1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመቅዲሾ እና የኡጋንዳ ሽምግልና

ማክሰኞ፣ መስከረም 28 2000

የሶማልያ የሽግግር መንግስትን ለመርዳት ከኢትዮጽያ የጦር ሰራዊት ጋር በመቅዲሾ ተሰልፎ በሚገኘዉ በኡጋንዳዉ የጦር ሰራዊት የጦር ሰፈር ላይ የጥቃት ሙከራ እንዳተጣለ ተገለጸ። ባለፈዉ ሳምንት ማጠናቀቅያ ላይ የኡጋንዳዉ የጦር ሰራዊት በሶማልያ የሽግግር መንግስት እና በተቃዋሚዎች መካከል ድርድር ለማደረግ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ መሆኑን ገልጾአል።

https://p.dw.com/p/E0Y5
የኡጋንዳ ወታደሮች በመቅዲሾ
የኡጋንዳ ወታደሮች በመቅዲሾምስል AP

የሶማልያን የሽግግር መንግስት ከሚረዳዉ ከኢትዮጽያ የጦር ሰራዊት ሌላ የአፍሪቃዉን ህብረት ወክሎ በሶማልያ በሚገኝዉ በኡጋንዳዉ የጦር ሰራዊት ላይ የጥቃት እርምጃ መድረሱን የጦሩ ሰራዊቱ ቃል አቀባይ ካፒቴን Paddy Ankunda በመቅዲሾ መሰጡት መግለጫ አስታዉቀዋል። ጥቃቱ ከመቅድሾ አራት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘዉ የአፍሪቃዉ ህብረት የጦር ሰፈር ላይ ሁለት ከባድ ፍንዳታ እንደነበር ታዉቋል። በሶማልያ መቅዲሾ የሚገኘዉ የሮይተርስ የዜና ወኪል ጋዜጠኛ ጥቃቱ በጣም ትልቅ ነበር ሲል በስልክ በተለይ ለዶቸ-ቬለ ሲገልጽ
ትልቅ ጥቃት በሶማልያ መቅዲሾ ሰፍረዉ በሚገኙ የአፍሪቃዉ ህብረት ወታደሮች የመኖርያ ጣብያ ላይ እንደደረሰ አዉቃለሁ ነገር ግን በጥቃቱ ማንም አልተጎዳም ነበር ያለዉ
በሳምንቱ ማጠናቀቅያ ላይ በሶማልያ የሚገኘዉ የኡጋንዳ የጦር ሰራዊት መሪ Ngoma Ngime አገራቸዉ በሶማልያ የሽግግር መንግስት እና በአሪገቷ ዉስጥ ከሽግግሩ መንግስት ጋር በመዋጋት ላይ ያሉ ተቃዋሚዎችን ፣ በጎረቤት ኤርትራ የሚገኙ የሽግግር መንግስቱን የሚቃወሙ ሶማልያዉያንን ለማደራደር ዝግጅት ላይ መሆንዋን አስታዉቀዋል። ጥረታችን ቁርጠኛ ነዉ በሶማልያ ሰላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን ሲሉ ማስታወቃቸዉም ተገልጾአል።

ሞቃዲሾ ውስጥ በሶማሊያ መንግሥት ወታደሮችና በዓማጺያን መካከል በሚካሄደው ውጊያ ባለፈው አርብ እለት ብቻ 2 የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ 8 ሲቪሎች መገደላቸውን የአይን ምስክሮች ገልጸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰሜናዊ መቅዲሾ አንድ ማንነቱ ባልታወቀ ታጣቂ የቀድሞ የሶማልያ የጦር ጀነራል Ahmed Jilow Addow ን እና ሹፊራቸዉ መገደላቸዉን የአካባቢዉ ሆስፒታል ገልጾአል። በሶማልያ በተለይ በመቅዲሾ በርካታ ሲቪሎች በቦንብ ፍንዳታ፣ ኢላማ በተደረገ ግድያና የተኩስ ሰለቦች በመሆን ሕይወታቸውን በማጣት ላይ ይገኛሉ።
በሶማልያ ማቆምያ ያጣዉን ጦርነት ለማብቃት የኡጋንዳ መንግስት በተቀናቃኝ ቡድኖች እና በሶማልያ የሽግግር መንግስት ለሰላም ድርድር ዝግጅት ሲያደርግ፣ በሶማልያ የሽግግር መንግስቱ ተቃዋሚ ሃይሎች የኢትዮጽያ የጦር ሰራዊት ከአገሪቷ ለቆ እስካላስወጣ ለድርድር አንቀርብም ማለታቸዉም ተገልጾአል። የሶማልያን የሽግግር መንግስት የሚረዳዉ ኢትዮጽያ የጦር ሰራዊት ከዘጠኝ ወራት በፊት በደቡባዉ እና በመካከለኛዉ የሶማልያ ክፍል አክራሪ እስላማዊ የንቅናቄ ሃይሎችን ካባረረ በኻላ በቁጥር ያልታወቁ የጦር ሃይሎች በሶማል እንደሚገኙ ይታወቃል። የአፍሪቃዉን ህብረት ወክሎ ደግሞ 1500 ያህል የኡጋንዳ ጦር በሶማልያ ሰፍሮ እንደሚገኝ ተጠቅሶአል።