1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሴት ፕሬዝደንት

ሐሙስ፣ ኅዳር 15 1998

ላይቤሪያ ከብዙ ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ተላቃ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሚሆኑትን ሴት ፕሬዝደንት ኤሊን ጆሃንሰን ሲርሊፍን መረጠች። ምንም እንኳን በፕሬዝደንታዊ ምርጫዉ ተፎካካሪያቸዉ የነበረዉ በእግር ኳሱ ዓለም በኮከብነቱ የታወቀዉ ጆርጅ ዌህ ተጭበርብሯል በማለት ዉጤቱ እንዲጣራ አቤቱታ ቢያቀርብም የማጣራቱ ሂደት ተከናዉኖ ሲርሊፍ አሸናፊ መሆናቸዉ ትናንት ይፋ ሆኗል። ድጋፉና ደስታዉም ከአገር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቱንም ሴቶች አዳርሷል።

https://p.dw.com/p/E0jK
ተስፋ የተጣለባቸዉ አዲሷ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ኤሊን ጆሃንሰን ሲርሊፍ
ተስፋ የተጣለባቸዉ አዲሷ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ኤሊን ጆሃንሰን ሲርሊፍምስል AP

የማሸነፋቸዉ ዜና ትናንት በይፋ ሲነገር በሰላም አስከባሪዉ ጦር ተጥሎ የነበረዉን የሰላማዊ ሰልፍ እገዳ ጥሶ ነበር ህዝቡ ደስታዉን ለመግለፅ ወደጎዳና የወጣዉ።
የሞንሮቪያ ኗሪዎች ያንቺ ጊዜ ነዉና እስኪ እድል ስጪን እያሉ በመረጧቸዉ ፕሬዝደንት ላይ የጣሉትን የለዉጥ ተስፋ የሚያንጸባርቁ መፈክሮችን አሰምተዋል።
ላይቤሪያዉያን ብቻ አይደሉም የሲርሊፍን ፕሬዝደንትነት በጉጉት የተቀበሉት አፍሪካዉያን በተለይም ሴቶቹ ማማ ኤሊን የሚሏቸዉን የመጀመሪያ አፍሪካዊት ሴት ፕሬዝደንት ግጭት ባደቀቃት ላይቤሪያ የሚያመጡትን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ለዉጥ ለማየት ቸኩለዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበዉ ከስራ አጡ አንስቶ እስከ መንግስት ባለስልጣናት ደረጃ የሚገኙት አፍሪካዉያን ሴቶች የወንድ የበላይነት በነገሰባት አህጉር በፆታ ረገድ ያለዉን የተዛባ ግንዛቤ ይለዉጣል በሚል በሲርሊፍን መመረጥ ደስታቸዉን እየገለፁ ነዉ።
ሴኔጋላዊቷ የስነህብረተሰብ ምሁር ማሪ አንጌሊኬ ሳቫኔ በአፍሪካ የነበረዉን ባህላዊ ትብታብ የበጣጠሰ ታሪካዊ አጋጣሚ ብለዉታል የሲርሊፍን አሸናፊነት።
ወንዶች ምን መስራት እንደሚችሉ እስከዛሬ አሳይተዋል አሁን ሲርሊፍን የሚያዩ በርካታ ሴቶች ደግሞ እኔስ ማለት ይጀምራሉ ሲሉም በማህበረሰቡ ዉስጥ ሊመጣ የሚችለዉን ያመለካከት ለዉጥ ጠቁመዋል።
እስከዛሬ በአፍሪካ የተለያዩ ሴቶች በመንግስታት ዉስጥ መሳተፍ ችለዋል በርካቶችም ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ደርሰዋል። በብሄራዊ ምርጫ ተወዳድረዉ የአገር መሪነት ስልጣን ላይ የወጡ የመጀሪያዋ ሴት ግን ሲርሊፍ ናቸዉ።
በአህጉሩ ለሚገኙ ለበርካታ ሴቶች ይሄ አጋጣሚ ፈር ቀዳጅ መሆኑን የገለፁት የ67ዓመቷ ሲርሊፍ የዚህ ለዉጥ የመጀመሪያ በር ከፋች በመሆናቸዉ መደሰታቸዉን ገልፀዋል።
በርካታዎቹ የሲርሊፍ አድናቂዎች ወንዶች ሲሆኑ በእነሱም እምነት ከወንድና ሴቶች ይልቅ ወንዶች ብዙ ጊዜ ቃታ መሳብ ስለሚቀናቸዉ አብዛኛዎቹን የአፍሪካ አገራት ወደግጭትና እንስሳዊ እልቂት እንደከተቱ ይናገራሉ።
ይህ ሁሉ ሙገሳና ድጋፍ ያጀባቸዉ ቢሆንም ጆሃንሰን ሲርሊፍ የ14ዓመታት የእርስ በርስ ግጭት 250,000 ዜጎቿን ባሳጣት ላይቤሪያ ሰላም አስፍነዉ የማልማት ሃላፊነት ከፍታቸዉ ተደቅኗል።
ብዙዎች ብረቷ እመቤት ደጋፊዎቻቸዉ ደግሞ ማማ ሲርሊፍ የሚሏቸዉ አዲሷ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ለረዥም ጊዜያት ጎራ ለይተዉ ሲተላለቁ የነበሩትን ወገኖቻቸዉን ለማስማማት በመጣር እንዲሁም በህፃንነታቸዉ መሳሪያ አንግበዉ እንዲዋጉ የተገደዱትን ታዳጊዎች በመርዳት ይታወቃሉ።
የዑጋንዳ የፆታ፤ የስራና የማህበራዊ ልማት ሚኒስትር ዞይ ባኮኮ ባኮሩ ይህ አገጣሚ በላይቤሪያ ታሪክ ወደሰላም የመሻገሪያዉ ደረጃ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አላቸዉ።
ምክንያቱንም ሚኒስትሯ ሲያብራሩ ሴቶች ጦርነትና ግጭትን አንፈልግም በአሁኑ ወቅትም ላይቤሪያን ከእኚህ ሴት የተሻለ ማን ሊመራት እንደሚችል መገመት ያዳግተኛል ብለዋል።
አህጉሪቱ አፍሪካ ስትታይ ሴቶችን በመንግስት የአስተዳደር ስልጣን በስፋት በማሳተፍ ከአዳጊ አገራት በተሻለ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በቆዳ ስፋቷ ትንሽ በሆነችዉ ሩዋንዳ በአሁኑ ጊዜ በፓርላማ ዉስጥ የሚያገለግሉት ሴቶች 49በመቶ ደርሰዋል።
በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛዋ ሴት ፖለቲከኛ ምክትል ፕሬዝደንቷ ፉምዚል ምላምቦ ናጉካ ሲሆኑ በተመሳሳይ ሁኔታም በጎረቤቲቱ ዚምባቡዌ ምክትል ፕሬዝደንቷ ጆይስ ሙጁሩ ናቸዉ።
ሞዛምቢክና ሳዖ ቶሜም ጠቅላይ ሚንስትሮቻቸዉ በጠንካራ አስተዳደራቸዉ የሚደነቁ ሴቶች ሲሆኑ በአፍሪካ በነዳጅ ሃብቷ የምትታወቀዉ ናይጀሪያም የገንዘብ ሚኒስትሯ ናጎዚ ዖኮንጆ ኢዌይላ ናቸዉ።
በዘመናዊቷ አፍሪካ ከዚህ በፊት በምርጫ ተወዳድረዉ ሳይሆን ለፕሬዝደንትነት ተሹመዉ የነበሩት እዚያዉ ላይቤሪያ ዉስጥ በ1988ዓ.ም ላይ ሩዝ ፔሪ ሲሆኑ ኤልዛቤት ዶሚቲንም በፈረንጆቹ 1975ዓ.ም. በመካለኛዉ አፍሪካ ሪፐብሊክ ስልጣን ላይ የወጡ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።
የፖለቲካ ፓርቲ በመምራት የመጀመሪያዋ የሆኑት ዛሚቢያዉቷ የፖለቲካ ሰዉ ኤዲዝ ናዋክዊ ጉዳዩ ስለሴቶች ሳይሆን የተሻለ የአስተዳደር ስርዓት መዘርጋት መሆኑን ነዉ የሚናገሩት። የተመረጡት ሴቶች ይህን ማሳየት ከቻሉ ደግሞ ምርጫዉ የተሳካ መሆኑን ያረጋግጣሉ።
ኬንያዊቷ የኖቤል ተሸላሚ ዋንጋሪ ማታይ ሴቶች ለሰላም የመንቀሳቀስ እድል እንዳለዉ በመግለፅ በላይቤሪያ የተገኘዉ ዕድል የአፍሪካ ህዝቦች ሲመኙት የነበረ ነዉ ብለዋል።
በላይቤሪያ ዛሬም የሴቶች ህይወት ለግዳጅ ጋብቻና የወሲብ ጥቃት የተጋለጠ ነዉ። ለዚህም ነዉ በርካቶች በተስፋ ከጆንሰን ሲርሊፍ ብዙነገር የሚጠብቁት።