1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ዉሳኔ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 25 2010

የመንግሥትን የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ዜና ብዙዎች ገና አልሰሙትም። ያልተጠበቀ ከመሆኑ በተጨማሪ የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ የኤክትሪክ መጥፋት ተደማምረዉ ከመረጃዎች እንዳራቋቸዉ ነዉ የሚናገሩት።  የሰሙትም ለማመን የከበዳቸዉ ይመስላል።

https://p.dw.com/p/2qJ65
Äthiopien Journalisten Martin Schibbye und Johan Persson
ምስል AP

ዜናዉ ለብዙዎች መልካምም የማይታመንም ነዉ የሆነዉ፤

ጥቂት የማይባሉ ከፍተኛ አመራሮቹ የታሠሩበት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ዜና እዉነት መሆኑ የሚረጋገጠዉ ተግባራዊ ሲሆን ነዉ ይላሉ። የሕግ ባለሙያ እና ከታሳሪዎቹ የአንዱ ጠበቃ ደግሞ ዜናዉ አስደሳች መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዉ ድሮዉምንም ቢሆን መታሰር አልነበረባቸዉም ሲሉ አስተያየታቸዉን ለዶቼ ቬለ ሰጥተዋል። 

በሚያስደንቅ ርምጃ የኢትዮጵያ መሪዎች ዛሬ ረቡዕ በፖለቲካ እስረኞች ላይ የቀረቡ ክሶችን የማንሳት እና ስመጥፉውን እስር ቤት ማዕከላዊን የመዝጋት ዉሳኔ አሳለፉ ሲል ይነበባል የአሶስየትድ ፕረስ ዘገባ። አክሎም ዘገባው ይህ ርምጃም በሀገሪቱ ያለዉን የፖለቲካ ምህዳር የማስፋት ጥረት አንዱ አካል መሆኑንም ይገልጻል። ይህን ዜና ሰምተው እንደሆነ የጠየኳቸዉ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ ዜናዉን ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና ከዋልታ ኢንፎርሜሽን መስማታቸውን ቢጠቅሱም «ካልታዘልኩ አላምንም» አለች እንደተባለዉ ሙሽራ አይነት ሆኖባቸዋል። «ይህ ህዝባችን በከፍተኛ ደረጃ በአንደኝነት ሲጠይቀው የቆየ የሕዝብ ጥያቄ ነው። የፓርቲያችንም ጥያቄ ነው። እንዳልሽዉ ኦፌኮ በከፍተኛ ደረጃ ከስራ አመራር ኮሚቴ በከፊል ሥራ አመራሮቹ ታስረው ሲሰቃዩ የቆዩ ስለሆኑ መፍታቱ አንድ ርምጃ ነው እንላለን፤ ተግባራዊ ከሆነ እና ሰዎቹ ከተፈቱልን።»

አቶ ሙላቱ እንዳነሱት በፍርድ ቤት ደረጃ የተወሰኑ ጉዳዮች በማረማያ ቤቶቹ ተግባራዊ ሳይሆኑ የቀሩባቸው አጋጣሚዎች ይታወሳሉ። አሁን ግን ፍርድ ቤት ሳይሆን ሀገሪቱን የሚያስተዳድረዉ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነዉ ገዢ ፓርቲ ማለትም መንግሥት ያሳለፈው ዉሳኔ መሆኑ ነው የተነገረው። አቶ ሙላቱ ግን እንዲህ ነዉ የሚሉት።

«መንግሥት ወክሎ የሚፈታ ፍርድ ቤት አለ፤ እንግዲህ የፍትህ ሥራን የሚሠሩ ሰዎች ናቸዉ። ፍትህን የሚያዛባ መንግሥት መቼም እንዴት ነዉ ብለን ለመቀበል መቼም ኢህአዴግ አንድ ነዉ አራትም ሆነ ሦስት እኛ አንድ አካል ነዉ ብለን ነዉ የምንወስደዉ። እዉነተኛዉን የምናየዉ በተግባር ከተገለጸ በኋላ ነዉ። ተግባራዊነቱን እየተጠባበቅን ነዉ ያለነዉ።»

ከኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ አመራሮች የአንዱ ማለትም የሊቀመንበሩ የዶክተር መረራ ጉዲና ጠበቃ፣ የሕግ ምሁር እና የፖለቲካ አዋቂዉ ዶክተር ያዕብ ኃይለማርያም በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሂደት ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነዉ ብለውታል።

Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

«እንግዲህ በጣም ደስ የሚል ዜና ነው፤ የሕዝብ ትግል የሕዝብ አንድነት ምን ያህል ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ጥሩ ጠቋሚ ነው። እና ለኢትዮጵያውያን ደግሞ በዴሞክራሲ ሂደት ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው ማለት ይቻላል።  እና በይቅርታ መታለፉ፣ ክሳቸው መሰረዙ፣ እሚገባው ነው መሆንም የነበረት ነው። እውነቱን ለመናገር ሕጉን በተመለከተ ብዙዎቹ የተፈረደባቸው አግባብ እንዳልነበረ ብዙ የሕግ ምሁራን ሊያውቁት የሚቻል ነገር ነው። አንዳንድ የታሠሩባቸዉ ሕጎች ለምሳሌ እንደ ፀረ ሽብር ሕግ የመሳሰሉቱ ፍጹም በዓለም የሰብዓዊ መብት ሕጎች አንጻር ሲገመገም በፍጹም ማንንም ሊያስቀጣ የሚችል ሕግ አይደለም።»

የተቃዉሞ ፓርቲዎችም ሆኑ የመብት ተሟጋች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ዉስጥ እጅግ በርከት ያሉ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። ቁጥራቸዉን በተመለከተ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጫ ባይሰጥም በሺህዎች እንደሚቆጠሩ ይነገራል። መንግሥት ዛሬ ወሰንኩ ያለዉ አንዳንድ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታትን የሚመለከት መሆኑን ለመንግሥት ቅርበት ያለዉ መገናኛ ብዙሃን ይፋ ያደረገዉ ዘገባ ይጠቁማል። ይደረጋል የተባለው ምህረት ልዩነት ይኖረዉ ይሆን? ዶክተር ያዕቆብ፤

«ዜናዉ የተነገረው እርግጥ የተፈረደባቸውም በምህረት ይለቀቃሉ፤ ክስ ላይ ያሉት ደግሞ ክሱ ይቋረጣል የሚል ነው እንግዲህ የሰማነው። እና ይሄ በእውነት ተገቢ ነገር ነው። ቀደም ብዬ እንዳልኩት መጀመሪያውኑ መታሰር የሌለባቸው ሰዎች ናቸው የታሰሩት። እንዲሁ በጅምላ በአሸባሪ ተብለው የታሰሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አሉ፤ እነሱ ሁሉ መፈታት አለባቸው። በዚህ በጸረ ሽብር፣ ሕገ መንግሥቱን በመናድ በዚህ በዚህ በመሳሰሉት ክሶች የተከሰሱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ መለቀቅ አለባቸው፤ እገሌ እገሌ የሚባል ነገር የለም። ይሄ በሕግም የሚጠየቅ ነገር ነው። ለሀገራችንም የሚበጀው መንገድ ይኸው ነው።»

በሀገሪቱ አመቺ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግም ሆነ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ይፈቱ የሚሉ ጥያቄዎች በሀገር ዉስጥም ሆነ ከዉጭ የሚቀርብለት መንግሥት በተደጋጋሚ የፖለቲካ እስረኛ በሀገሪቱ የለም የሚል ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል። ዛሬ የተሰማው ግን የተፈረደባቸዉም ሆነ ጉዳያቸዉ እየታየ የሚገኝ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መንግሥት መወሰኑ ነው። ከዚህ ዉሳኔ ያደረሰው ምን ይሆን? አሁንም አቶ ሙላቱ

Äthiopien Irreecha Feierlichkeiten
ምስል DW/Y. Gebregzihabher

«ከአሁን በፊት ቅድም እንዳልሽዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይፈቱ ብለን ለመንግሥት እንኳን አቤቱታ ስናቀርብ አንድም ሰዉ የፖለቲካ እስረና በሀገሪቷ ዉስጥ የለም፤ የታሠሩት በሙሉ ወንጀኞች ናቸዉ ሲሉን እና ፍርድ ቤት ሲያመላልሱን የቆዩ ሰዎች ናቸዉ። አሁን ግን እዉነታዉ የሕዝብ ትግል እያየለ በመምጣቱ፤ መንግሥት ሕዝብ ወደማዳመጡ ካላዘነበለ በየጊዜዉ መግለጫ በመግለጫ በማዉጣት ብቻ ይህችን ሀገር ማሻሻል እንደማይቻል፤ የህዝብን ጥያቄ መፍታት እንደሚገባ፤ መልስ መስጠት እንደሚገባ ሊረዳም ይገባል፤ ከዚህ በላይም ሕዝብ እየተጠየቀ ያሉት በሙሉ ጥያቄዎች መልስ እስካልተሰጠ ድረስ ትግሉ ስለሚቀጥል በዚህ ያበቃል ማለት አይደለም። አሁንም ርምጃ መዉሰዱ ጥሩ ነዉ።»

በየጊዜው በዚያ በታሰሩ እና ታስረው በሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ላይ ቁም ስቅል ይፈጸምበታል ተብሎ የሚጠቀሰው በተለምዶ ማዕከላዊ በመባል የሚታወቀው እስር ቤት ይዘጋል መባሉን የሰሙት አቶ ሙላቱ፤ እሱ አንድ ነገር ሆኖ ለተለያዩ ወንጀሎች በተጠያቂነት መቅረብ የሚገባቸዉ ሰዎች ጉዳይም መታየት አለበት ባይ ናቸዉ።

 «የሰቆቃ ቦታ ደም የፈሰሰበት ፤ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚካሄድበት ቦታ ስለነሆነ በመዘጋቱ ሕዝባችንም ደስ ይለዋል እኛም እሰይ እንላለን። ነገር ግን የእኛ ጥያቄ ብቻ አይደለም፤ ብዙ ሰው ወጣት፣ የ13 የ12 ዓመት ልጆች የሞቱበት፣ አሮጊቶች፣ ሽማግሌዎች የሞቱበት፤ አሁንም በመሞት ላይ ያሉ ሰዎች አሉ። እስካሁን ድረስ ተኩስም አልቆመም። ጦር ሠራዊት በየቦታው እየተበታተነ፣ በየወረዳው ደረጃ ሕዝብን ቤት ገብቶ እየደበደበ፣ እየገረፈ፣ ሕዝባችን ብዙ ጥያቄ አለው። ሕዝብ የሞተበት ምንም የደም ካሣ ወይም ደግሞ ጉማ ያልተከፈለ ለኦሮሞ ደም፤ በኢሬቻ ላይ ሕዝባችን አልቋል፤ እናም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በተለያዩ ቦታዎች፣ በአፋር፣ በሶማሌ ብዙ ሕዝብ ያለቀበት እና ደም የፈሰሰበት በመሆኑ ያንን ያደረጉ፤ ያዘዙ፤ አነጣጥረው ተኩሰው የገደሉ ሰዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸዉ።»

Äthiopien Trauer für gestorbenen Demonstranten
ምስል REUTERS/Tiksa Negeri

ለዶክተር ያዕቆብ በዚህ ስፍራ በአንድ ወቅት ታስረዉ እንደነበር በማስታወስ በበኩላቸው ይህን ብለዋል፤

«ይሄ ወህኒ ቤት ጣልያኖች የሠሩት ወህኒ ቤት ነዉ። እኔም ለተወሰነ ጊዜ ኖሬበታለሁ። እና በእዉነት የሰው ልጅ ሊኖርበት፤ ለሰው ልጅ ጥበቃ ሊደረግበት የሚችል ቦታ አይደለም። በፍፁም ከሰውነት የወጣ ሁኔታ ነው ያለው እዚያ ውስጥ። እና መፍረስ ያለበት ነገር ነው ወይም ሙዚየም ተብሏል ሙዚየም መሆኑ ደግ ነዉ። ግን ደግሞ ከእንግዲህ ሰው በዚያ አይነት መያዝ የለበትም። ዓለም አቀፍ ሕግም ይደነግጋል። አንድ ሰው ሕግ ጥሰሃል ተብሎ በተያዘ ጊዜ ሰብዓዊ በሆነ መልኩ ነው መያዝ ያለበት። ማዕከላዊ ግን ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሰውን ማሰቃያ፣ ከሰውነት ውጭ የሚፈጸሙ ድርጊቶች መፈጸሚያ ነበር።»

ከፖለቲካ እስረኞች መፈታትም ከፍተኛ ማሰቃየት ይፈጸምበታል ከሚባለው እስር ቤት መዘጋት ባሻገር መንግሥት አሁንም ሊያስብበት የሚገባ ዋና ጉዳይ እንዳለ ነው የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ የሚያጠቁሙት።

«እንደምታውቂው እስካሁን ድረስ በሀገሪቱ ዉስጥ በሰላማዊ መንገድ የተደረገ የመንግሥት ሽግግር የለም። አሁን ግን እኛም ኢህአዴግን የምንለዉ ሰላማዊ የሆነ ሽግግር እንዲኖር ሕዝቦች በስምምነት የሚያቋቁሙት መንግሥት ሊኖር ይገባል እያልን ነው።»

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ