1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የለንደኑ ፀረ ሙስና ጉባኤ እና የማጉፉሊ እርምጃ

ሐሙስ፣ ግንቦት 4 2008

ፖለቲከኞችን ጨምሮ የአለማችን ታዋቂ ሰዎች በሃገራቸው ግብር ላለመክፈል ገንዘባቸውን እንዴት ወደ ውጭ እንደሚያሸሹ የፓናማ ሰነዶች ካጋለጡ ከአንድ ወር በኋላ ለንደን ውስጥ ዛሬ ፀረ ሙስና ጉባኤ ተካሂዷል ።

https://p.dw.com/p/1ImVR
Großbritannien London Cameron Anti-Korruptions-Konferenz
ምስል Reuters/D. Kitwood/Pool

[No title]

የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን የጠሩት የመንግሥታት መሪዎች የሲቪል ማህበራት እና የባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች የተካፈሉበት ይኸው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሙስናን መዋጋት የሚያስችል ጠንካራ ውሳኔ ያስልፋል ተብሎ ይጠበቃል ። ከአለማችን በሙስና ሰበብ ብዙ ኪሳራ የምደርሳባት ክፍለ አለም አፍሪቃ ናት ። አፍሪቃ በሙስና እና በሌሎች የፋይናንስ ወንጀሎች በየአመቱ 50 ቢሊዮን ዶላር ታጣላች ። ሙስና የአፍሪቃ መለያ እስከመሆን ደርሷል ። የታንዛንያው ፕሬዝዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ግን በሃገራቸው ይህን ስር የሰደደ ልምድ ለማስቀረት ተነስተዋል ። የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ቡልዶዘር የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቷቸዋል ።ሙስናን ለመዋጋት የሚወስዱት እርምጃ በሃገራቸውም ሆነ ከሃገራቸው ውጭ ክብር እና ዝናን አትርፎላቸዋል ። ማጉፉሊ በለንደኑ ፀረ/ ሙስና ጉባኤ ጉባኤ ከተጋበዙት መሪዎች አንዱ ናቸው ። ምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ታንዛንያ በአፍሪቃ የከፋ ሙስና ይካሄድባቸዋል ከሚባሉ 20 የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ አንዷ ናት ። ማጉፉሊ በዚህ አመት በህዳር ወር ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ሙስናን መዋጋት ቅድሚያ ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች አንዱ ነው ። ፕሬዝዳንቱ በተለያዩ ጊዜያት በሙስና የተከሰሱ የመንግሥት ባለ,ሥልጣናትን ከስራ ያገዱ ሲሆን ለህዝባዊ በአላት ገንዘብ ወጪ መደረጉ ተሰርዞ ለልማት ፕሮጀክቶች እንዲውልም አድርገዋል ። ዶቼቬለ ከአሩሻ ያነጋገራቸው ታንዛንያውያን ፈተናዎች ቢኖሩትም ፕሬዝዳንቱ የያዙት መንገድ ትክክለኛ ነው ይላሉ ።
«ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ሙስናን በሚዋጉበት መንገድ ምክንያት ከባድ ፈተናዎች ተጋርጠውባቸዋል ።ጥሩ ስራ እየሰሩ ነው ። ሙሰኞች ግን ስራቸውን አያደንቁም ። በእውነት ከልባቸው እየሞከሩ ነው ።ለዚህም ነው ጉቦኞች የሚቃወሟቸው ።እኛ እንደ ዜጎች ሙስናን ለማሸነፍና ሙሰኛ ባለሥልጣናትን ለመዋጋት ከፕሬዝዳንታችን ጋር መስራት አለብን ።»
«በሙስና ላይ የሚከፈት ጦርነት ትልቅ ጦርነት ነው ። ምክንያቱም ከህዝቡ አብዛኛውን ክፍል የሚያቅፍ ነውና ።ስለዚህ ትግሉን መቀጠል አለባቸው ።በዚህ ትግል ውስጥ ትልቅ ወይም ትንሽ የሚባል ሰው የለም ።»
«በርካታ መሰናክሎች ገጥመዋቸዋል ።ሰዎች ስራዎችን በፈለጉት መንገድ ማካሄድ ነው የለመዱት ።ፕሬዝዳንቱ ግን በእውነት ሙስናን ለመዋጋት በጣም እየጣሩ ነው ። በሙስና የተሳሰሩ መረቦችን እየበጣጠሱ ነው ። ጸሎታችን ፕሬዝዳንታችን በዚሁ ተግባራቸው እንዲገፉ እና እንደ እኛ ያሉ ደሃ እና ደካሞችን እንዲረዱ ነው ።»
አስተያየት ሰጭዎች እንዳሉት ሙስናን መዋጋት ብዙ ተግዳሮቶች አሉት ። ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተፅእኖ ያላቸው መሪዎች እና ሃብታሞች በሙስናው መረብ ውስጥ አሉ ።በአንዳንዶች አባባል የፀረ ሙስና መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት ፣ ፖሊስ እና የፍትህ አካላት ራሳቸው ሙሰኞ መሆናቸው ትግሉን አስቸጋሪ ያደርገዋል ።በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ሙስናን ከሃገራቸው ለማጥፋት ይዝታሉ ። ሙሰኞች የሚቀጡባቸውን ህጎች ያረቃሉ ።የፀረ ሙስና ባለስልጣናትንም ይሰይማሉ ። ይሁንና በተጨባጭ የሚመጣ ለውጥ ግን አይኖርም ።የአገራትን የሙስና ደረጃ የሚያጠናው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በ2014 አም ባወጣው ዘገባ እንዳስታወቀው 22 በመቶ የሚሆኑ አፍሪቃውያን በጎርጎሮሳዊው 2013 አም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ጉቦ መስጠታቸውን ተናግረዋል ። ሩዋንዳዊው ተመራማሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ዘጋቢ ካዩምባ ክሪስቶፍ ማጉፉሊ ከሌሎች አቻዎቻቸው በተለየ ሙስናን መታገሉ የተሳካላቸው ያሉትን በተግባር በመተርጎማቸው ነው ይላሉ ።
« ቃላቶቹ ወዲያውኑ ተግባራዊ አልሆኑም ። ማጉፉሊ ያደረጉት ፣በአካባቢው የሚገኙ ፕሬዝዳንቶች ያላደረጉት ምንድነው ቃላቸውን ተግባራዊ ማድረጋቸው ነው ። ይኽውም በሙስና የተከሰሱትን ባለሥልጣናት ማገዳቸው እና የመንግሥት ወጪን መቀነሳቸው እንዲሁም ራሳቸው የመንግሥት ገንዘብ ተጠቃሚ አለመሆናቸው ነው ።»
በለንደኑ ፀረ ሙስና ጉባኤ ጉባኤ ላይ የተገኙት የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ባሰሙት ንግግር ወቅታዊ እና በጣም አሳሳቢ በሆነው በዚህ ጉዳይ ላይ ጉባኤ መካሄዱ ተገቢ መሆኑን አስረድተው በሙስና ላይ የሚካሄደው ትግል ኢንዲጠናከር ጠይቀዋል ።
« ሙስና ከዘመናችን ታላላቅ ጠላቶች አንዱ ነው ። ከእሴቶቻችን ጋር የማይሄድ ብዙዎች በድህነት እየማቀቁ ሃብት በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ስር እንዲውል የሚያደርግ ነው ። ይህን እኩይ ልምድ ለመዋጋት ትግላችንን ማጠናከር አለብን »

Nigeria Muhammadu Buhari Präsident Rede vor der UN Vollversammlung
ሙሃማዱ ቡሃሪምስል Getty Images/AFP/M. Ngan
Tansania Präsident John Magufuli
ማጉፉሊ በታንዛንያ የነፃነት በአል ምትክ በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ ሲሳተፉምስል Getty Images/AFP/D. Hayduk

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ