1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዚምባቡዌ የምርጫ ጥሪና የመንግሥት እርምጃ

ዓርብ፣ መጋቢት 2 2003

የዚምባቡዌ ፕሬዝዳት ሮበርት ሙጋቤ ከጥቂት ወራት በሕዋላ አዲስ ምርጫ እንደሚደረግ በቅርቡ አስታዉቀዋል።የምርጫዉ ትክክለኛ ቀን በዉል ሳይወሰን ግን የሐገሪቱ ፀጥታ አስከባሪዎች የሙጋቤ ተቃዋሚዎችን፥ የተቃዋሚዎቹን ደጋፊዎችና የመብት ተሟጋቾችን እያሰሩና እየደበደቡ ነዉ።

https://p.dw.com/p/R8Wt
ምስል AP

ከሙጋቤ ፓርቲ ጋር ብሔራዊ አንድነት መንግሥት የመሠረዉና MDC በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉን ፓርቲ አባላት እንደሚሉት የሙጋቤ እቅድ ተቃዋሚዎቻቸዉን አስፈራርተዉና አሸማቀዉ ምርጫዉን ለማሸነፍ ነዉ።ኤሊሳቤት ጃን የዘገበችዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል። 

ዘጋቢ ኤልሳቤት ጃን እንደምትለዉ ርዕሠ-ከተማ ሐራሬ ዉስጥ ታንክ፥ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፥ ዉሐ መርጫ መኪኖች፥ እና ፀጥታ አስከባሪዎችን ያሳፈሩ ካሚዮኖች የማይታዩበት መንገድ የለም።የዚምባቡዌ ሴቶችን አንቂ (WOZA) የተሰኘዉ ማሕበርና ሌሎች የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ደግሞ የፕሬዝዳት ሙጋቤ መንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች በብዛት የሚታዩት ሐራሬ ብቻ አይደለም።በሌሎች ከተሞችም የተጠናከረ ቁጥጥር ያደርጋሉ፥ ተቃዋሚዎችና የመብት ተሟጋቾችን ያንገላታሉ፥ ያሸማቀቃሉም።

ባለፈዉ ማክሰኞች የዋለዉን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በዋዜማዉ ሰኞ ቡላዋዮ የተባለችዉ የሐገሪቱ ደቡባዊ ምዕራብ ከተማ ሴቶችን ለሠላማዊ ሠልፍ ጠርቶ ነበር።የማሕበሩ ባልደረባ ማጎዶንጋ ማላንጉ እንዳሉት ግን ሰልፉ እንደተጀመረ ፖሊስ ሠልፈኛዉን አባረረዉ፥ የተወሰኑትንም አሰራቸዉ።

«ፖሊሶች ከተማይቱን አጥለቅልቀዋታል።ሰወስት ባልደረቦቻችን ታስረዉብናል።በይፋ የቀረበባቸዉ ክስ የለም።እስካሁን ድረስ ጠበቃ እንዲያነጋግሩም አልተፈቀደላቸዉም።»

ሠልፉ ከመበተኑ በፊት ሠልፈኞቹ የሐገራቸዉ ፀጥታ አስከባሪዎች ያደርሱብናል የሚሉትን በደል ለማስቆም የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝዳት ያኮብ ዙማ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዉ ነበር።የዚምባቡዌ የመብት ተሟጋቾችና ሑይማን ራይትስ ወች የተሰኘዉ አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት በየፊናቸዉ እንዳስታወቁት ፕሬዝዳት ሙጋቤ የሚመሩት የዛኑ-ፒኤፍ ፓርቲ አባላትና ካድሬዎች በተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ በደል እየፈፀሙ ነዉ።

ዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ፣ንቅናቄ ለዲሞክራሲያዊ ለዉጥ (MDC-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) እንዳስታወቀዉ እስከ የካቲት ማብቂያ ድረስ ብቻ አርባ-አምስት አባላቱ የቱኒዝያዉንና የግብፁን ሕዝባዊ አብዮት በቴሌቪዥን ተመለከታችሁ ተብለዉ ታስረዉ ነበር።ኋላ ግን ብዙዎቹ ተለቀዋል። ካልተለቀቁት መካካል ከፍተኛ ወንጀል ፈፅመዋል የተባሉ ስድስቱ ሞት የሚያስቀጣ የወንጀል ጭብጥ ተይዞባቸዋል።

የእስረኞቹ ጠበቆች እንደሚሉት ብዙዎቹ እስረኞች ተደብድበዋል።አንዳዶቹ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።የሑዩማን ራይትስ ወች ባልደረባ ቲሴኬ ካሳምባላ እንደሚሉት ዛኑ-ፒኤፍ የወደፊቱን ምርጫ ዉጤት በሐይል ለመቆጣጠር እየጣረ ነዉ።

«የምናየዉ እርምጃዉ ሕዝቡ ለዛኑ-ፒ ኤፍ ድምፁን እንዲሰጥ ለማስገደድ የሚደረግ ሙከራ ነዉ።ምክንያቱም ፓርቲዉ ከዚሕ ቀደምም ተመሳሳይ ነገር ሲያደርግ አይተናልና።»

በርግጥም እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር የሁለት ሺሕ ስምንቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመደረጉ በፊትም የሙጋቤ ሐይላት ተቃዋሚዎቻቸዉን ሲስሩ፥ ሲደበድቡ፥ ሲያሰቃዩም ነበር።የምርጫዉ ዉጤትም ለአንድ አመት ያሕል ሲያወዛግብና ሲያጋጭም ነበር።ሙጋቤ አሁን የሚመሩትን ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ለመመሥረት የተገደዱትም ምዕራባዉያን ሐገራት በማዕቀብ ከቀጧቸዉና ከፍተኛ ግፊት ካደረጉባቸዉ በሕዋላ ነዉ።

የኤም ዲ ሲ ባለሥልታናት እንደሚሉት ሙጋቤ በአፍሪቃ መሪዎች በተለይም በቀደሞዉ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳት ታቦ ኢምቤክ ሸምጋይነት የተመሠረተዉን የብሔራዊ የአንድነት መንግሥት አፍርሰዉ አዲስ ምርጫ ለማድረግ የፈለጉት የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥት እንዲቀየር የቀረበዉን ሐሳብ ለማፍረስ ነዉ። በመጪዉ መስከረም ይደረጋል የተባለዉ ምርጫ ጊዜዉ ከመቃረቡ በፊት አሁን የሙጋቤ ፓርቲና ታማኞች የሚያደርሱት በደል ያለፈዉን አይነት ችግር እንዳያስከትል እያሰጋ ነዉ።

ይሁንና የኤም ዲ ሲ ባለሥልጣን ኮልተርት እንደሚሉት ዚምባቢዌ በሁለት ሺሕ ሥምንት የገጠማት አይነት ችግር እንዲገጥማት የአካባቢዉ ሐገራት አይፈልጉም።

«ዚምባቡዌ ወደ ሁለት ሺሕ-ስምንቱ ትርምስ እንድትመለስ የአካባቢዉ ሐገራት አይፈልጉም።በዚሕም ምክንያት ባለፈዉ የደረሰዉ አይነት ማሸማቀቅ መፈፀሙንም የአካባቢዉ ሐገራት አይታገሱትም ብዬ አስባለሁ።»

ከአካባቢዉ ሐገራት ሁሉ በዚምባቡዌ ላይ ከፍተኛ ተፅኖ የምታሳርፈዉ ደግሞ ደቡብ አፍሪቃ ናት።እስካሁን ግን ደቡብ አፍሪቃ አቋሟን በግልፅ አላስታወቀችም።

ኤልሳቤጥ ያን

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ