1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመዉሊድ ባህላዊ አከባበር

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 6 2009

በየዓመቱ በሚከበረዉ በነብዩ መሐመድ የልደት ቀን  የኃይማኖት ተቋማት ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በአስተምሮቱ ሰላምን መረዳዳትን፣ ፍቅርና መከባበርን እንደሚያነሳ የነገሩንን እንግዶች ይዘን የመዉሊድን ባህላዊን የአከባበር ሁኔታ እንቃኛለን።

https://p.dw.com/p/2ULw1
Äthiopien Geburt des Propheten Muhammad (Mewlid)
ምስል DW/G. Tedla

የመዉሊድ በዓል

 

ለ1ሺህ 491ኛ ጊዜ ተከብሮ የዋለዉ የመውሊድ በዓል በብሔራዊ ደረጃ የተከበረዉ ጅማ አባ ጅፋር ቤተ-መንግስት አጠገብ ሲሆን በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናት እንደተገኙ ተመልክቶአል።

Äthiopien Geburt des Propheten Muhammad (Mewlid)
ምስል DW/G. Tedla

የነብዩ መሃመድ 1ሺህ 491ኛዉ የልደት በዓል ማለትም «መውሊድ»  ባለፈዉ ሳምንት እሁድ ታኅሳስ 2 ቀን ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ላይ በታላቁ አንዋር መስጂድ የተከበረ ሲሆን በብሔራዊ ደረጃ በጅማ የአባጅፋር ቤተ-መንግስትን በመጎብኘት ብሎም የሃይማኖትቱን ሥርዓቶች በማሰብና በመፈፀም መከናወኑ ተነግሮአል። በዚሁ በጅማ በአባጅፋር ቤተ-መንግስት አጠገብ በተከናወነዉ የአከባበር ሥርዓት ላይ የጅማዉ አባጅፋር ጥንታዊ ቤተ-መንግሥትና ራሱ የመዉሊድ አከባበር ሥርዓት በ«ዩኔስኮ» ማለትም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት መዝገብ እንዲሰፍር  ሃሳብ ቀርቦኦአል። በርግጥ የነብዩ መሃመድ ልደት ማለት «የመዉሊድ» በዓል ማለት ምንድን ነዉ አከባበሩስ? አዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑትና የዝግጅት ክፍላችንን የሁልጊዜ ተባባሪ ዑዝታዝ ቶፊክ ባህሩ የመዉሊድ በዓል በይፋዊ መልኩ በዓመት ይከበራል እንጂ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ነብዩ መሐመድን በሁሉ አጋጣሚ ያስባል ሲሉ ገልፀዋል።

Äthiopien Geburt des Propheten Muhammad (Mewlid)
ምስል DW/G. Tedla

በዓለም ዙርያ የመዉሊድ በአል አከባበር ደማቅ ቢሆንም በሀገራችን በኢትዮጵያ ግን ለየት ያለ ነዉ በ አከባበሩ ነሼዳ በማድረግ በመንዙማ ዚክራ፤ ማለት ለአምላክ ምስጋና በማቅረብ እንደሆን ዑዝታዝ ቶፊክ ገልፀዉልናል። በዓሉ በተለይ ምሽት ላይ የሚደረገዉ በመንዙማ የሚካሄደዉ  የምስጋና ማቅረብ ሥነ-ስርዓት እጅግ ደማቅ እና ተወዳጅ መሆኑንና የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሄርያ በድሩ ወላጅ አባታቸዉ በየዓመቱ በሠፊዉ ድግስ በመደገስ ቀኑን አስበዉ እንደሚዉሉ በሰፊዉ አብራርተዋል። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ