1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያው ዘግናኝ የሽብር ተግባርና ግብፅ

ረቡዕ፣ የካቲት 11 2007

በሊቢያ የግብጽ ተወላጆች የሆኑ 21 ክርስቲያኖች በአሠቃቂ ሁኔታ ከተገደሉና የግብፅ ፕሬዚዳንትም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ርምጃ እንዲወስድ ካሳሰቡ ወዲህ ፣ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት ጉዳዩ ን አንስቶ መወያያቱ ተገለጠ። ግብፅ በሀገር

https://p.dw.com/p/1Ee6j
ምስል picture-alliance/dpa/Elfiqi

ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ፣ ከአሸባሪነት ጋር ተጋፍጣለች። ግብፅ ውስጥ፣ ከሞላ ጎደል በየዕለቱ የፈንጂ አደጋ በመጣል የሰው ሕይወት ለማጥፋት ይሞከራል። ጦር ሠራዊቱ በአክራሪ ሙስሊሞች ላይ ክትትሉንም ሆነ ዘመቻውን አጠናክሯል። በሌላም በኩል በግብጽ ጎረቤት በሊቢያ የሚካሄደው የርስ-በርስ ውጊያ የአካባቢውን የጸጥታ ይዞታ ይበልጥ አወሳስቦታል።

በላዕላይ ግብፅ ሚንያ በተሰኘው ጠ/ግዛት፣ አውራ፣ በተሰኘችው መንደር በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀሳውስት የሐዘን መዝሙር ይዘምራሉ፤ የግብጽ ቴሌቭዥን ከትናንት በስቲያ ሰኞ አንስቶ በሊቢያ በአሠቃቂ ሁኔታ የተገደሉትን 21 የቅብጥ(ኮፕት) ክርስቲያኖች ሁኔታ አስመልክቶ ምስላቸውን እያቀረበ፣ በሀገሪቱ በመላ የሚታየውን የሐዘን መታሰቢያ አዘውትሮ ያሳያል። ከተገደሉት መካከል 13 ቱ የተጠቀሰችው መንደር ሰበካ አባላት ነበሩ። የግብፅ ክርስቲያንና ሙስሊም ዜጎች በአንድነት ተመሳሳይ ቃልም ሆነ ዐረፍተ ነገር ነው የሚናገሩት።

«ግብፅ ውስጥ ፤ በአሸባሪነት ላይ አንድ ጠንካራ ውስጣዊ ግንባር መፈጠሩ ጠቃሚና አስፈላጊም ነው። ሕዝቡ በአሸባሪነት ላይ እንዲነሣሣ፣ የተጠናከረ ንቃተ ሕሊና ያሻል።»

ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች በግብጻዊ ዜግነታቸው አንድ ላይ መቆም እንዳለባቸውም ነው ከየአቅጣጫው መልእክቶች የሚተላለፉት። «የግብፅ ሕዝብ አንድ ችግር ተደቅኖበታል ፣ አሸባሪነት የሚባል! ይኸው አሸባሪነት ደግሞ ሃይማኖትን የማያውቅ ነው» የሚል ቃል ሲሰነዘር ከውጭም ከውስጥም የሚዘነዘረውን ሽብር ለማመላከት ነው። ግብፅ ውስጥ በየዕለቱ ነው አሸባሪ ርምጃ የሚቃጣው ለምሳሌ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ አደጋ ይጣላል ወይም መጨረሻ ደቂቃ ላይ ፣ የማክሸፍ ርምጃ ይወሰዳል። ቀድሞ የወታደራዊ መረጃ ክፍል ጀኔራል የነበሩ አሁን በካይሮ የ «ጉምሁሪያ» የስልታዊ ጥናት ማዕከል ባልደረባ ሳሜህ ሰይፍ ኧል ያዛል ፤ የግብፅ የጸጥታ ጥበቃ ኃይሎች አስመሥጋኝ ተግባራትን በማከናወን ላይ ናቸው። ነገር ግን ፣ ችግሩ ን ያጠናከረው የተለየ ኃይል አለ በማለት እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል።

Französischer Verteidigungsminister Le Drian mit Koptischem Papst Tawadros II
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Nabil

«ዋናው ነጥብ ፤ አካራሪዎቹ ታጣቂዎች ከውጭ ሰፊ የገንዘብ ርዳታ የሚደረግላቸው መሆኑ ነው። ርዳታው ከአንዳንድ መንግሥታት እንዲሁም አሸባሪ ድርጅቶች ነው የሚገኘው። የሚቀርበው ገንዘብ ብዙ ነው ፤ ሥራም ላይ ይውላል።»

በግብፅ ፣ አሁን የሚታየው ሂደት ከሙሐመድ ሙርሲ አገዛዝ መወገድ በኋላ የቀጠለ ነው። ከህዝቡ አመጽና ሆስኒ ሙባረክም ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ፣ በምርጫ ሙርሲ ለሥልጣን በቅተው ነበር። ሆኖም የሙስሊም ወንድማማችነት ማሕበር የተሰኘውን የፖለቲካ ድርጅት መርኃ ግብር ብቻ የሙጥኝ በማለታቸውበዛ ያለው የግብፅ ሕዝብ ተነሳባቸው ፤ ጦር ኃይሉም በመጨረሻ ከሥልጣን አስወገዳቸው። የሙስሊም ወንድማማችነት ማሕበር ከፊል አባላትና ሌሎች ጽንፈኛ ሙስሊሞች ናቸው የሕቡዕ ትግል በመጀመር ሙርሲን ከሥልጣን ባስወገዷቸው ላይ ለመበቀል ፣ ግብጽ ውስጥ የሽብር ተግባር የሚያከናውኑት። አክራሪ ሙስሊሞቹ ተጠናክረው የሚገኙት ማዕከላዊው የካይሮ መንግሥት በአመዛኙ ችላ ብሎት በቆየው በሲና ደሴት አከል ምድር ነው። ራሱን በሶሪያና በኢራቅ የሚገኘው እስላማዊ መንግሥት የተሰኘው የጽንፈኞች ድርጅት ተቀጥላ አድርጎ የሚመለከተው የግብፅ አካራሪ ሙስሊሞች ድርጅት፤ ባለፈው ጥር፤ በግብፅ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የተቀነባበረ ጥቃትና ግድያ መፈጸሙ የሚታወስ ነው። አንዷ የጥቃት ሰለባ ኤል አሪሽ ናት።የቀድሞው ጀኔራል ሳሜህ ሰይፍ ኤል ዛዛል--

«የግብፅ ጦር ሠራዊት በራሱ ምድር በሲና ካቆጠቆጡ አሸባሪዎች ጋር ነው የተጋፈጠው። እርግጥ ግብጻውያን ብቻ ሳይሆኑ፤ ከሶሪያ ወደ ሲና የተሻገሩ አሸባሪዎችም ተቀላቅለዋል። በይበልጥ የተደራጁ በዘመናዊ ጦር መሳሪያም የታጠቁ ናቸው። ስለሆነም በኤል አሪሽ ያደረሱት ጉዳት ከባድ እንደነበረ መገንዘብ አላዳገተም።»

21 ግብጻውያን ክርስቲያኖች ከተገደሉ ወዲህ ፣ ከ 1, 100 ኪሎሜትር በላይ ከሊቢያ ጋር በሚያዋስነውና መቆጣጠር በሚያዳግተው ምዕራባዊ ድንበር የተቃጣው አደጋ ማሥጋቱ አልቀረም። ያዛል ግን መቆጣጠር አያዳግተንም ባይ ናቸው።

Französischer Verteidigungsminister Le Drian mit Ägyptens Präsident al Sisi
ምስል AFP/Getty Images/K. Desouki

«ወሰኑን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደማያቅተን ርግጠኛ ነኝ። ጦር ሠራዊታችን፤ ወሰን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የሥነ ቴክኒክ ውጤቶችንና ስልቶችን ከአውሮፓና ከእስያ አግንቷል። በሊቢያ ወሰን በኩል ራስ ምታት የሚሆን ችግር ወደፊት መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ከሌሎች አካባቢዎች ይልቅ በጣም የሚያሳስበውም በሊቢያ በኩል ያለው ነው። »

የግብፅ ጦር ኃይል ፤ በአየር ኃይል ከመደብደብ ባሻገር ፣በሊቢያ ወሰን በኩል እግረኛ ጦር ያዘምታል ተብሎ አይታሰብም ፣ አለበለዚያ በሁለት አቅጣጫ የጦር ግንባር መክፈት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ከአሸባሪነት ጋር መጋፈጥ ከባድ ነው የሚሆንበት።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ