1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህዳሴዉ ግድብና የግብጽ ለዉይይት መዘጋጀት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 16 2006

በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሱዳን ድንበር አቅራቢያ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባዉ የኃይል ማመንጫ ግዙፍ ግድብ የአባይ ተፋሰስ ሃገራትን ብቻ ሳይሆን የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ፕሮጀክት ነዉ። ግድቡ ሲጠናቀቅ 6,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/1ChGR
Äthiopien Staudamm Nil 16.03.2014
ምስል Reuters

እስካሁን አንድ ሶስተኛዉ መገንባቱ የሚነርለት ግድብ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከአፍሪቃ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ ለሆነችዉ ሀገር ተፈላጊዉን ኮረንቲ ከማቅረብ አልፎ ለገቢ ምንጭነትም ትልቅ ሚና እንደሚኖረዉ ተስፋ አለ። ግብፅ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1929 እና 1959,ም የነበሩ የአባይ ዉሃ አጠቃቀምን የሚገድቡ ስምምነቶች በመመርኮዝ በዉሃዉ ላይ ታሪካዊ መብት እንዳላት በመግለፅ የግድቡን ግንባታ በጥርጣሬ ስትመለከት ቆይታለች። አልፎ ተርፎም የኃይል ርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ማስፈራራትን ያካተቱ መግለጫዎችም ተሰምተዉ ያዉቃሉ። የግብፅ ስጋት ግድቡ የሕልዉናዋ ድርና ማግ የሆነዉን የአባይ ዉሃን ፍሰት ይቀንሳል ወይ ያግዳል የሚል ነዉ። የቀደሙት ዉሎች ግብፅ ከአባይ ዉሃ ሁለት ሶስተኛዉን እንድትጠቀም፤ የዉሃዉን ፍሰት የሚያዉኩ በወንዙ ላይ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ካሉም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት የሚያጎናጽፏት ነበሩ። ከአባይ ዉሃ ምንም እንዳልተጠቀመች የምትገልጸዉ ኢትዮጵያ ዉሎቹ ጊዜ እንዳለፈባቸዉ በማመልከት ዉሃዉን የተፋሳሽ ሃገራትን መሠረታዊ ጥቅም በማይነካ መልኩ ለኤልክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ልታዉለዉ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ተግባር በማከናወን ላይ ትገኛለች። የዘጋርዲያን ዘገባ የጠቀሳቸዉ በአፍሪቃ ኅብረት የግብፅ ተጠሪ ሞሀመድ ጎኒም እንዲህ ያለዉ ግዙፍ ግድብ የዉሃዉ ፍሰት ሊቀንስ ስለሚችል ከታች ያሉ የተፋሰሱ ሃገራት ወደበረሃነት ሊለወጡ ይችላሉ፤ ጨዉ በአፈር ዉስጥ ይከማቻል፤ ግድቡም ምናልባትም ሊሰበር ይችላል ብለዋል ። እንዲህ ያለዉ የግብፅ ስጋት አዲሱ ፕሬዝደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ስልጣን ለመያዝ ባኮበኮቡበት ዋዜማ አንስቶ እየቀነሰ ከካይሮም መለሳለስ እየታየ መጥቷል። የግድቡን ተግባር አጠናክራ የቀጠለችዉ የኢትዮጵያ ግስጋሴ ወደማይሆን ፍጥጫ ቢገፉ ማንንም እንደማይጠቅም ያስተዋሉ የመሰሉት አልሲሲ ኢትዮጵያ አባይን የመጠቀም መብቷ እንዲከበርላት ከተደረገ እሷም ለታችኞቹ ተፋሳሽ ሃገራት ልታስብ እንደምትችል ሲናገሩ ተደምጧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኢብራሂም ሜህለብ አወዛጋቢ የሆነዉ የአባይ ግድብ ኢትዮጵያ የምትሻዉን ኤሌክትሪክ እያመነጨች ለግብፅ ግን የዉሃዉ ፍሰት እንደማይቀንስ ማረጋገጫ ብቻ እንድትሰጥ መንግስታቸዉ እንደሚሻ ነዉ ያመለከቱት። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነቢል ፋሚም እንዲሁ ሀገራቸዉ በዚህ ግድብ ግንባታ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋ ወደግጭት እንደማትገባ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። ሲካሄድ የነበረዉ የሶስትዮሽ ዉይይት ራሷን አግልላ የነበረችዉ ግብፅ በዉይይቱ ለመቀጠል መጠየቋ ተሰምቷል። ንግግሩ ዳግም ይጀመር መባሉ ምንን እንደሚያመላክት ዶቼ ቬለ የጠየቃቸዉ በካይሮዉ ሂሊያፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና የዩኒቨርሲቲዉ የቦርድ ፕሬዝደንት ዶክተር ኢብራሂም አቦሌሽ ማድረግ የሚቻለዉ የተሻለዉ ነገር ይሄዉ ነዉ ይላሉ፤

Bildergalerie Megacities Kairo
ምስል imago/OceanPhoto
Luftverschmutzung in Ägypten
ምስል picture-alliance/ dpa/dpaweb

«ልናደርግ የምንችለዉ የተሻለዉ ነገር ይኸዉ ብቻ ነዉ። እርግጥ ነዉ በዓለም የሚገኙ ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ማግኘት የሚችሉት ከድድብና ርምጃዎችና ጦርነቶች ይልቅ በዉይይትና በዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች ነዉ። ስለዚህ ሁለቱም ለመገናኘትና ለኢትዮጵያም ሆነ ለግብፅ የሚገኙትን ጥቅሞች ለማየት መወሰናቸዉ አስተዋይነት እንደሆነ ነዉ የምመለከተዉ። ፕሬዝደንታችንም ያሉት ይህንን ነዉ ግብፅም ብትሆን ለኢትዮጵያ ማሰብ አለባት። እናም ለወደፊቱ መልካም ነገር አመላካች ሆኖ ነዉ ያገኘሁት።»

እንደሚታወቀዉ ግብፅ ከአባይ ወንዝ ካላት ትስስር የተነሳ ከፍተኛ የይገባኛልና የባለቤትነት ስሜት ስታንጸባርቅ መቆየቷ ይታወሳል። ፕሬዝደንት አልሲሲ ጦር ኃይሉን በሚመሩበት ወቅት ከአንድ ዓመት በፊት ከስልጣን ያሰናበቷቸዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ፖለቲከኞች ግን ዶክተሩ እንደሚሉት ለሁለቱ ወገኖች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢዉም አደገኛ አካሄድን ለመከተል ሞክረዉ ነበር። አሁን የታየዉን የአቋም ለዉጥና መለሳለስ የመጣዉ ዶክተር አቦሌሽ እንደሚሉት ስልጣን ላይ የወጡት የቀድሞዉ የሀገሪቱ የጦር ኃይል መሪ ከፍጥጫ ይልቅ ብልሃት የታከለበት አቀራረብን በመምረጣቸዉ ነዉ። ይህም መጥፎ ሃሳቦችን ለሚያራግቡት ወገኖች አስደማሚ ነዉ የሆነዉ፤

Nil Dammbau in Äthiopien Archiv 28.05.2013
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

«አሁን አዲሱ ፕሬዝደንት በጣም በጣም በብልህነት ነዉ የሚንቀሳቀሱት፤ እናም አንዳችን ለሌላችን እናስባለን፤ ለግብፅ እንደምናስበዉ ለኢትዮጵያም ማሰብ ይኖርብናል፤ እናም ለሁለቱም ምን ሊገኝ እንደሚችል እናያለን ብለዋል። ይህ በእርግጥ መጥፎ ሃሳብ ለሚነዙና በአካባቢዉ ሊፈጠር የሚችለዉን ጦርነት ለማየት ለሚጠባበቁት አስገራሚ ነዉ። እኔ ግን በጣም አስተዋይነትና ጥሩ ነገር ሆኖ ነዉ ያገኘሁት።»

ግብፅ የአባይ ተፋሰስ ሃገራትን የትብብር የመግባቢያ ሰነድ እስካሁን አልፈረመችም፤ የተፋሰስ ሃገራቱ በተሰባሰቡበት መድረክም አባል አይደለችም። ዶክተር ኢብራሂም አቦሌሽ ካምፓላ ላይ በወቅቱ በተካሄደዉ ስብሰባ ግብፅ እንዳልተገኘች እንደዉም እንዳልተጋበዘች በማመልከት በአሁኑ ዉይይት ይሄም ሊነሳ እንደሚችል ነዉ የገለፁት። እንደዉም ግብፅ ስህተት ሰርታለች ሲሉም ከዚህ ቀደም የነበረዉን በአባይ ጉዳይ ለመነጋገር ፍላጎት አለማሳየቷን ተችተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ