1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁለተኛው የመንግሥት ምሥረታ ጥረት በጀርመን

ረቡዕ፣ ኅዳር 27 2010

ሁለተኛው አማራጭ ታላቅ የሚባለው ጥምር መንግሥት ምሥረታ ቢሆንም ለዚህ ጥምረት የሚያስፈልገው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ከምርጫው ውጤት በኋላ ተቃዋሚ ሆኜ እቀጥላለሁ ያለበትን አቋሙን መቀየር የሚችለው አባላቱ ከተስማሙ ብቻ መሆኑን ማሳወቁ ሁለተኛውም ሙከራ መሳካት መቻል አለመቻሉን ጥያቄ ውስጥ ከቷል።

https://p.dw.com/p/2ooja
Berlin - Steinmeier lädt zu GroKo-Gesprächen ein - Merkel u Seehofer
ምስል picture alliance/dpa/B. von Jutrczenka

የመንግሥት ምሥረታ ችግር በጀርመን

የጀርመን ህዝብ የምክር ቤት እንደራሴዎቹን ከመረጠ ሁለት ወር ከአንድ ሳምንት ቢያልፍም እስካሁን አዲስ መንግሥት አልተመሰረተም። አራት ፖርቲዎች ተጣምረው መንግሥት ለመመስረት ያካሄዱት ድርድር ያለ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ሌላ የመንግሥት ምሥረታ ጥረት ተጀምሯል።የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ህብረት  በጀርመንኛው ምህጻር CDU እና እህት ፓርቲው የክርስቲያን ሶሻል ህብረት CSU ባለፈው መስከረም በተካሄደው የምክር ቤት ምርጫ አብላጫ ድምጽ ቢያገኙም እስካሁን መንግሥት መመሥረት አልቻሉም። ከምርጫው ውጤት በኋላ ባለፉት ዓመታት ከሁለቱ ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ ሀገሪቱን ይመራ የነበረው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር ኤስ.ፔ.ዴ በታላቁ ጥምር መንግሥት  እንደማይቀጥል ይልቁንም ተቃዋሚ እንደሚሆን ካሳወቀ በኋላ  ሴ.ዴ.ኡ እና ሴ ኤስ ኡ  ከነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በምህፃሩ ኤፍ.ዴ.ፔ እና ከአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ጋር ተጣምረው መንግሥት ለመመሥርት ቢደራደሩም በኤፍ.ዴ.ፔ አለመስማማት ምክንያት አልተሳካላቸውም። የድርድሩ መክሸፍ የፖለቲካ ሳይንስ ሙሁር እና የህግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋ እንደሚሉት፣ በተደራዳሪዎቹም ሆነ በሌሎች ፖለቲከኞች ዘንድ የተጠበቀ አልነበረም። ከውጤቱ በኋላ የተፈጠረው ሁኔታም በርሳቸው አስተያየት ይህንኑ የሚያሳይ ነው።
በድርድሩ ከተሳተፉት ከጃማይካ ባንዲራ ቀለም ጋር ከሚመሳሰለው የየፓርቲዎች አርማ ቀለም  ማለትም ከሴ.ዴ.ኡው ጥቁር፣ ከኤፍ.ዴ.ፔ ቢጫ እና ከአረንጓዴዎቹ አረንጓዴ ቀለማት በመነሳት ጀማይካ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ጥምር መንግሥት ምሥረታ በመክሸፉ፣ ሁለተኛ የመንግሥት ምሥረታ ሙከራ ተጀምሯል። ሁለተኛው አማራጭ ታላቅ የሚባለው ጥምር መንግሥት ምሥረታ ቢሆንም ለዚህ ጥምረት የሚያስፈልገው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ከምርጫው ውጤት በኋላ ተቃዋሚ ሆኜ እቀጥላለሁ ያለበትን አቋሙን መቀየር የሚችለው አባላቱ ከተስማሙ ብቻ መሆኑን ማሳወቁ ሁለተኛውም ሙከራ መሳካት መቻል አለመቻሉን ጥያቄ ውስጥ ከቷል።  በታላቁ ጥምር መንግሥት ውስጥ ሊሳተፉ የሚችሉት የሴዴኡ መሪ አንጌላ ሜርክል የሴ ኤስ ኡ መሪ ኽርስት ዜሆፈር እንዲሁም የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ መሪ ማርቲን ሹልትስ በጉዳዩ ላይ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ከጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በጋራ መክረው ነበር። ከምክክሩ በኋላ የኤስ ፔ ዴ መሪ «መንግሥት ለመመሥረት ሁሉንም አማራጭ መሞከር እንደሚገባ ሆኖም ጥምር መንግሥት የመመሥረቱ ጉዳይ ገና ያልተጨበጠ»መሆኑን አሳውቀው ነበር። ትናናት በሰጡት አስተያየትም ጉዳዩ በዚህ ሳምንት ሐሙስ ፓርቲያቸው ለሁለት ቀናት በሚያካሂደው ጉባኤ ላይ መልስ እንደሚያገኝ ተናግረዋል። 
«ሁሉም ነገር በእቅዳችን መሠረት የሚሄድ ከሆነ የቀረበውን ሀሳብ የኤስፔዴ ፓርቲ ጉባኤ ይቀበለው አይቀበለው ሐሙስ ምሽት ከፓርቲው ጉባኤ በኋላ ግልጽ ይሆናል። ተቀባይነት ካገኘ ከወይዘሮ ሜርክል እና ከአቶ ዜሆፈር ጋር  ቀጠሮ እይዛለሁ። በዚህ ስብሰባ ላይ የምንነጋገረው በጽሁፍ የተቀመጠውን ሀሳብ መሠረት አድርገን ነው። ከዚያ በኋላ በንግግሩ መቀጠሉ ትርጉም የሚሰጥ መሆን አለመሆኑን እናውቃለን።»
ሹልትስ እንዳሉት ፓርቲያቸው ሐሙስ የሚደርስበት ውሳኔ ለሀገራቸው ለአውሮጳ እና ለዴሞክራሲ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚሻለው ምንድነው የሚለውን ጥያቄ መሠረት ያደረገ ነው የሚሆነው። የፓርቲያቸው አባላት ወደ ጥምር መንግሥት ምሥረታ ንግግር እንዲገባ ከተስማሙ በመጪው ሳምንት የመንግሥት ምሥረታው ድርድር ሊጀመር ይችላል እንደ ሹልትስ። ይሁንእና በዶክተር ለማ አስተያየት የኤስ ፔ ዴ እና  የሴዴኡ ወጣት አባላት እንዲሁም ሌሎች የየፓርቲዎቹ አባላት ከያዙት የተለያየ አቋም በመነሳት ወደ ታሰበው የመንግስት ምሥረታ ድርድር መገባቱን ይጠራጠራሉ። 
በዚህ መካከል የሴዴኡ እህት ፓርቲ የሴኤስኡ መሪ እና የባቫርያ ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር  ኽርስት ዜሆፈር በጎርጎሮሳዊው 2018 በባቫርያ ግዛት በሚካሄደው ምርጫ አልወዳደርም ማለታቸው ከSPD ጋር የተረጋጋ መንግሥት ለመመሥርት በሚደረገው  ጥረት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል የሚል ስጋት ፈጥሯል። የስጋቱ መነሻም ርሳቸውን የሚተኩት ማርኩስ ዘደር ይበልጡን ወደ ቀኝ የሚያደላ አቋም ያላቸው መሆኑ ነው።  ያም ሆኖ ዜሆፈር  በርሳቸው እና በተተኪያቸው መካከል ጠንካራ ትብብር ይኖራል ብለው ይጠብቃሉ። ፓርቲያቸው የሚፈልገውም ከሶሻል ዴሞክራቶች ጋር ተጣምሮ መንግሥት መመሥረት ነው። ይህ ግን በርሳቸው አባባል በኤስፔዴ እጅ ነው ያለው።
«በመጀመሪያ ደረጃ የሚያሳስበኝ የፓርቲዎቹ መሪዎች ለፕሬዝዳንቱ በገባነው ቃል መሠረት ሥራውን ማካሄድ የሚችል መንግሥት መመሥረቱ ነው። ይህ ነው የመጀመሪያው ግባችን። ባቫርያ እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት የሚሰሩትም ለዚሁ ነው።  ይህ ይሳካ አይሳካ ማንም ከወዲሁ ምንም ማለት አይችልም። ይህ ሁኔታ ለሳምንታት ይዘልቃል። አንዱ ወይም ሌላው ስብሰባ በዚህ ዓመት ሊካሄድ ይችላል። ይህ ግን ሶሻል ዴሞክራቶች ለመስማማት በተዘጋጁበት ጉዳይ ነው የሚወሰነው።»
ከመስከረሙ የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ በኋላ የተካሄደው የመጀመሪያው የመንግሥት ምሥረታ ጥረት ከሽፎ አሁን የተያዘው ሁለተኛው ሙከራ በሂደት ላይ ነው። ይሳካ አይሳካም አይታወቅም ።የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው በጀርመን አዲስ መንግሥት ምሥረታ መዘግየቱ የተለያዩ ተጽእኖዎችን ማሳደሩ አይቀርም። እንደ ይልማ ከሁሉም በላይ ሀገሪቱ በውጭ ላላት ገጽታም ሆነ ለዜጎች የተረጋጋ ሥራ እና ህይወት የመንግሥት ምሥረታው መፋጠን ወሳኝ ነው።
የትልቁ ጥምር መንግሥት ምሥረታ ሙከራ ካልተሳካ ሁለት አማራጮች ናቸው የሚቀሩት። አንደኛው የክርስቲያን ዴሞክራቶች  እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲዎች ከአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎቹ ጋር ተጣምረው የሚመሰርቱት አናሳ መንግሥት ካልሆነ ደግሞ ሌላ ምርጫ ማካሄድ ነው። 
ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ በጀርመን ህግ መሠረት ሊሆን የሚችለውን ያስረዳሉ። ጀማይካ የሚባለው ጥምረት ሙከራ ሳይታሰብ መክሸፉ አስደንግጧል። ሁለተኛው የመንግሥት ምሥረታ ጥረትም መሳካቱ ጥያቄ ውስጥ ነው። ጀርመን ግን አዲስ መንግሥት መመሥረት አለባት። ግን እንዴት? አብረን የምናየው ይሆናል።

Combo Angela Merkel und Martin Schulz
ምስል Getty Images/AFP/T. Schwarz
Berlin - Steinmeier lädt zu GroKo-Gesprächen ein
ምስል picture-alliance/Bundesregierung/G. Bergmann
Berlin - Steinmeier lädt zu GroKo-Gesprächen ein
ምስል picture-alliance/Bundesregierung/G. Bergmann

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ