1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የለንደን ኦሎምፒክና የኢትዮጵያ ተሥፋ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 17 2004

30ኛው የዘመናችን የኦሎምፒክ ጨዋታ በይፋ አጠራሩ «30ኛው ኦሊምፒያድ» በፊታችን አርብ ለንደን ላይ ይከፈታል።

https://p.dw.com/p/15ddY
ምስል picture-alliance/ dpa

30ኛው የዘመናችን የኦሎምፒክ ጨዋታ በይፋ አጠራሩ «30ኛው ኦሊምፒያድ» በፊታችን አርብ ለንደን ላይ ይከፈታል። የብሪታኒያ ርዕሰ-ከተማ የኦሎምፒኩን ጨዋታ የማስተናገድ ዕድል ሲገጥማት ከጎርጎሮሳውያኑ 1908 እና 1948 ዓመተ-ምሕረት በኋላ ለሶሥተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ለንደን ለመሰተንግዶው የተመረጠችው ዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በ 2005 ሢንጋፑር ላይ ባካሄደው 117 ስብሰባ በተፎካካሪነት የቀረቡትን ከተሞች ፓሪስን፣ ማድሪድን፣ ኒውዮርክንና ሞስኮን በማሸነፍ ነበር። ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ከስፍራው እንደዘገበችው ለንደንና ነዋሪዎቿ አሁን ዓለምን ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን አከናውነው በጉጉት/በኩራት እየጠበቁ ነው።                                        

ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ለለንደኑ ኦሎምፒክ የተደረገው አጠቃላይ ግንቢያና ዝግጅት 14,5 ቢሊዮን ኤውሮ ሲፈጅ እስከፊታችን ነሐሴ 6 ቀን የሚዘልቀው ውድድሩ ከባድ የጸጥታ ጥበቃ በሰፈነበት ሁኔታ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። በለንደኑ ኦሎምፒክ 10,490 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶችንም 302 የወርቅ ሜዳሊያዎች ተዘጋጅተው እየጠበቁ ነው።                                                                               

ካለፈው የቤይጂንግ ኦሎምፒክ ከዋክብት መካከል ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል የጃማይካው የአጭር ርቀት መንኮራኩር ዩሤይን ቦልት፤ የአሜሪካው ሃያል ዋናተኛ ማይክል ፌልፕስ፤ እንዲሁም በተለይ ከቀነኒሣ በቀለ እስከ ቪቪያን ቼሩዮት ሃያላኑን የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች የመሳሰሉት ዘንድሮም ተሳታፊዎች ናቸው። የቴኒሱ ስፖርት ከዋክብት ሮጀር ፌደረር፣ ኖቫክ ጆኮቪችና ሤሬና ዊሊያምስም ለጨዋታው ድምቀት እንደሚሰጡት ጨርሶ አያጠራጥርም።

ኢትዮጵያ ከ 1960 የሮማ ኦሎምፒክ ወዲህ አበበ ቢቂላን፣ ማሞ ወልዴን፣ ምሩጽ ይፍጠርን፤ እንዲሁም ሃይሌ ገብረ ስላሴን፣ ቀነኒሣ በቀለን፣ ደራርቱ ቱሉን፣ ፋጡማ ሮባን፣ጥሩነሽ ዲባባን፣ ወይም መሠረት ደፋርን የመሳሰሉ ታላላቅ አትሌቶችን ስታፈራ በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ ዓለም ያወቀና ያደነቃት ሆና ነው የኖረችው። እንግዲህ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ ታላቅ ውጤት ስታስመዘግብ ቆይታለች። ዘንድሮስ?

Flash-Galerie Usain Bolt Leichtatlethik-WM 2011 Daegu Südkorea
ምስል dapd

ጊዜው እርግጥ በኢትዮጵያ አትሌቲክ መድረክ ላይ ሃይሌን የመሰለ ታሪካዊ አትሌት ስንብት ያደረገበት፤ በአካል ጉዳት የተነሣ የሜዳሊያ ዋስትና የነበሩ አትሌቶቻችን በሚገባ አገግመው ወደ ቀድሞ ጥንካሬያቸው መመለሳቸው ያልለየበትና ተተኪ ማግኘታቸውም እንዲሁ ገና እርግጠኛ ያልሆነበት ነው። ለምሳሌ ያህል ቀነኒሣ በቀለ በቅርቡ በፓሪስ የዳያመንድ ሊግ ውድድር አኳያ ለረጅም ጊዜ ስላጀበው የአካል ጉዳትና ይሄው ስላሳደረበት ተጽዕኖም ተናግሮ ነበር።

Sport Leichtathletik WM Berlin Deutschland 5000m
ምስል AP

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓለምአቀፍ ደረጃ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ የጀመሩ ብዙ ወጣት አትሌቶችን ስታፈራ አዲሱ ኮከብ፤ አዲሷ ኮከብ ወይም አዳዲሱ ከዋክብት ለንደን ላይ ሊወለዱ የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም።

እንግዲህ ቀድሞ አንዱ ሌላውን እየተካና እያስናቀ እንደመጣው ሁሉ አሁንም ተሥፋ አለ ማለት ነው። 33 አትሌቶችን ያቀፈው የኦሎምፒክ ቡድን ወደ ለንደን የሚያመራውም ዋና አሰልጣኙ ዶር/ይልማ በርታ ዛሬ እንደገለጹልን ግሩም ዝግጅቱን አጠናቆ፣ በግሩም የጤንነት ሁኔታና ትልቅ ተስፋ ጭምር ነው። ዶር/ይልማ በርታ ይሁንና ምን ውጤት እንደሚገኝ ቀድሞ መተንበዩን አልመረጡም።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በለንደኑ ኦሎምፒክ የቤይጂንጉን ከዋክብት ቀነኒሣንና ጥሩነሽ ዲባባን የሚተኩ አትሌቶች ማግኘቷን ብዙዎች ናቸው የሚጠራጠሩት። ይህን ግምት ከሚጋሩት መካከል ደግሞ የኢትዮጵያው የቆየ የስፖርት ጋዜጠኛ ሰለሞን በቀለም አንዱ ነው። የዘንድሮው ከበድ ሳይል አይቀርም ባይ ነው።

ጋዜጠኛ ሰለሞን በቀለ እርግጥ ዘንድሮ በኦሎምፒኩ ጨዋታ ከሚሳተፉት ወጣት አትሌቶች መካከል አንጋፎቹን የሚተካ ሊፈጠር እንደሚችልም ተሥፋውን ሲገልጽ ብዙም ዕድል የማይታየው በተለይ በማራቶን ሩጫ ረገድ ነው። ኢትዮጵያ በወቅቱ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ከመካከለኛ ጥንካሬ ያለፈ የማራቶን ሯጭ የላትም። ለማንኛውም ለቡድኑ ስኬት እንመኛለን።  

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ