1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃይድሮ ፍሎሮ ካርቦን ቅነሳ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 8 2009

ዓለም የሙቀት መጠን እንዲቀንስ ለማድረግ ሃገራት ሊወስዷቸዉ የሚገቡ ርምጃዎች ላይ ስምምነቶች እየተደረሱ መሆኑ እየተነገረ ነዉ። ኪጋሊ ሩዋንዳ ላይ የተሰባሰቡት 200 የሚሆኑት ሃገራት ባሳለፍነዉ ቅዳሜ ሃይድሮ ፍሎሮ ካርበንን አጠቃቀም ላይ ገደብ ለማድረግ መስማማታቸዉ ተሰምቷል።

https://p.dw.com/p/2ROTH
Mäßig gefüllter Kühlschrank
ምስል DW/H. Kiesel

 ስምምነቱ ባለፈዉ ዓመት ፓሪስ ላይ ሃገራቱ የተስማሙበትን ብክለት የመቀነስ ቁርጠኝነት ያጠናክራል፤ ትልቅም ርምጃ ነዉ የሚሉ አሉ። በተቃራኒዉ ስምምነቱ አንድ ነገር ቢሆንም ለመሆኑ ምን ያህል መጠን ከባቢ አየር ዉስጥ አለና ነዉ ብለዉ የሚጠይቁም አልጠፉም።

ከ190 በሚበልጡ ሃራት ኪጋሊ ላይ የተስማሙት ሃይድሮ ፍሎሮ ካርቦኖች አጠቃቀም እና ምርቱም ላይ ገደብ ለማድረግ ነዉ። ሃይድሮ ፍሎሮ ካርቦኖች ከባቢ አየር ዉስጥ ሙቀትን በማመቅ የመድራችንን ሙቀት እንዲጨምር አድርጓል፤ የአየር ብክለትንም አስከትሏል በሚል ከሚወቀሰዉ ካርቦን ዳይኦክሳይድ የበለጠ ጉዳትንም ያስከትላሉ ነዉ የተባለዉ። በትክክል ሃይድሮ ፍሎሮ ካርቦኖች ምንድናቸዉ? በአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለዉጥ ሚኒስቴር፤ የደን ዘርፍ አቅም ግንባታ መርሃግብር አስተባባሪ ዶክተር ተፈራ መንግሥቱ ያብራሩታል።

እነዚህ ሃይድሮ ፍሎሮ ካርበኖች ወደላይ ከፍተኛዉ የከባቢ አየር ንጣፍ ድረስ ሄደዉ በሚያደርሱት ጉዳትም አደገኛዉ የፀሐይ ጨረር መሬት ላይ አርፎ የሰዎችን ጤና በማወቅ ብቻ አይገቱም፤ የዓለም የሙቀት መጠን እንዲጨምርም አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ዶክተር ተፈራ ያስረዳሉ።  

Klimaanlage in Asien
ምስል picture-alliance/dpa

በኪጋሊዉ ስምምነት መሠረት ሃይድሮ ፍሎሮ ካርቦኖችን ማምረትም ሆነ መጠቀም በሦስት ደረጃዎች በመከፋፈል ነዉ እንዲቀነሱ የተወሰነዉ። አብዛኞቹ በኢንዱስትሪ ያደጉት እና አንደኛዉ ዓለም በመባል የሚታወቁት እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ ዘመን 2018፤ እነ ቻይና፣ ብራዚል እና መላዉ አፍሪቃ እስከ 2024፣ ሕንድ ፓኪስታን እና ሌሎች በርካታ ሃገራት ደግሞ እስከ 2028 ድረስ እንዲቀንሱ ነዉ የተደለደሉት። በተጠቀሱት የጊዜ ገደቦችም የሃድሮ ፍሎሮ ካርቦን ምርትም ሆነ ጥቅም ላይ መዋላቸዉ ከ15 እስከ 20 በመቶ ለመቀነስ ነዉ የታቀደዉ። ይህ ደግሞ የዓለም የሙቀት መጠንን በ0,5 ዲግሪ ዝቅ እንዲል ይረዳል ነዉ ተስፋዉ። የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት አቶ አለባቸዉ አደም ኑርዬ ሃገራቱ የደረሱበት ስምምነት ትልቅ ርምጃ ነዉ ባይ ናቸዉ።

የአየር ንብረት ለዉጥን የሚያስከትሉ ሙቀት አማቂ ጋዞችን በየደረጃዉ ለመቀነስ የሚደረጉ ስምምነቶች ስብስብ በዚህ ጉዳይ በመጪዉ ኅዳር ወር መገባደጃ ላይ የሚደረገዉን አብይ ድርድር ወደፊት ትንሽ ሊያራምደዉ እንደሚችል ነዉ ተስፋ የተደረገዉ።

 ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ