ዚምባብዌ ና የአልማዝ ማዕድኗ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 4 2005የአልማዝ ማዕድን በብዛት ከሚመረትባት ከዚምባብዊ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ አልማዝ ተስርቋል ሲል አንድ የአልማዝ ንግድ ታዛቢ ድርጅት አስታወቀ ። እንደ ድርጅቱ ተሰርቋል ያለው ገንዘብ ለዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ፓርቲ ዛኑ ፒፍ ባለሥልጣናትና ለደላላሎች መበልጸጊያ ነው የዋለው ። መንግሥት ግን ክሱን ሃሰት ና በምዕራባውያን የተፈበረከ ሲል አጣጥሎታል ። የዶቼቬለ የዚምባብዌ ዘጋቢ ኮምቡስ ማቭሁንጋ የዘገበውን ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።ፓርትነርሽፕ አፍሪቃ ካናዳ በተባለው የአልማዝ ንግድ ታዛቢ ድርጅት ትናንት ባወጣው ዘገባ የዚምባብዌአልማዝ ለሃገሪቱ ሳይሆን ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መበልፀጊያ መዋሉን ይጠቁማል ። የዚምባብዌ የማዕድንንና ልማት ኮርፖሬሽን ሃላፊ ጉድ ዊል ማሲሚሬምብዋ ግን ዘገባውን አጣጥለው ምዕራባውያን የፈበረኩት ወሪ ነው በለዋል ። ሃላፊው ዘገባው የወጣበትን ጊዜ ራሱ አጠያያቂ ነው ይላሉ ።
በርሳቸው አባባል ይህ ዘገባ የወጣው ዚምባብዌ ገፅታዋን ለማስተካከል በአልማዝ ማዕድን ንግድ ላይ የሚነጋገር ጉባኤ በምታስተንግድበት ወቅት ነው ። ማሲሚሬምብዋ በዘገባው ላይ አስተያየት ከመስጠት ይልቅ የዚምባብዊ አልማዝ በአለም ገበያ ትክክለኛውን ዋጋ እንዲያገኝ ምዕራባውያን በሃገሪቱ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ማንሳት ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል ። እጎአ በ2ሺህ አመተ ምህረት ዚምባብዌ ሰብአዊ መብት እንደምትጥስ ዘገባ ከቀረበ በኋላ ምዕራባውያን በዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ና በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ላይ የተመረጡ ማዕቀቦች ጥለውባቸዋል ። በሃገሪቱ የሚካሄደው የሰብአዊ መብት ጥሰት ወደ ሃገሪቱ የማዕድን ማውጫዎችም በመዛመቱ የአለም የአልማዝ ንግድን የሚቆጣጠረው ኪምብርሊ ፕሮሰስ ዚምባብዌን ከአልማዝ ንግድ ገበያ ለማገድ አስገድዶታል ። ይህ እገዳ ግን ተነስቷል ። ያማለት ግን የአውሮፓ ህብረት በዚምባብዌ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ያነሳል ማለት እንዳይደለ በዚምባብዌ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር አልዶ ዴል አሪካ ተናግረዋል
ብራሰልስና ሃራሬ ግንኙነታቸውን ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ የሚያካሂዱት ንግግር ዚምባብዌ እንደምትለው በአውሮፓ የአልማዝ ገበያ ዋጋ ላይ የፅእኖ እያሳደረ ነው ። ከአለም ከፍተኛ የአልማዝ ክምችት የሚገኝባቸው የዚምባብዌ የአልማዝ ማዕድን ማውጫዎች የሃገሬቱን ኤኮኖሚ ከሚገኝበት አዘቅት እንዲወጣ አላገዙም አንዳንዶች የችግሩ ምክንያት ሙስና ነው ይላሉ ። ሙጋቤ ደግሞ ምክንያቱ ማዕቀቡ ነው ይላሉ ። በዚህ መነሻ ነው መንግሥት ለችግሩ መፍትሄ ፍለጋ የ 2 ቀናት ጉባዜ ያዘጋጀው ። በዚሁ ጉባኤ ላይም ዓለም አቀፍ ደላሎችና ከአልማዝ አምራች ሃገራት የተውጣጡ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል ። ሻሚሶ ሚትሶ የተባሉት የዚምባብዌ የሲቪል ማህበራት ጥምረት መሪ እንዳሉት ጉባኤው በሰዎች ችግሮች ላያ ካላተኮረ ለርሳቸው ትርጉም አይኖረውም ።
ኮሎምቡስ ማቭሁንጋ
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ