቡርግ ከተማ ንጎኒ ባህላዊ የሙዚቃን ከዘመናዊ ሙዚቃ ጋር በማጣመር ድንቅ የሙዚቃ ድግስ ካቀረቡት መካከል የማሊዉ ተወላጅ እና የንጎኒ የሙዚቃ መሳርያ ተጫዋች ባዜሁ ኮየቴ ይገኝበታል። በአሁኑ ወቅት በኮየቴ ትዉልድ ሀገር በማሊ ምንም አይነት ሙዚቃን መጫወትም ሆነ ማቀናበር አይቻልም። ቀደም ሲል ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በማሊ መዲና በባማኮ በየቀኑ በሙዚቃ መሳርያ የተቀናበረ የመድረክ ላይ የሙዚቃ ድግስን በየቦታዉ ማየት የተለመደ ነበር። አሁን ግን በዝያ ፈንታ ጸጥታ ነዉ የነገሰዉ። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ መንግስት ከጥር ወር መጀመርያ ጀምሮ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን በመደነገጉ እና የመድረክ ላይ ሙዚቃን ሁሉ በማገዱ ነዉ። ይህ ደንብ ለአገሪቷ የኪነ-ጥበብ እድገት ከባድ አደጋ ነዉ ያለዉ፤የማሊዉ ታዋቂ ሙዚቀኛ ሃቢብ ኮቴ በሚያቀርበዉ የመድረክ ሙዚቃ ላይ የባዝ ሙዚቃ መሳርያን የሚጫወተዉ አብዱል ዋሂብ ቤርት እንደሚለዉ

«የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንደተደነገገ፤ በአብዛኛዉ ችግር ላይ የወደቁት ሙዚቀኞች ናቸዉ። ምንም አይነት ስራን መስራት አይፈቀድላቸዉም፤ በስቱድዮ የቀረጻ ስራ፤ አልያም የመድረክ የሙዚቃ ቅንብር፤ ምንም ምንም አይፈቀድላቸዉም። በማሊ የምንገኝ ሙዚቀኞች በአሁኑ ሰዓት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮን ነዉ የምንኖረዉ። በፊት ይረዱን የነበሩት ጥሩ ጓዶቻችንም በአሁኑ ሰዓት እራሳቸዉም በችግር ዉስጥ ነዉ የሚገኙት። አጣብቂኝ ዉስጥ ነዉ ያለነዉ። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ነዉ ለዚህ የዳረገን»

Aly Keita
ምስል OhWeh

እንዲያም ሆኖ አብዱል ዋሂብ አንዳንዴ ወደ አዉሮጳ ወጣ እያለ በአንዳንድ መድረኮች ላይ ሙዚቃዉን በማሳየት ትንሽ ገንዘብ በማግኘቱ ደስተኛ እንደሆነ ይገልጻል። ባላፎ የተሰኘን በምዕራብ አፍሪቃ የሚገኝ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያን የሚጫወተዉ ሌላዉ የማሊ ተወላጅ እና እዚህ በጀርመን የበርሊን ከተማ ነዋሪዉ፣ አልያ ኪታ ከማሊ ታዋቂ ሙዘቀኞች ጋር በዓለም ዙርያ በሚገኙ የሙዚቃ መድረኮች እየተዘዋወረ የማሊ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያን ይጫወታል። በቅርቡ የትዉልድ ሀገሩን ገብኝቶ በሀገሩ የኪነ-ጥበብ እድገት ሂደት መገታትን ተመልክቶ፤ የነገሩን አስፈሪነት እንዲህ ነዉ የገለጸዉ።«በሰርግ ላይ በባህላዊ የማህበረሰብ ስብስብ ላይ ሙዚቃን ይጫወቱ የነበሩት ጓደኞቼ ነገር ሁሉ ከባድ ነዉ የሆነባቸዉ። ባህላዊ ሙዚቃን የሚጫወት ከያኒ ሁሉ የሙዚቃ መሳርያዉን ከመኖርያ ቤቱ ዉጭ ሌላ ቦታ ይዞ አይሄድም። ምንም አይነት የመድረክ ላይ የሙዚቃ ድግስ፤ በቡና ቤትም ሆነ በክለቦች ዉስጥ አይደረግም። ሙዚቀኞች ሁሉ የሰነቁትን ተስፋ በማሟጠጣቸዉ በጃቸዉ ላይ ያለዉን ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያ መሸጥ ጀምረዋል» ሙዚቃ ይላል አልያ በመቀጠል። ሙዚቃ ጸጥታን እና ጥበቃን ያዉቃል። ግን ለፀጥታ ጥበቃ ተብሎ ሙዚቃን በጋራ መጫወት መከልከሉን እንዲህ ይቃወማል። «ሙዚቃ ሰዎችን በማግባት ያስተሳስራል። አጥፍቶ ጠፊ ታጣቂዎች የሙዚቃ ድግስን ለማየት የተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ገብተዉ ራሳቸዉን እና ህዝብን ይጨርሳሉ ተብሎ ተፈርቶ ነዉ። ብዙ ሰዎች ግን፤ ለምን ሙዚቃን እና ለሙዚቃ ድግስ መሰብሰብን መከልከሉ አልገባቸዉም። በጣም ያሳዝናል፤ ብዙዎችን አላስደሰተም፤ ይህ የሆነዉ ግን ፤ ለጸጥታ ጥበቃዉ ነዉ»

ንጎኒን የሙዚቃ መሳርያን የሚጫወተዉ ማሊያዊዉ ከያኒ ባሴኩ ኮየቴ፤ ባለፈዉ ዓመት ከሰሜናዊ ማሊ ስለተፈናቀሉት የማሊ ሙዚቀኞች ጉዳይ ያስባል። እስላማዊ አማፅያን ሰሜናዊ ማሊን ረዘም ላሉ ወራቶች በተቆጣጠሩበት ወቅት፤ በርካታ አካባቢዎች ሙዚቃ ማዳመጥም ሆነ ማዜም የተከለከለ ነበር። ሰሜናዊ ማሊን ለቀዉ ባማኮ መዲና የገቡ ሙዚቀኞችም በአሁኑ ሰዓት ሙዚቃን ማዜም ተከልክለዋል። «መንግስት በፀጥታ ምክንያት ሙዚቃ እንዳንጫወት ካገደ፤ በሙዚቃዉ ምትክ በገንዘብ ድርጎማ ሊያደርግልን ይገባል። በማሊ ለሚገኘዉ የፀጥታ ሃይል ብዙ ገንዘብ የሚያፈሰዉ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ፤ በቀጣይ ስራቸዉን መስራት ስላልቻሉት ስለ ማሊ ሙዚቀኞች ሊያስብ ይገባዋል። ሙዚቃ እጅግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ አንድ ትንሽ ድጋፍን ይፈልጋል። እኛም፤ ለዚች ሀገር በተቻለን ሁሉ የምንቆም የማሊ ዜጎች ነን»

Auftritt der Tuareg-Band Tinariwen aus Mali. Foto: DW/Julia Hahn, bei einem Konzert der Band am 21.04.12 in Köln
ምስል DW

ከያኒ ባሴኩ ኮኡቴ ከረጅም ግዜ ጀምሮ በትዉልድ ሀገሩ በማሊ ለሰላም ጥረት በማድረጉ ይታወቃል። የሙዚቃ ስራዎቹ በአብዛኛዉ በማሊ ያሉትን የተለያዩ የጎሳ ቡድኖች አንድ እንዲሆኑ የሚያነሳሳ፤ የሃይማኖት ነጻነትና መቻቻል እንዲሰፍን የሚቀሰቅሱ ናቸዉ። ከያኒ ባሴኩ ኮኡቴ በመንግስት ፋላጎት በብሄራዊዉ የቴሌቭዝን ጣብያ ስራዎቹን በተደጋጋሚ ይዞ ሲቀርብ፤ የማሊ ተወላጆች ፤ በተለይም በሰሜናዊ ማሊ የትዋሪግ ጎሳዎች አንድ እንዲሆኑ ጥሪዉን አስተላልፎአል።

«በማሊ ብዙ ደም ፈስዋል።አሁን እኛ የምንሻዉ የተለመደዉ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ትብብር እና አንድነትን ነዉ። በማሊ 300 በላይ የተለያዩ ጎሳዎች ይገኛሉ፤ ታድያ እነዚህ ጎሳዎች ለየራሳቸዉ ይህችን አገር ቆርሰዉ መዉሰድ ቢፈልጉ፤ ለየአንዳንዱ ቡድን የሚደርሰዉ 100 ካሪ ሜትር ብቻ ነዉ። እናም መብትን በመሳርያ ሳይሆን በመነጋገር ማስከበር ይሻላል» በምዕራብ አፍሪቃዊትዋ አገር በማሊ በቀጠለዉ ዉጥረት ምክንያት፤ የማሊ ሙዚቀኞች የገጠማቸዉን አስቸጋሪዉ ግዜ የፊታችን ሐምሌ ወር መጨረሻ ከሚጀምረዉ ፕሪዘደንታዊ ምርጫ ዘመቻ እና ምርጫ በኋላ የተጣለዉ የአስቸኳይ ግዜ ደንብ ይነሳል የሚል ተስፋን ሰንቀዋል። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ መስምያ ምልክቱን ተጭነዉ ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ