1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የህዋ ሳይንስ ባለሙያዎች በ10 ቀናት 18 ከተሞች ያዳርሳሉ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 8 2010

ካለፈው አስር ዓመት ወዲህ የህዋ ሳይንስ በኢትዮጵያ ትኩረት እያገኘ የመጣ ይመስላል፡፡ የህዋ ሳይንስ፣ የስነ ፈለክ እና በአጠቃላይ የሳይንስ ትምህርትን የማስተዋወቅ ተመሳሳይ ዓላማ ያነገቡ ወጣት የዘርፉ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ባሉ ከተሞች በአውቶብስ ለመዞር ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2m7Fv
TRAPPIST-1
ምስል NASA/JPL-Caltech

የህዋ ሳይንስ ባለሙያዎች በ10 ቀናት 18 ከተሞች ያዳርሳሉ

የሃያ አንድ ዓመቱ ዘላለም ታረቀኝ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የአውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ነበር፡፡ ወደ ዩኒቨርስቲ የተቀላቀለው በዚያው በባህር ዳር ካለው የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ ህዋ ሳይንስ የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ቢኖረውም በሁለተኛ ደረጃም ሆነ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ስለዚህ የሳይንስ ዘርፍ በቂ ዕውቀት የሚያስጨብጠው ማግኘት አልታደለም፡፡ 

“ስለጸሀይ እና ጨረቃ፣ በህዋ ሳይንስ ስላሉ ነገሮች ገና ከድሮም ጀምሮ ልዩ ትኩረት ነበረኝ፡፡ ፍላጎቱ ያደረብኝ ከስምንተኛ እና ዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ነው፡፡ በተለይ ስለ ቅጣው እጅጉ ማወቅ ከጀመርኩኝ በኋላ እርሱ ልክ ለእኔ መነሳሻ ምክንያት ነበረ፡፡ እና አሁንም በጣም እፈልጋለሁ፡፡ ቤተ መጽሃፍታችን እንኳን ለዚህ የተመቹ ብዙም ነገሮች ስለሌሉት አብዛኛውን ጊዜ ከኢንተርኔት ነው፡፡ ዩቲዩብ ላይ ያሉ ቪዲዮዎች በማየት እንደዚሁም ጉግል ላይ ብዙ መረጃዎች አሉ እነሱን አያለሁ፡፡ ሲቀጥል ደግሞ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ንቁ ተሳታፊ ነኝ፡፡ በተለይ ከህዋ ሳይንስ ጋር የተገናኙ ሰዎች ጋር እጻጻፋለሁ፣ አወራለሁ፡፡ ከተመረቅኩኝ በኋላ ዕድሉ ቢመቻችልኝ ከህዋ ሳይንስ ጋር በተያያዘ ትምህርቶች ወስጄ ተመርቄ ከዚያ በኋላ ለኢትዮጵያ የሆነ ነገር ማበርከት እፈልጋለሁ” ይላል ዘላለም፡፡ በእርግጥም ዘላለም ለህዋ ሳይንስ ያለውን ፍቅር ለመመልከት በፌስ ቡክ ገጹ የሚከታተላቸውን ተቋማት እና ጦማሪያን ገረፍ ማድረግ ብቻ ይበቃል፡፡ ከአሜሪካው ናሳ እስከ እንጦጦ የህዋ መመልከቻ (ኦብዘርቫቶሪ) ድረስ ተዘርዝረዋል፡፡ ህዋ ነክ ጉዳዮችን በፎቶ እና ቪዲዮን በማቀናበር ቀልድ የሚፈጥሩቱም አልቀሩትም፡፡ ለዘርፉ እንዲህ ከፍተኛ ጉጉት ያለው ዘላለም በፊልሞች ላይ እንዳየው ክዋክብትን በቴሌስኮፕ የመመልከት ምኞቱ ከፍተኛ ነው፡፡ እስካሁን ግን ዕድሉ አልገጠመውም፡፡ 

Bildergalerie mysteriöse Galaxien
ምስል NASA/R. Lucas

ይህ ህልሙ እውን የሚሆንበት ቀን የተቃረበ ይመስላል፡፡ እርሱ ቴሌስኮፑ ወዳለበት መሄድ ባይችልም ቴሌስኮፑ እርሱ ወዳለበት ባህር ዳር በዚህ ወር ይመጣል፡፡ ቴሌስኮፑን እና ሌሎች ህዋን እና ሳይንስን የተመለከቱ መረጃዎችን ጭኖ ወደ ባህርዳር ሊጓዝ እየተሰናዳ ያለው አውቶብስ “አስትሮባስ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የአውቶብሱ ስያሜ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የህዋ ሳይንስ ባለሙያዎች የነደፉት የፕሮጀክት መለያም ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካው ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ዶ/ር ጌታቸው መኮንን ከባለሙያዎቹ አንዱ ናቸው፡፡ አውቶብሱ በተቻለ መጠን አይን ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ይላሉ ዶ/ር ጌታቸው፡፡

“የእኛው አውቶብስ ውጪው ሙሉ በሙሉ በስነ ፈለክ፣ ህዋ ሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በስነ ጥበብ ያጌጠ አይነት አውቶብስ ነው የምናደርገው፡፡ በውስጡ ግን የምንጠቀምባቸውን ቁሳቁሶች፣ ከደቡብ አፍሪካ ቴሌስኮፖችን ይዘን እንሄዳለን፡፡ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ እና በእንግሊዘኛ የተዘጋጁ ፖስተሮች አሉ” ይላሉ ባለሙያው፡፡

በ“አስትሮባስ” ፕሮጀክት 13 ባለሙያዎች ይሳተፉ እንጂ በአውቶብሱ በየከተሞቹ በመሄድ ገለጻ የሚሰጡት ባለሙያዎች ስምንት ናቸው፡፡ ባለሙያዎቹ በጉዟቸው በክዋክብት ጥናት እና ህዋ ሳይንስ ያለውን ግንዛቤ የመሳደግ እና የሙያ ልምዳቸውን የማጋራት አላማ ሰንቀዋል፡፡ “ዓላማችን ሶስት ነው” የሚሉት ዶ/ር ጌታቸው እንዲህ ይዘረዝሯቸዋል፡፡

“አንደኛው ወጣቱን ትውልድ ወይም ደግሞ አዲስ የሚመጣውን ትውልድ፣ ህጻናትን ወደ ሳይንሱ እንዲመጡ ፍላጎታቸው እንዲነሳሳ ለማድረግ ነው፡፡  ሁለተኛው ዓላማው ደግሞ የተለያዩ የሙያ መስኮች በአንድነት በማድረግ ኪነጥበብን፣ ቴክኖሎጂን ወይም ምህንድስናን እና ፈጠራ የምንለውን (innovation) እነዚህ ሶስቱንም የጥናት መስኮች በአንድ ላይ አድርጎ ለተሻለ ነገር መዋል እንደሚቻል ለማሳየት አስበን ነው፡፡ ለምሳሌ በእኛ በአስትሮባስ ፕሮጀክታችን ውስጥ የጨመርናቸው የስነጥበብ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ምንድነው የምናደርገው ሸራ እንወጥርና ህጻናት ወይም ደግሞ ዝግጅቱን የሚከታተል ማንኛውም ሰው በጭንቅላታቸው ውስጥ ህዋን እንዴት እንደሚስሉት በስዕል እንዲገልጹት እናደርጋለን፡፡ በትንሹ እንዲማሩበት ለማድረግ ማለት ነው፡፡ የልብስ ዲዛየነሮችም አሉ፡፡ እነርሱም ፕሮጀክታችን ውስጥ ገብተዋል፡፡ ምክንያቱም ህጻናትን ለምሳሌ ወደ ጠፈር በሚኬሄድበት ጊዜ የሚለበሰውን ልብስ ሰፔስ ሱት የምንለው በዋናው አይነት ቁስ ባይሆንም እኛ በምናገኘው ቁስ ዲዛይን ተደርጎ እንዲሰራ እና እንዲያዩት ለማድረግ ታስቦ የተደረገ ነው፡፡ 

USA Cadillac Mountain im Acadia-Nationalpark
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Perry

ሶስተኛው ደግሞ ምንድነው? ለመነሸጥ ወይም ደግሞ ወጣቶች አርአያ አድርገው ሰውን እንደሚለከቱ ለማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ተምረን ሁላችንም ጓደኞቼን በአካል ስትመለከታቸው ከ30ዎቹ አጋማሽ አይበልጥም ዕድሜያቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዕድሜያችን ሁላችንም እዚህ ደረጃ የደረስነው ከብዙ ልፋት በኋላ ስለሆነ ህጻናት እና ወጣቱ፣ አሁን ያለው ትውልድ እኛን አይቶ መነሳሳት እንዲኖረው፣ ወደሳይንስ የመምጣት ፍላጎት እንዲኖረው አርኣያ በመሆን እነርሱም ልምድ እንዲወስዱ ለማድረግ ነው” ሲሉ ዶ/ር ጌታቸው  ዓላማቸውን ያስረዳሉ፡፡

የእዚህ ሀሳብ ጠንሳሽ በሮም ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ያብባል ፋንታዬ ናቸው፡፡ ተመራማሪው በደብብ አፍሪካ ኬፕታውን ዩኒቨርስቲ በነበሩ ወቅት ከጓደኞቻቸው በስነፈለክ ጉዳይ ስለሚሰሩ ፕሮጀክቶች ይሰማሉ፡፡ ምክረ ሀሳብ ተጽፎ ስለሚገኝ የገንዘብ ድጋፍም ይነግሯቸዋል፡፡ ይሄኔ በዚያው በደቡብ አፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ ለሚገኙ ስምንት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ሀሳባቸውን በኤሜይል ይልካሉ፡፡ ምን ማድረግ እንደሚቻልም ይማከራሉ፡፡ በሀሳቡ የተደሰቱት እንደ ዶ/ር ጌታቸው በጋራ ምክረ ሀሳቡን ማዘጋጀት ላይ በረቱ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን እና የዘርፉን ማህበራት ሰዎችም አካተቱ፡፡ ወደ ስምንት ወር ከወሰደ ዝግጅት በኋላ የተሰናደው ምክረ ሃሳብ ወደ ለዓለም ዓቀፍ የስነ ፈለክ ህብረት ተላከ፡፡ ተቀባይነትም አገኘ፡፡ 

“አስትሮባስ” ፕሮጀክት የጥበብ እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ከስነ ፈለክ እና ህዋ ሳይንስ ባለሙያዎች ጋር ያቀናጀ ነው፡ ይህ የተለያዩ ዘርፎችን የመዋሃድ ሙከራ በሌላው ሀገር ከተለመደው ለየት እንደሚያደርገው ዶ/ር ጌታቸው ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት እንደ መነሻ ሆኖ ያገለገለው እና በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሴኔጋል ከሁለት ዓመት በፊት የተደረገ ተመሳሳይ የአውቶብስ ጉዞ ህዋ ሳይንስ ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በስነ ጥበብ እገዛ ከባድ የሚባሉ የህዋ እና የስነ ፈለክ ሀሳቦችን ማስተማር እንደሚቻል ዶ/ር ጌታቸው ይጠቅሳሉ፡፡ በብዙ ባለሙያዎች ዘንድ ግን ሁለቱን ዘርፎች አዋህዶ ለመጠቀም ተነሳሽነት የለም ባይ ናቸው፡፡

“እኛ ግን በምን አሰብነው ጥበብ በመኖሩ ህጻናት ስለ ህዋ ያላቸውን ግንዛቤ በስዕል እንዲያስቀምጡ እናደርጋለን፡፡ የስዕል ባለሙያዎችም ደግሞ የሚያስፈልገውን የቀለም ዓይነት እንዲያዘጋጁ ተደርጓል፡፡  ሸራ ተዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ ህጻናት ተነስተው የሚፈልጉትን ነገር ይስላሉ፡፡ በተጨማሪም ቴክኖሎጂን እኛ እንጠቀማለን፡፡ ከኬንያ የሚመጡ ኢትዮጵያዊ የIBM ልጆች አሉን፤ እዚያ የሚሰሩ፡፡ በቴክኖሎጂው ሁሉንም ለምሳሌ ተግባራዊ ሙከራዎች የምንላቸው አሉ፤ ማንኛውም ህጻናት በእጃቸው እየነኩ፣ ቴሌስኮፖቹን  በቀላሉ እንዲሰሩ እናደርጋለን፡፡ እኛ ከገለጽንላቸው በኋላ ራሳቸው ህጻናት ነገሮችን እንዴት አድርገው አዋህደው ቴሌስኮፖችን መስራት እንደሚችሉ ለማድረግ የሚያስችል ማለት ነው” ብለዋል፡፡

Weltraumabfall bei Stern Weißer Zwerg
ምስል NASA/ESA/STScI/G. Bacon

ወጣቶቹ ባለሙያዎች እነዚህን ተግባራት በየከተሞቹ እየዞሩ ለማከናወን አስር ቀን መድበዋል፡፡ አውቶብሳቸው በትልልቅ ከተሞች ላይ ለሁለት ቀናት ቆይታ የሚያደርግ ሲሆን አነስ ያሉ በሚሏቸው ደግሞ ከሁለት እስከ ሶስት ሰዓት ይቆማል፡፡ ለዕይታ የሚያበቋቸውን ነገሮች በርካታ ሰው መጥቶ እንዲጎበኝ በማሰብ አውቶብሳቸውን በከተሞች ማሃል ላይ የማቆም ሀሳብ አላቸው፡፡ ባለሙያዎቹ ሶስት የጉዞ መስመሮችን ቀይሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ሀዋሳ በመጪው አርብ ጥቅምት 10 የሚጓዙበት ነው፡፡ ቢሾፍቱ፣ ዝዋይ እና ሻሸመኔ በዚህ መስመር የጥቂት ሰዓታት ቆይታ የሚደረግባቸው ናቸው፡፡ ባለሙያዎቹ ወደ አዲስ አበባ በሚያደርጉት የመልስ ጉዞ ከሀዋሳ ተነስተው አርባ ምንጭ፣ ወላይታ፣ ሆሳዕና እና ቡታጅራን የማዳረስ እቅድ አላቸው፡፡

ሁለተኛው የጉዞ መዳረሻቸው አዳማ ይሆናል፡፡ በዚያ የሁለት ቀናት ቆይታ ያደርጋሉ፡፡ በመቀጠል አዲስ አበባን መነሻ አድርገው በሰሜን አቅጣጫ ፍቼ፣ ደጀን፣ ደብረማርቆስ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ወልዲያ፣ ደሴ እና ኮምቦልቻን የማካለል ሀሳብ አላቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ደብረማርቆስ፣ ባህር ዳር እና ጎንደር ለሁለት ቀናት ቆይታ ተመርጠዋል፡፡ በከተሞቹ ባሏቸው ቆይታ ሊያደርጓቸው ያሰቧቸውን ክንውኖች ዶ/ር ጌታቸው ያብራራሉ፡፡ 

“የመጀመሪያው የቀን ፕሮግራም አለን፡፡ እያንዳንዳችን ስለስነፈለክ፣ ስለ ህዋ ሳይንስ የተለያዩ ነገሮች እናቀርባለን፡፡ ልምዳችንን እናካፍላለን፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ ፖስተሮቻችን ለምልከታ እንደሚቹ ተደርገው ይቀመጣሉ፡፡ ሰው እየገባ እነሱን ያነባል፡፡ ጥያቄዎችን ያነሳል፡፡ ጥያቄዎችን እንመልሳለን፡፡ በዚህ መልኩ ሰውን ለማስተማር እንሞክራለን፡፡ ከዚያ ደግሞ የማታ ዝግጅት አለን፡፡ የሰማይ ምልከታ የምንለው አለ፡፡ ማታ ደግሞ የተለያዩ ስነ ክዋክብትን በቴሌስኮፕ እያሳየን ማህብረሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው እናደርጋለን” ብለዋል ባለሙያው፡፡

እንዲህ አይነት ተነሳሽነቶች የሚያበረታታው የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ማህብረሰብ የተሰኘው ማህበር ከ“አስትሮባስ” ሀሳብ ጠንሳሾች ጋር በትብብር እየሰራ ነው፡፡ አውቶብሱ ከሚጓዝባቸው ቦታዎች ሀዋሳ፣ ባህርዳር እና አዳማ የቀናት ቆይታ እንዲደረግባቸው  ለመመረጣቸውም የማህበሩ አስተዋጽኦ አለበት፡፡ የማህበሩ የህዝብ ግንኙት ኃላፊ ቤዛ ተስፋዬ በእነዚህ ከተሞች ስለህዋ ሳይንስ ማወቅ የሚፈልጉ በርካታ ወጣቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ፍላጎቱ በአብዛኛው የሚታየው ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ ባሉ ተማሪዎች እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

Installation Teleskope in Addis Abeba
ምስል DW/Getachew Tedla Hailegiorgis

“እኛ በስራ በኩል ወደዚያ ብዙ እንሄዳለን፡፡ ቅርንጫፎች አሉን፡፡ በቅርንጫፎቹ አባላትም አሉን፡፡ በእነዚያ ስራ ስናይ በጣም ፍላጎቱ እንዳለ ነው፡፡ ግን ከየት ወዴት ወዴየት የሚለው ነገር ገና ብዙ ተጣርቶ አይታወቅም፡፡ ሰው ይፈልጋል ግን እንደዚህ ብዙ ክንውኖች፣ እርስ በእርስ ተገናኝቶ የሚወያይበት እና ብዙ መማር  የሚችልበት መድረኮች ብዙ አልነበሩም፡፡ እና አሁን ይሄኛው በአውቶብስ መዞሩ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለን እናስባለን፡፡ ዋናው ዓላማ ሰውን ማነቃቃት ነው፡፡”

ስለአውቶብሱ ጉዞ መረጃ ያልነበረው የባህርዳር ዩኒቨርስቲው ዘላለም ስለ“አስትሮባስ” ሲነገረው በእቅድ ይዞት የነበረውን ጉዳይ ለማማከር ወስኗል፡፡ በዩኒቨርስቲው የህዋ ሳይንስ ክበብ ለማቋቋም ምክረ ሀሳብ ማዘጋጀቱን የሚናገረው ዘላለም ከባለሙያዎቹ አጥጋቢ ምክሮች ለማግኘት ተስፋ ሰንቋል፡፡    

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ