1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የለዉጥ እንቅስቃሴ በስዋዚላንድ

ዓርብ፣ ሐምሌ 15 1997

በስዋዚላንድ የንጉስ አገዛዙ የዘረጋዉን አምባገነናዊ ስርዓት ወደዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመለወጥ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የለዉጥ እንቅስቃሴዉ በብዛት ከአገር ዉጪ በስደት በሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚመራ ሲሆን አገር ዉስጥም አልፎ አልፎ የተቃዉሞ እርምጃ በህዝቡ ሲወሰድ ይታያል።

https://p.dw.com/p/E0jj

እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝቡ በቀር ድጋፍ የሚያደርግላቸዉ አካል እንደሌለ ይነገራል። በሌላ ወገን ደግሞ ስራ አጡም ሆነ በኤችአይቪ የተጠቃዉ የአገሪቱ ህዝብ ቁጥሩ እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ንጉሥ የዉጪ እርዳታ ሳያስፈልገኝ ችግሩን አስወግዳለሁ ይላሉ። በዚህ መሃል ግን በአገሪቱ ዉጥረት መንገሱ ነዉ የሚሰማዉ።
ስዋዚላንድ እንደ ሩዋንዳና እንደቡሩንዲ ወይም እንደሴራሊዮን እንድት በጠበጥ አንፈልግም ባይ ናቸዉ በሲዋዚላንድ ዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ የተባበሩት የዲሞክራሲ ንቅናቄ መስራች ጋብርኤል ማክሁሜ።
የስዋዚላንድ ህዝብ አንዱ በሌላዉ ላይ በቁጣ ክንዱን አያነሳም! ያ ከጥያቄ ዉጪ ነዉ። ቀዝቃዛዉ ጦርነት አብቅቷል። እኛ የምንፈልገዉ ዓለማቀፉ ህብረተሰብ በሲዋዚላንድ የፖለቲካ ለዉጥ እንዲመጣ ጫና እንዲያደርግ ብቻ ነዉ ሲሉም ለአይፒኤስ የዜና ወኪል ገልፀዋል።
ምንም እንኳን በደቡብ አፍሪካ በስደት የሚገኙት ማክሁሜ ህዝቡ ለግጭት መነሳሳቱን ቢያጣጥሉም ወደዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የሚደረገዉ ጥረት ለዉጥ ባለማሳየቱ ተስፋ የቆረጡ ዜጎች ያሰቡትን ለማግኘት እርምጃ እንዳይወስዱ ስጋት አላቸዉ።
መቀመጫዉን ብሩሴልስ ያደረገዉ ዓለም ዓቀፍ የግጭት አጥኚ ቡድንም በበኩሉ በስዋዚላንድ ያለዉ መፋጠጥ ወደሌላ ደረጃ እንዳይ ደርስ እርምጃ መወሰድ አለበት በማለት አሳስቧል።
ባቀረበዉ ዘገባም በአገሪቱ የሚታየዉን አምባገነናዊ አስተዳደር የሚቃወሙት ቡድኖች ባለፉት ቅርብ ዓመታት የስራ ማቆም አድማ፤ የሙያ ማህበራት፤ ተማሪዎች፤ የሃይማኖት ድርጅቶችና የወጣቶች ንቅናቄዎችን በማስተባበር የተቃዉሞ ሰልፍ እንዲሁም የመንግስት ህንፃዎችን በቦምብ እስከማጋየት የደረሰ እርምጃ መዉሰዳቸዉን ለአብነት ጠቅሷል።
በተጨማሪም ዘገባዉ በደቡብ አፍሪካ የግጭት አጥኚ ቡድኑ ዳይሬክተር የሆኑትን ፒተር ካግዋንጂን ጠቅሶ እንዳሰፈረዉ የአፍሪካ ተቋማት፤ የአዉሮፓዉ ህብረትና እንዲሁም እንደ ደቡብ አፍሪካና ዩናይትድ ስቴትስ ያሉት ወሳኝ አገራት በአምባገነኑ አስተዳደር አዝግሞ ይመጣል የሚባለዉን ለዉጥ አይቀበሉትም።
እሳቸዉ እንደሚሉት በስዋዚላንድ አምባገነኑን ህገ መንግስት ለመለወጥ እድሜዉ በረዘመ ቁጥር የአገሪቱ ደህነትና መረጋጋት አደጋ ላይ ይወድቃል።
አምባገነናዊዉን ስርዓት ከሚደግፈዉ ሁኔታ በቀር በመጠኑም ቢሆን አገሪቱ ስትታይ የተረጋጋች በመምሰሏ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ተቆርቋሪዎችም ዓለም ዓቀፉን ህብረተሰብ በስዋዚላንድ ጉዳይ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ለማሳመን ችግር ገጥሟቸዋል።
በደቡብ አፍርካ በጆሃንስ በርግ የምርጫ ተቋም ተመራማሪ ክላዉዲ ካቤምባ እንደሚሉም ስለስዋዚላንድ ሊሰማ የሚችለዉ ዜና ቢኖር የአገሪቱ ንጉስ ይህን ገነቡ የሚል ብቻ ነዉ።
በደቡብ አፍሪካና በሞዛምቢክ መካከል የምትገኘዉ የአፍሪካ የመረሻዋ በንጉሳዊ አምባገነን ስርዓት ስር የምትገኘዉ ስዋዚላንድ ከቅኝ ገዢዋ ከብሪታንያ ነፃ የወጣችዉ በ1960ዓ.ም. ነዉ።
በ1965 ዓ.ም. ንጉስ ሶቡዛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ፓለቲካ ፓርቲዎችንና የአገሪቱን ህገ መንግስት አገዱ።
ሶቡዛ በልጃቸዉ በማስዋቲ ሶስተኛ ተተኩ። የ37 ዓመቱ ልዑል የአገሪቱን የዜና አዉታሮች ርዕሰ ዜና የሚያጣብቡት ለሚስቶቻቸዉ በሚገዟቸዉ የቀበጡ መኪናዎች ነዉ።
ዘመናዊና የቅንጦት መኪናዎች እንደሚወዱ የሚነገርላቸዉ እኝህ ሰዉ እስከዛሬ 12ጊዜ አግብተዋል።
የእሳቸዉ የተቀኛጣ የኑሮ ሁኔታ 40 ከመቶ ከደረሰዉ ከስዋዚላንድ የስራ አጥ ቁጥር ጋር ሲተያይ ግራ ነዉ።
አንድ ሚሊየን ከሚሆነዉ የአገሪቱ ህዝብ 70 በመቶ የሚሆነዉ የሚኖረዉ በቀን ከአንድ ዶላር በታች በሆነ ገቢ መሆኑ ይነገራል።
ከተባበሩት መንግስታት የኤች አይቪ መርሃ ግብር የተገኘ መረጃም እንደሚያሳየዉ የበሽታዉ ስርጭት 40 በመቶ ደርሷል።
የስዋዚላንድን አምባገነናዊ አስተዳደር የሚቃወሙ አካላት ድጋፍ ይሰጣሉ ይባሉ የነበሩት የዓለም ዓቀፍ ህብረተሰብ ቡድኖች ትግላቸዉን በገንዘብም ሆነ በማቴሪያል መደገፍ እንዳቆሙ ይናገራሉ።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኘዉ የስዋዚላንድ የህብረት ቅንጅት ዋና ፀኃፊ ቦንጋኒ ማሱኩ እነሱ ድጋፍ የሚሰጡት ለሲቪክ ማህበራት ነዉ እነዚያ ደግሞ በስዋዚላንድ የታሰበዉን ለዉጥ የሚያመጣ አቅም የላቸዉም ባይ ናቸዉ።
የሚታገሉት በጦር ኃይል፤ በፓለቲካና በምጣኔ ሃብት ከደረጀ አካል ጋር በመሆኑም ካለ ዓለም ዓቀፍ ድጋፍ ቅስቀሳቸዉ ብቻ ለዉጥ ለማምጣት አላስቻለንም ሲሉም ችግራቸዉን ገልፀዋል።
ማሱኩ የዚምባቡዌዉን ሮበርት ሙጋቤን እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዉ የስዋዚላንዱን ማስዋቲን በመላዉ አዉሮፓ እንዲዞሩ መፈቀዱ አስገርሟቸዋል።
ይህም አዉሮፓ ሁለት አይነት አቋም ይዞ እየተጫወተ መሆኑን ያሳያል ሲሉም ትችታቸዉን ሰንዝረዋል።