1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስራ መጀመር እና ትችቱ

Eshete Bekeleሰኞ፣ መስከረም 24 2008

5 ተኛው የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ ። አቶ ኃይለ ማርያም ምክር ቤቱ የሰጣቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ቃለ መሓላ ፈጽመዋል፡፡

https://p.dw.com/p/1Gj0r
Äthiopien Parlament Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. G. Egziabher

[No title]

5 ተኛው የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ ። አቶ ኃይለ ማርያም ምክር ቤቱ የሰጣቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ቃለ መሓላ ፈጽመዋል፡፡ ምክር ቤቱ አቶ አባዱላ ገመዳን ለአፈጉባኤነት እንዲሁም ወይዘሮ ሽታዬ ምናለን በምክትል አፈጉባኤነት በድጋሚ መርጧል ። የፌደሬሽን ምክር ቤት በበኩሉ ዛሬ ጠዋት ባካሄደው ስብሰባ አቶ ያለው አባተን በአፈ ጉባኤነት አቶ መሀመድ ረሺድ ሃዲን ደግሞ በምክትል አፈ ጉባኤነት ሾሟል ።

የአዲሱ ምክር ቤት ምስረታ ግን ትችቶች አላጡትም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ የመንግስት አወቃቀር ከፍተኛው የስልጣን ባለቤት የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካለፉት 20 አመታት ወዲህ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል ነው የተመሰረተው።

በኢትዮጵያ የተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ-ጉባዔዎቻቸውን ሲመርጡ ገዢው ፓርቲም የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲያቀርብ የተሰሙት ድምጾች ተመሳሳይ ናቸው-ድጋፍ። ተቃውሞም ሆነ ድምጸ ተዓቅቦ በዛሬው የኢትዮጵያ መንግስት ምስረታ ሂደት አልተደመጡም። ጋዜጠኛ ዮሐንስ አንበርብር የሁለቱን ምክር ቤቶች ጉባዔዎች የተከታተለ ጋዜጠኛ ነው። ዮሐንስ የዛሬው የሁለቱ ምክር ቤቶች ጉባዔ ከቀደሙት የቀዘቀዘ ሆኖ አግኝቶታል።

«ተቃዋሚዎችም አብላጫው ተቀበለም አልተቀበለ የራሳቸውን ድምጽ ያሰሙ ነበር።» የሚለው ጋዜጠኛ የስልጣን ድልድሉ በገዢው ፓርቲ አልቆ ለተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ በመሆኑ አዲስ ነገር አይጠበቅም ሲል ተናግሯል።

Äthiopien Parlament Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. G. Egziabher


በተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ባገለገሉባቸው አመታት በሰላ ትችቶቻቸው የሚታወቁት ዶ/ር መረራ ጉዲና «170 ተቃዋሚዎች በምክር ቤቱ በነበሩበት ጊዜም ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሚለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መመሪያ ይሰራ ነበር።» ሲሉ ይናገራሉ። በአምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተሳተፉት ዶ/ር መረራ «ዛሬ ያለው ፓርላማ ሳይሆን የኢህአዴግ ምክር ቤት ነው።» ሲሉ ይተቻሉ።


የአገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት፤ ህጐችን የማውጣት የህግ አስፈጻሚው አካል የሚዋዋላቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶች የማጽደቅ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ሌሎች የፌዴራሉ መንግሥት ባለሥልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የአስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ስልጣን ተሰጥቶታል። የፌዴራል መንግሥት ፍርድ ቤት ዳኞችን፣የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን፣ የኮሚሽነሮችን የዋናው ኦዲተርን የመሳሰሉ ኃላፊነቶችም የሚጸድቁት በዚሁ አሁን በኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎቹ በተሞላው ምክር ቤት ነው። በምክር ቤቱ የሚሰሙት ድምጾች ተመሳሳይነት ግን ኃላፊነቱን ለመወጣት ሳንካ ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ይደመጣል። ጋዜጠኛው ዮሐንስ አንበርብር ይህ ጉዳይ በገዢው ኢህአዴግ ቁርጠኝነት የሚሻ መሆኑን ይናገራል። «ፓርላማው ሥራ አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ስራ እንዲሰራ የፖለቲካ ስልጣን ከተሰጠው ስኬታማ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።» የሚለው ዮሐንስ ለተግባራዊነቱ ግን ጥርጣሬ አለው።


ዶ/ር መረራ ጉዲና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በኢትዮጵያ ፈተና እንደገጠመው ያምናሉ። አሁን ያለውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር «ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ወይም ግንባታ የሚባለውን የተለየ ሃሳብ ይንጸባረቃል የሚባለውን ሙሉ በሙሉ ያቆመበት።» ሲሉ ይገልጹታል።

በዛሬው ጉባዔ አገሪቱን ለሚቀጥሉት አምስት አመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመሩ የተመረጡት አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ነገ ካቢኔያቸውን ይመሰርታሉ ተብሎ ይጠበቃል። የካቢኔ ምስረታውም ሂደት ቢሆን ግን አዲስ ነገር አይጠበቅበትም።

Äthiopien Parlament
ምስል DW/Y. G. Egziabher


ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

እሸቴ በቀለ
ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ