1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሙሳቬኒ በዓለ-ሲመትና ተቃዉሞዉ

ዓርብ፣ ግንቦት 5 2003

የዩጋንዳዉ ፕሬዝዳት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ሐገሪቱን ለተጨማሪ አራት አመት ለመምራት ዛሬ ቃለ-መሐላ ፈፀሙ።

https://p.dw.com/p/RNlM
ምስል AP

የሥልሳ-ስድስት አመቱ አዛዉንትና የቀድሞ አማፂ ቡድን መሪ ከ1978 ጀምሮ ምሥራቅ አፍሪቃዊቱን ሐገር እየመሩ ነዉ።ባለፈዉ የካቲት በተደረገዉ ምርጫ ተቀናቃኞቻቸዉን በከፍተኛ የድምፅ ልዩነት ማሸነፋቸዉ ተነግሮ ነበር።ከምርጫዉ በሕዋላ በተደረገ የተቃዉሞ ሠልፍ ፀጥታ አስከባሪዎች አቁስለዋቸዉ ኬንያ ዉስጥ ሲታከሙ የነበሩት የሙሴ ቬኒ ዋነኛ ተቀናቃኝ ኪዛ ቤሲጄም ዛሬ ወደ ሐገራቸዉ ተመልሰዋል።ቤሲጄ እንደሚሉት የምርጫዉ ዉጤት፥ የዛሬቁ በአለ-ሲመትም የአጭበርባሪዎች ድግስ ነዉ።በበዓለ ሲመቱ ድግስ ላይ የናይጄሪያ፥ የኢትዮጵያ፥ የዚምባቡዌ፥ የሶማሊያና የደቡብ ሱዳንን ጨምሮ የበርካታ የአፍሪቃ ሐገራት መሪዎች ተገኝተዋል።ታዛቢዎች እንደሚሉት ድግሱ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈጅቷል።የኑሮ ዉድነት፥ ሥራ አጥነትና ድሕነት ያማረረዉ የሐገሪቱ ሕዝብ ግን ከትናንት በስቲያ ለተቃዉሞ ሠልፍ አደባባይ ወጥቶ ነበር።