1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዚምባብዌና እየቆረቆዘ የሚሄድ ብሄራዊ ኤኮኖሚዋ

ረቡዕ፣ ጥር 9 1999

ብሄራዊ ኤኮኖሚዋ በድቀት ላይ የሚገኘው የዚምባብዌ ጉዞ በዚህ በአዲሱ 2007 ዓ.ም.ም የጨለመ ሆኖ የሚቀጥል ነው የሚመስለው። አንዴ “የአፍሪቃ የዳቦ ቅርጫት” በመባል በዕድገት አርአያነት ትታይ የነበረችው የደቡባዊው አፍሪቃ ግዛት ዛሬ በውድቀቷ በዓለም ላይ አቻ ተፈልጎ አይገኝላትም።

https://p.dw.com/p/E0dF
ፕሬዚደንት ሙጋቤ
ፕሬዚደንት ሙጋቤምስል dpa

ተወዳዳሪ የሌለው የኑሮ ዋጋ መወደድ፣ ቆርቋዥ ኤኮኖሚ፤ እንዲሁም የሕዝብ የሕይወት ዘመን ማቆልቆል ልዩ ባሕርያቷ ሆነዋል። ዚምባብዌ የውጭ ዕዳዋን መክፈል አልቻለችም፤ ሕዝቧ በሁሉም ነገር እጥረት ተወጥሮ ነው የሚገኘው። ዚምባብዌ ወዴት! ዚምባብዌ አሁን ለሰባተኛ ዓመት ብርቱ በሆነ የኤኮኖሚ ቀውስ ተወጥራ ነው የምትገኘው። የነጮችን መሬት መነጠቅ ተከትሎ ምዕራቡ ዓለም፤ በተለይም አውሮፓውያን መንግሥታት በአገሪቱ ላይ የጣሉት ማዕቀብ መዘዙ ቀላል አልሆነም።

የመሠረታዊ ምግብ ምርቶች ዋጋ በሶሥትና በአራት ዕጅ መናር፤ የውጭ ምንዛሪ እጦትና የምርት ማቆልቆል የአገሪቱን ኤኮኖሚና ማሕበራዊ ኑሮ ክፉኛ አደንዝዞታል። ከዚምባብዌ ነጻነት ወዲህ ለ 27 ዓመታት አገሪቱን ሲያስተዳድሩ የቆዩት የ 82 ዓመቱ አንጋፋ መሪ ሮበርት ሙጋቤ የአገሪቱን ኤኮኖሚ መልሶ ለማነሣሣት ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ቅድሚያ የሚሰጠው የብሄራዊ ልማት ዕቅድ አውጥተው በሥራ ላይ እንዲውል ቢያደርጉም እስካሁን ይህ ነው የሚባል የታየ ፍሬ የለም።

ለብዙሃኑ የዚምባብዌ ሕዝብ 2007 ዓ.ም.ም የጀመረው የበቆሎ ዱቄትን፤ ስንዴን፣ መቀቀያ ዘይትንና ስኳርን የመሳሰሉት መሠረታዊ ምርቶች እጥረት ወሰን ባለፈበት ሁኔታ ነው። በከሰል እጥረት የተነሣ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ሃይል እስከ አሥር ሰዓታት ያህል ሊቋረጥ እንደሚችልም የአገሪቱ አከፋፋዩ ባለሥልጣን ሰሞኑን አስጠንቅቋል። የአውሮፓ ሕብረት በአገሪቱ ላይ የጫነው ማዕቀብ ተጽዕኖ በቀላሉ ሊቋቋሙት የሚቻል አልሆነም። ከአገሪቱ ሕዝብ ግማሹ በሞት አፋፍ ላይ ነው የሚገኘው።

የአውሮፓ ሕብረት በዚምባብዌ ላይ ማዕቀብ የጫነው ተቃዋሚው ወገን ተጭበርብሯል ያለው የ 2002 ምርጫ ተካሂዶ ሙጋቤ የሥልጣን ዘመናቸውን እንደገና ካራዘሙ በኋላ ነበር። ሕብረቱ ሙጋቤና የቅርብ አበሮቻቸው ወደ አውሮፓ እንዳይጓዙ፤ በውጭ የሚገኝ ገንዘባቸውን እንዳሳንቀሳቅሱ አግዷል። ማዕቀቡ ለሃራሬ ማንኛውም ወታደራዊ ዕርዳታ እንዳይሰጥም ገደብ የጣለ ነው። ይሁንና ማዕቀቡ እስካሁን ሙጋቤን አላንበረከከም፤ ጎልቶ የሚታየው የሕዝቡ መከራ መባባሱ ነው።
የዚምባብዌ ሕዝብ በዚህ የኤኮኖሚ ምስቅልቅልና ውድቀት ሳቢያ በያዘው የሞትና የሽረት ትግል ባገኘው ዘዴ ላይ ሁሉ ሲረባረብ ወይም በገፍ ወደ ውጭ ሃገራት ሲሸሽ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ በበኩላቸው ሥልጣናቸውን ለማቆየት የአገሪቱን ወጣት ትውልድ የወደፊት ዕድልና ተሥፋ መቅጨታቸውን ቀጥለዋል። መንግሥታዊ ፓርቲያቸው ሥልጣኑን እስከ 2010 ለማራዘም ጥርጊያ ማመቻቸት ይዟል፤ ሙጋቤ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሐብት ቻይና ለምታቀርበው በሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ እንደ መያዣ ሊሰጡ እያቅማሙ ነው።

በዚህ ሁኔታ ጀርመንና ሌሎች መንግሥታት ለዚምባብዌ ያበደሩትን ገንዘብ መልሰው የማግኘታቸው ተሥፋ የጨረቃን ያህል የራቀ እየሆነ መሄዱ አልቀረም። ኪሣራ የተጠናወተው የዚምባብዌ መንግሥት በመሠረቱ የጀርመን መልሶ ግንባታ አበዳሪ ተቋም ከዓመታት በፊት ያቀረበለትን አርባ ሚሊዮን ኤውሮ ገና ድሮ መመለስ ነበረበት። ይህን ፓሪስ ላይ ተቀማጭ የሆነው ዓለምአቀፍ የንግድ ም/ቤት ሲወስን ሆኖም ግን ጀርመን ገንዘቧን መልሳ የማየቷ ዕድል የመነመነ ነው።

ለምን፤ ዚምባብዌ በለየለት ሁኔታ የከሰረች አገር ናት። የኑሮ ዋጋ መወደድ ወይም የምንዛሪዋ ውድቀት በመቶ ሲሰላ 12 እጥፍ ደርሷል፤ ይህም በዓለም ላይ አቻ የሌለው ነው። 80 በመቶው የዚምባብዌ ሕዝብ ወይም ከአምሥት-አራቱ ሥራ-አጥ ሲሆን ብዙዎች ኩባንያዎች በኤኮኖሚው መዋቅር መንኮታኮት ሳቢያ እየዘጉ መሄዱን መርጠዋል። ወደ ጀርመኑ ብድር እንመለስና በአሕጽሮት KfW በመባል የሚታወቀው የመልሶ ግንባታው አበዳሪ ተቋም እ.ጎ.አ. በ 1998 ዓ.ም. በከፊል የዚምባብዌ መንግሥት ይዞታ ለነበረው Ziscosteel ለተሰኘ የብረታ-ብረት ፋብሪካ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረውን ብድር ይሰጣል። ብድሩ የተሰጠው የጀርመንን የመንግሥት ዋስትና ተገን በማድረግ ነበር።

በስምምነቱ መሠረት MAN Ferrostahl የተሰኘው በምዕራባዊው ጀርመን ኤሰን ከተማ የሚገኝ ኩባንያ የተጠቀሰውን የዚምባብዌን የብረታ-ብረት ፋብሪካ መልሶ-ማነጽና ለተግባር ማብቃት ነበረበት። ኩባንያው የሚያገኘው ክፍያም ለዚምባብዌ በተሰጠው ብድር እንዲሸፈን ይታቀዳል። ሆኖም ብድሩ ከተሰጠ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ 2000 ዓ.ም. የዚምባብዌ መንግሥት በያዘው የመሬት ስሪት ፖሊሲ ሳቢያ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነጭ ገበሬዎች መባረር ይጀምራሉ። የአገሪቱ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ውድቀትም የጀመረው ከዚህ በኋላ ነው። ይህ ደግሞ በጊዜው የተጠበቀ አልነበረም።

ለማንኛውም በወቅቱ በመልሶ-ግንባታው ተቃም ብድር የሚንቀሳቀስ ፕሮዤ ባይኖርም የብረታ-ብረት ፋብሪካው በኪሣራም ቢሆን መንቀሳቀሱን አላቋረጠም። ሆኖም የዚምባብዌ መንግሥት ብድሩን መቼ እንደሚመልስ እስካሁን ያለው ጭብጥ ነገር የለም። ዚምባብዌ በዓለም የምንዛሪ ተቋም ዘንድ 150 ሺህ ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ተጭኗት ነው የሚገኘው። ከሁለት ዓመት በፊት ቻይና ፈጥኖ ደራሽ ሆና ብድር ባትሰጣት ኖሮ ዚምባብዌ እንዲያውም በድርጅቱ መገለሏ ነበር።

ታዲያ ቻይና ባለፉት ዓመታት በብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች እንዳደረገችው ሁሉ ለውለታዋ ምላሽ መሻቷ፤ በዚምባብዌ የብረታ-ብረት ሃብት ላይ ዓይኗን ማሳረፋም አልቀረም። አሁን ከአንድ የደቡብ አፍሪቃ ጋዜጣ ለማወቅ እንደተቻለው ቻይና የ Ziscosteel-ን 60 በመቶ ድርሻ ወይም ሼር ለመያዝ ፍላጎት አላት። ይህም ሆኖ ግን ጀርመን ከዚምባብዌ የምትጠብቀውን የዕዳ ምላሽ ቢቀር በቅርብ ጊዜ ማግኘቷ ሲበዛ የሚያጠራጥር ነው። ለጀርመን የመልሶ-ግንባታ ተቋም የሚቀረው ምርጫ አንድ ብቻ ይሆናል። ይሄውም በውጭ የሚገኝ የዚምባዌ ሃብት እንዲወረስ ማስደረግና ከዚሁ ድርሻውን ለማግኘት መሞከር! ግን ይህም ቀላል ነገር አይሆንም።

ለመሆኑ የዚምባብዌ ሁኔታ እንዴት ሊቀጥል ይችላል? የአውሮፓ ሕብረት ምንም እንኳ ፈረንሣይና ፖርቱጋል ቅሬታ ቢኖራቸውም በቅርቡ ማዕቀቡን ማራዘሙ የማይቀር ነው የሚመስለው። የሕብረቱ የማዕቀብ ዕርምጃ ከዴሞክራሲና ከሰብዓዊ መብት ግንዛቤ ይልቅ የሙጋቤ ጸር የሆነችው የብሪታኒያ ግፊት የፈጠረው ነው፤ በአፍሪቃ አምባገነኑ ሙጋቤ ብቻ አይደሉም ሲሉ ተጽዕኖውን የሚቃወሙት ብዙዎች ናቸው። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዕውነት አላቸው። ያም ሆነ ይህ የእስካሁኑ ተጎጂ የሃራሬ መንግሥት ሣይሆን ሕዝቡ መሆኑ ነው ሃቁ!