የመንግስት የደሞዝ ጭማሪ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 29 2006
በመጠናቀቅ ላይ ከሚገኘው የሐምሌ ወር ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኞች ከ33 በመቶ እስከ 46 በመቶ የሚደርስ የደሞዝ ጭማሪ የሚደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን አስታውቋል። የደሞዝ ጭማሪውን አስመልክቶ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሁን 420 ብር የሚከፈለው የመንግስት ደሞዝተኛ 46 በመቶ ጭማሪ ተደርጎለት ወደ 615 ብር የሚያድግ ሲሆን ለከፍተኛ የመንግስት ተከፋዮች ደግሞ 33 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ይህ የደሞዝ ጭማሪ በዓመታዊ በጀቱ ላይ 10.3 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስከትል የገለጹት አቶ ሱፊያን አህመድ "የመክፈል አቅማችንን በማሟጠጥ ይህ የደሞዝ ጭማሪ ተደርጓል" ብለዋል።
የሐምሌ ወርን የሚጨምረውና በሚቀጥለው የነሐሴ ወር ከተጠቃሚው እጅ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የደሞዝ ጭማሪ የመንግሥት ሠራተኛውን ያበረታታል ተብሎ ይታሰባል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር አሰፋ አድማሴ ይሁንና የዋጋ ግሽበትን ሊያመጣ የሚችልበት እድልም እንዳለ ይናገራሉ።
10.3 ቢሊዮን ተጨማሪ ብር ለገበያው ይዞ የሚመጣው የዘንድሮው የደሞዝ ጭማሪ ተጽዕኖው በዋጋ ግሽበት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከቀረጥ፤ ብድርና ከውጪ መንግሥታት የሚገኝን ድጋፍ ታሳቢ ተደርጎ ወጪዎች ይሰላሉ የሚሉት ዶክተር አሰፋ አድማሴ ይህ የደሞዝ ጭማሪ በመንግስት ዓመታዊ ወጪ ላይም ተጽዕኖ እንዳለው ነዉ የሚያስረዱት።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ