1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ድብደባ 1ኛ አመት: ዉጤትና አስተምሕሮቱ

ሰኞ፣ መጋቢት 17 2004

የሊቢያን ሕዝብ ከጥቃት ያድናል በተባለዉ ድብደባ መዘዝ ማሊም ተመሰቃቀለች።የሊቢያዉ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መጥፎ አስተምሕሮት ለሶሪያ እልቂት ፍጅት መባባስ፥ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት መከፋፈል ትልቅ ምክንያትም ሆነ የፓሪስ፣ ለንደን፣

https://p.dw.com/p/14SSB
A Libyan man stands over a destroyed tank as he flashes V signat Al-Katiba military base after it fell to anti-Libyan Leader Moammar Gadhafi protesters few days ago, in Benghazi, Libya, on Thursday Feb. 24, 2011. A Libyan witness says a Libyan army unit has blasted a minaret of a mosque in a city west of Tripoli. The witness tells The Associated Press by telephone that several protesters, who have been camped inside and outside the mosque while demanding the ouster of Moammar Gadhafi, have been killed or seriously wounded in Thursday's attack. (AP Photo/Hussein Malla)
ሊቢያ:- ድሉምስል AP


ዋሽንግተኖችን ሠወስትነት፣የአባሪ-ተከታዮቻቸዉን ብዙነት አኮስምኖ ባንድ ያቆመዉ፥ የረጅም ጊዜ ዕቅድ፣አላማን በድል ያሳረገዉ የሊቢያ የጦር ዘመቻ ከተጀመረ ባለፈዉ ሰኞ አመት ደፈነ።ድብደባዉን ሰወስቱ መንግሥታት የሚዘዉሩት የጋራ የጦር ድርጅት ኔቶ ከተረከበ ደግሞ የፊታችን ሰኞ አመቱ።የሐያላኑ የአመታት ደመኛ፣ የሪያድ፣ ዶሐ፣ የአማን ራባት ነገስታት ባላንጣ፣ የቤንጋዚዎች የቀድሞ ክቡር አለቃ፣ የኋላ ጠላት ኮሎኔል ሙዓመር አል-ቃዛፊ፣ ሲርት ላይ ከተፈፀሙ ስድስት ወሩ።ቃዛፊን ከነሥርዓታቸዉ የገደለዉ ድብደባ የተጀመረበት አንደኛ አመት መነሻ፣ ዉጤት አስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ለዘመናት እንደ ጠላት ሲያድኑ፣ ሲያወግዙ፣ ሲቀጡ፣ሲያገሏቸዉ የነበሩት የምዕራባዉያን ባለሥልጣናት እንደ ተባባሪ አቅርበዉ እንደ ወዳጅ ለመጎብኘት ወደ ትሪፖሊ በሚግተለተሉበት በሁለት ሺ ስምንት (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከትሪፖሊ ድንኳናቸዉ በር ላይ ይገፋፉ ከነበሩ አያሌ የምዕራብ ሐገራት ጋዜጠኞች አንዱ ሥለሚመሩት ሕዝብ ኑሮ ጠየቃቸዉ።

«ሰዉ» አሉ ሰዉዬዉ «ጀነት ዉስጥ ቢሆን እንኳን ማማረሩ አይቀርም፥ ሊቢያ አሁን ጀነት ነች።» ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ።የጀነትነቱ ንፅፅር ከባድ ምናልባትም ዉሽት ይሆን ይሆናል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት የመሰከረዉ እዉነት ግን እንዲሕ ነዉ።ቃዛፊ በ1969 ሥልጣን ሲይዙ አብዛኛዉ ሊቢያዊ ግመል እየጎተተ ከቦታ ቦታ የሚዞር፣ ደሳ ዉስጥ የሚኖር ዘላን፥ማይም ነበር።በሁለት ሺሕ አስር ግን ሰባት ሚሊዮን ከሚገመተዉ ሊቢያዊ ግማሽ ያሕሉ አንድም የዩኒቨርስቲ ምሩቅ፥ አለያም የከፍተኛ ተቋማት ተማሪ ነዉ።

በ1950 ሊቢያ አንዲት ዩኒቨርስቲ ነበራት፥ በሁለት ሺሕ አስር የሰማንያ-አራት ዩኒቨርስቲዎች፥ ኮሎጆችና ከፍተኛ ተቋማት ባለቤት ሆናለች።ሰማንያ ሁለት ከመቶዉ ሊቢያዊ የተማረ ነዉ።ቃዛፊ ሥልጣን ከመያዛቸዉ ከሁለት ዓመት በፊት የሊቢያ ሕዝብ የነብስ ወከፍ ገቢ አንድ-ሺሕ ዶላር ነበር።ቃዛፊ ከመገደላቸዉ አንድ አመት በፊት ግን ወደ አስራ-አራት ሺሕ ተንቻሯል።

በሰብአዊ መሠረታዊ ልማት ከአፍሪቃ ከሲሸልስ በተቀር ከሊቢያ የሚስተካከል የለም።በጊሰን-ጀርመን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር አንድሪያስ ዲትማን እንደሚሉት የቃዛፊ አረመኔ፥ አምባገነንነት፥ አሸባሪነትን እንጂ አልሚ፥ አበልፃጊ፥ አስተማሪነታቸዉን በትክክል የሚያዉቅ የለም።

«ከ1969 ጀምሮ ቃዛፊ የሐገሪቱን በርካታ ሐብት ለሐገሪቱ ልማት ማዋላቸዉና በርካታ የልማት አዉታሮች መገንባታቸዉ አያጠራጥርም።በዛሬዋ ሊቢያ አብዛኛ ወጣት ዘንድ ግን ይሕ በቅጡ አይታወቀም።ቃዛፊ አሸባሪዎችን ደጋፊ፥አምገነን፥ ፈላጭ ቆራጭ ብቻ አልነበሩም፥አልሚዉ ቃዳፊ ጭምር እንጂ፥ በተለይ በወጣትነት ዘመናቸዉ።»

ለረጅም ጊዜ ከቴል አቪቭ፥ ከለንደን፥ ከአትላንታ፥ከኒዮርክ፥ ከፓሪስ፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲሕ ደግሞ ከዶሐ ለድፍን አለም የሚንቆረቆሩት ዘገባዎች ቃዛፊን ከ«እብድ ዉሻነት፥ አሸባሪ፥ አረመኔ ጨቋኝነታነት ባለፍ ሥለ ሌላዉን ጎናቸዉን ብዙም የነገሩን የለም።ዛሬም-እንዲሁ።

የዶቼ ቬለዉ ዘጋቢ ማርክ ዱገ ግን በቅርቡ ማሊ-ርዕሰ ከተማ ባማኮ ነበር።«ወደ አንድ የእደ-ጥበብ ዉጤት መደብር ጎራ አልኩ።» ይላል ጋዜጠኛዉ።ቀጠለ፥-ቃዛፊ የወታደር ልብስ-መለዮቸዉን ለብሰዋል።የፀይ መነፅር አድርገዋል።ፈገግ እንዳሉ ነዉ።ትልቁ ፎቶ-ግራፍ ወየብ ብሏል።ግን ከሱቁ በር በላይ ባለዉ ስፍራ በክብር ተቀምጧል።» የሱቁ ባለቤት ሶንካሎ እንደሚለዉ ደግሞ ሌላ የሚያደርገዉ ሥለ ሌለ እንጂ ለቃዛፊ ያለዉ ክብር ያን ፎቶ-ግራፍ በመስቀሉ የሚገለጥ አይለም።

«የቃዛፊን ፎቶ ግራፍ የሰቀልነዉ፥ እሳቸዉ ለአፍሪቃ ብዙ በማድረጋቸዉ ነዉ።እዚሕ በጣም ብዙ ገንዘብ ሥራ-ላይ አዉለዋል።ለዚሕ ነዉ የምናከብራቸዉ።በመገደላቸዉ ክፍኛ አዝነናል።ብዙ ችግሮቻችንንም አስፍቶብናል።»

አምና ይኸኔ።ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከምረጡኝ ዘመቻቸዉ ጀምሮ እንደዛቱት ኢራቅ የሰፈረ ጦራቸዉን በቆረጡት ቀን ማስወጣቱ አልከበዳቸዉም። ኢራቅ ግን እንደመተሰቃቀለች ነዉ። ወደ አፍቃኒስታን ተጨማሪ ጦር አዝምተዉ የአፍቃኒስታኑን ጦርነት ባጭር ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ የገቡት ቃል ዉል ስቶ ጦርነቱ የወታደሮቻቸዉን፣ አካል፣ ሕይወት የሐገራቸዉን ሐብት እያሻመደዉ ነዉ።

ፍልስጤምና እስራኤሎችን ለማስማማት የገቡት ቃልም በዜሮ ተጣፍቶ።ዜሮ ላይ ቆሟል።በዚሕ መሐል ሆስኒ ሙባረክን የመሳሰሉ የሐገራቸዉ ታማኝ አገልጋዮች በሕዝብ አመፅ ከየሥልጣናቸዉ እየተወገዱ ነዉ።የሰነዓ፣ የማናማ፣ የአማንና ሎችም ታማኞች ሥልጣንም በየሐገሬዉ ሕዝብ አመፅ እየተገዘገዘ፥ ሕዝቡ ከየገዢዎቹ እኩል ገዢዎቹ ያደሩላቸዉን ሐያላንን እያወገዘ ነዉ።

ዋሽግተን ከሙባረክ እኩል ተወግዛ ሙባረክን እንዳጣች ሁሉ፣ ፓሪስ ቤን ዓሊን አጥታ ቱኒስ ላይ
ለዘመናት የተከለችዉ እግሯ ባይነቀል ተሰንክሎባታል።ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና ቶኒ ብሌር ኢራቅ ያዘመቱት ጦር ገድሎ፣ ሞቶ፣ አሸብሮ-ተሸብሮ ሳዳም ሁሴንን ያስወግድ እንጂ የባግዳድን ቤተ-መንግሥት የተረከቡት ኢራን የነበሩ፣ የቴሕራን ገዢዎች ወዳጆች፣ ሺዓዎች ናቸዉ።

ሺዓ የሚበዛበት የባሕሬን ሕዝብ አመፅ ንጉስ ሐሚድ ቢን ኢሳ አል ኸሊፋን ካስወገደ ሥልጣን የሚይዘዉ ሺዓ መሆኑ አላጠራጠረም።የየመን ሕዝብ አመፅ ዓሊ አብደላ ሳሌሕን ከሰነዓ ቤተ-መንግሥት ካፈናጠረ፣ የሁቲ አማፂዎች፣ ወይም የአል-ቃኢዳ ጀሌዎች የሚባሉት አክራሪዎች መሪነቱን ቢያጡ ወሳኝ ሥፍራዎችን መያዛቸዉ አይቀርም።

ይሕ ማለት ቤይሩትና ደማስቆ ላይ ደመቅ፣ ባግዳድ ሳሳ ብሎ የተዘረጋዉ የቴሕራን እጅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወደ ማናማና ሰነዓ ሊዘረጋ ነዉ ማለት ነዉ።የቴሕራን ተፅዕኖ መጠናከር ከቴል-አቪቭ ከዋሽግተን፤ ከለንደን፤ ከፓሪስ፣ ከበርሊን እኩል ለሪያድ፣ ለዶሐ፣ለአማን እና ለብጤዎቻቸዉም አስጊ ነዉ።

ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ለሬጋን፣ለታቸር፣ለሚትሯ ጠላት የነበሩትን ያክል ለዳግማዊ ቡሽ፣ለኦባማ፣ ለብሌር፣ ለካሜሩን፣ ለሲራክ፣ ለሳርኮዚ ወዳጅ-ባይሆኑ ጠላት አልነበሩም።ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ፣ ከፓኪስታን እስከ ሶማሊያ የተያዘዉ ጦርነት እንበለ ድል መቀጠሉ ያሰላቸዉን ሕዝብ ስሜት ለመግዛት፣ የተገባ ቃል መብነኑን ለማካካስ፣ ታማኝ ገዢዎችን በሚያስወግደዉ ሕዝብ፣ መወገዝ፣ መገለልን ለመግታት፣ የኢራኖችን መስፋፋት ለመገደብ፥ ከሊቢያዊ በላይ ለሊቢያ ሕዝብ መጨነቅ ግን በርግጥ ተገቢ ነበር።

በዚያ ላይ ሰዉዬዉ አሸባሪ ነበሩ።የሊቢያን ነዳጅ ዘይት በወርቅ-እንጂ በከሰረዉ ዶላር አልሸጥም እያሉ መታበይም ጀምረዋል።ከዓለም ባንክ ይሁን ከሌሎች የምዕራባዉያን ተቋማት ቤሳ-ቢስቲን አልበደርም ብለዉ የአበዳሪዎችን ጥቅም የተጋፉ ሞገደኛ ናቸዉ።ጭዳ መሆን አለባቸዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን።

«ኮሎኔል ቃዛፊ ቃላቸዉን አጥፈዋል።የተኩስ አቁሙን ጥሰዋል።የራሳቸዉን ሠላማዊ ሰዎች መግደሉን ቀጥለዋል።ይሕ መቆም አለበት።ማስቆም ይገባናል።እሳቸዉ አፀፋዉን መቀበል አለባቸዉ።»

ትሪፖሊን ለታማኝ አስረክቦ፥ የሚወድመዉን መሠረተ-ልማት በመጠገን ሰበብ ነዳጅዋን ማለብ።እና የደቀቀዉን ምጣኔ ሐብት መደጎምም ቀላል ነገር አይደለም።መጋቢት አስራ ሰባት-2011 የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የሊቢያን ሠላማዊ ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል የዉጪ ጦር ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቅደዉን ዉሳኔ፥-ቁጥር 1973 አፀደቀ።በማግስቱ።

«አምባገነኑ ለሕዝቡ ምሕረት የለም ብሎ ሲናገር እየሰማን፥ ወታደሮቹ እንደ ቤንጋዚ፥ ሚስራታ የመሳሰሉ ከተሞችን ሲያጠቁና ሠላማዊ ሰዎች በራሳቸዉ መንግሥት እጅ ሲገደሉ ዝም ብለን አናይም።ዩናይትድ ስቴትስ ሠላማዊ ሰዎችን ለማዳን ልዩ ችሎታችንን በግንባር ቀደምትነት ለዘመቻዉ ትለግሳለች።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ።የካሜሩንን እቅዱ፥ ኦባማ አፈፃፀሙን በተናገሩ ማግስት ሳርኮዚ ገቢራዊነቱን አንድ አሉት።መጋቢት አስራ-ዘጠኝ ማታ።የዩናይትድ ስቴትስ፣ የብሪታንያ እና የፈረንሳይ ፣ኋላ ደግሞ የኔቶ ጦር ከባሕር፣ ከሰማይ፣ የአማፂያኑና የሊቢያ መንግሥት ጦር ከምድር ያቺን ሐብታም ሰፊ ሐገር ያወድሟት ያዙ።ሊቢያ፣ የዘመተባት ጦር በስድስተኛ ወሩ የአርባ አንድ ዘመን ገዢዋን ከነ-ሥርዓታቸዉ ባስገደላላት ማግስት ወጪ-ቀሪዋን ታሰላ ያዘች።ከሰላሳ ሺሕ በላይ ተገድሏል።ከሐምሳ ሺሕ በላይ ቆስሏል።በቢሊን ዶላር የሚቆጠር ሐብት ንብረት ወድሟል።

ድብደባዉ የተጀመረበት አንደኛ አመት በዝም-ዝምታ በታወሰ በአራተኛዉ ቀን-ባለፈዉ አርብ የደረሰቺኝ ኢሜየል ደግሞ የዛሬ አመት የዛሬን ዕለት የሊቢያዉን ጦርነት ሽሽት በባሕር ሲጓዙ ያለቁትን አራት መቶ አፍሪቃዉያን ስደተኞችን ሙት አመት እንዘክር ትላለች።አብዛኞቹ የኤርትራዜጎች ነበሩ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች እንደገመቱት ጦርነቱን ሲሸሹ ባሕር የበላቸዉ አፍሪቃዉያን ስደተኞች ቁጥር ወደ ሁለት ሺሕ ይደርሳል።የተባበሩት መንግሥታት የሊቢያዉን አይነት የዉጪ ጦር ዘመቻን ሶሪያ ላይ እንዳይፈቅድ አጥብቃ የምትሟገተዉ የሩሲያ ተመራጭ ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈዉ የካቲት ሊቢያ ዉስጥ አሁን ሥለሚፈፀመዉ ግፍ ለምንድነዉ የማይነገረዉ ብለዉ ጠይቀዉ ነበር።

አምንስቲ ኢንተርናሽናል ትንሽ መነጋሩ አልቀረም።ከዚሕ ባለፍ የተናገረ፣ የተነገረዉንም-ያሰማ፥ ለመስማት የፈለገም የለም።

የሃያ አመቱ ሶማሊያዊ ወጣት ዓሊ ዑመር እንደ ብዙ ሐገር ብዙ ብጤዎቹ ወደ አዉሮጳ ለመሻገር አልሞ ደቡባዊ ሊቢያ የገባዉ ቃዛፊ በተደገደሉ፣የገዳይ አስገዳዮች የድል ጮቤ ባሳረገ በሰወስተኛ ወሩ ነበር።ሊቢያን ከሱዳንና ከቻድ ጋር ከሚያዋስነዉ ኩፍራ ግዛት ሲደርስ እሱንና ብጤዎቹን አስርገዉ የሚያስገቡ የሁለት ጎሳ ታጣቂዎች ዉጊያ ገጥመዉ ጠበቁት።

አካባቢዉ የኮንትሮባንድ፤ ሸቀጦች፤ የጦር መሳሪያ፣ አደንዛዥ እፅና ስደተኞችን ካንዱ ድንበር ወደ ሌላዉ የሚያሻግሩት የዛዉያና የቱቡዉ ጎሳ ተወላጆች ከቃዛፊ መገደል በሕዋላ እስካፍንጫቸዉ ታጥቀዋል።ነባር ጠባቸዉን ባዲሱ ትጥቅ ያጠናከሩት ሐይላት ባለፈዉ የካቲት ወር ባደረጉት ግጭት ብቻ ከአንድ መቶ በላይ ሰዉ ተገድሏል።


ዓሊና ብጤዎቹ በዉጊያዉ መሐል አልፈዉ ካንዲት ትንሽ መንደር ሲደርሱ መንደሪቱን የሚቆጣጠሩት ቃዛፊን ያስወገዱት የቀድሞዉ አማፂያን አሰሯቸዉ።አራት መቶ የሚሆኑት ስደተኞች ካተሩ ሰወስት ወር አፋቸዉ።ከሐገሬ የወጣሁት ጦርነትን ሸሽቼ ነበር---እዚሕም----አለ ዓሊ።

የዛሬ አመት ይኸኔ ሙስጠፋ አብዱል ጀሊልና ተባባሪዎቻቸዉ ቃዛፊን የሚያስወግዱበትን ብልሐት ያወጠነጠኑባት ቤንጋዚ ዛሬ የወደፊቷ ራስ ገዝ መስተዳድር ዋና ከተማ እንድትሆን ተወስኗል። የቤንጋዚና ያካባቢዉ ጎሳ መሪዎች፥ የሚሊሻ ተጠሪዎች ባለፈዉ የካቲት ማብቂያ ቤንጋዚ ላይ ባደረጉት ጉባኤቸዉ የቅኝ ገዢዎቻቸዉን መስመር ተከትለዉ የሲሬይናይካ ራስ-ገዝ መስተዳድርን ለመመስረት ወስነዋል።

ሴራናይካ ከማዕከላዊ መንግሥት ካፈነገጠች ከቃዛፊ ጨቋኝ፥ ገዳይ፥ ግፈኛ አገዛዝ ነፃ ወጣች የተባለችዉ ሊቢያ እንደ ጥንቱ ትሪፖሊ ላይ የትሪፖሊታኒያን ጁፍራ ላይ የፌዛንን ራስ ገዝ ወይም ነፃ መንግሥት ማቆሙ አይደዳትም።ሰወስት መንግሥት።ያም ሆኖ የቃዛፊ መገደል ለሊቢያዎች ብዙ መጥቀሙን እንጂ ጉዳቱን ሊቢያ ዉስጥ ባደባባይ መናገር ቢያንስ ላሁኑ «ሐራም» ነዉ።

ማሊዎች ግን አለመናገር አይችሉም።በቃዛፊ መንግሥት ድጋፍ ይሰሩ የነበሩ መንገዶች፥ ሆቴሎች፥ የነዳጅ ማከፋፈያ ተቋማት በጅምር ቀርተዋል።ሊቢያ ዉስጥ ሰርተዉ ዘመድ፥ ወዳጆቻቸዉን የሚደጉሙት የማሊ ተወላጆች ዛሬ ሥራ አጥናቸዉ።የሊቢያ መንግሥት ጦር ባልደረቦች የነበሩት የቱዋሬግ ጎሳ አባላት ሰሜናዊ ማሊ ዉስጥ የከፈቱት ዉጊያ ደግሞ የትንሺቱን ሠላማዊት ሐገር ሰላማዊ ሕዝብ አመሰቃቅሎታል።

የባማኮ የሰላም ጥናት ተቋም ባልደረባ ሞዲባ ጎይታ የሊቢያ ጦርነት መመዝ ለማሊ እንደሚተርፍ ገና ያኔ ተናግሬለሁ ይይላሉ።

«ከሊቢያ የተመለሱት ተዋጊዎች ሚሳዬሎች ብቻ ከሰወስት ሺሕ በላይ ታጥቀዋል።ገና ያኔ ተናግሬ ነበር።ከሊቢያ መንግሥት ጦር የሚበተኑት ወታደሮች ወደዚሕ ሲመጡ ትጥቃቸዉን አስፈትቶ መሳሪያዉ ወደ ሊቢያ መመለስ አለበት ብዬ ነበር።ይሕ አለም አቀፍ መብት ነዉ።ገቢራዊ ግን አልሆነም።»

የቀድሞዉ የሊቢያ መንግሥት ጦር ባልደረቦች የሚመሩት የቱዋሬግ አማፂ ቡድንና በማሊ ጦር መካካል እስካለፈዉ ወር ድረስ በተደረገዉ ዉጊያ በአስርሺ የሚቆጠር ሠላማዊ ሰዉ ተገድሏል።ከሁለት መቶ ሺሕ የሚበልጥ ተፈናቅሏል።

ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ከነ-ሥርዓታቸዉ ያጠፋዉ የአየር፥ የባሕር ድብደባ የተጀበረበት አንደኛ አመቱን ባለፈዉ ሳምንት ሲደፍን፥ በቱዋሬጎቹ ዉጊያ የተሸነፈዉ የማሊ ጦር መኮንኖች ፕሬዝዳት አማዱ ቱማኒ ቱሬ መንግሥትን ከስልጣን አስወገዱ።እና የሊቢያን ሕዝብ ከጥቃት ያድናል በተባለዉ ድብደባ መዘዝ ማሊም ተመሰቃቀለች።የሊቢያዉ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መጥፎ አስተምሕሮት ለሶሪያ እልቂት ፍጅት መባባስ፥ ለፀጥታዉ ጥ’በቃ ምክር ቤት አባላት መከፋፈል ትልቅ ምክንያትም ሆነ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

French President Nicolas Sarkozy, right, gestures towards Libyan Transitional National Council chairman Mustafa Abdel Jalil, center, and Libyan Transitional National Council Prime Minister Mahmoud Jibri during the final press conference at the Elysee Palace in Paris, Thursday, Sept.1, 2011. World leaders and top international envoys started talks Thursday with Libya's rebel government about how to keep the country together and build a new democracy, after months of civil war and decades of dictatorship under Moammar Gadhafi. (AP Photo/Michel Euler)
ድል አድራጊዎችምስል AP
Libyan military perform at a lavish private dance spectacle thrown for African heads of state by Libyan leader Moammar Gadhafi, and celebrating the 40th anniversary of the 1969 military coup that brought him to power, at a military airfield outside Tripoli, Libya, in the early hours of Tuesday, Sept. 1, 2009. The African heads of state were in Libya attending the special session of the African Union Assembly on the consideration and resolution of conflicts in Africa, and attended the exclusive night-time event featuring thousands of dancers, singers, horses, tanks, acrobats and the Libyan military. (AP Photo/Ben Curtis)
ዉድቀቱምስል AP

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ




















ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ