1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኖቤል እነማን አሸነፉ?

ረቡዕ፣ መስከረም 26 2008

ወባ፣ ዐይነ-ማዝ እና ዝሆኔ የተባሉ በሽታዎች በዓለማችን የሰው ልጆችን ይገድላሉ አለያም አካል ጉዳተኛ ያደርጋሉ። ለዚህ ዓመት የኖቤል ሽልማት ሎሬቶች ምሥጋና ይድረሳቸውና በሽታዎቹ ከእንግዲህ በሕክምና ይድናሉ።

https://p.dw.com/p/1Gk0T
Anopheles Mücke schlägt zu
ምስል picture-alliance/dpa/ Birgit Betzelt/actionmedeor

ዘንድሮ በኖቤል እነማን አሸነፉ?

በስዊድን መዲና ስቶክ ሆልም የሚገኘው የካሮሊንስካ ተቋም በሕክምና የዘንድሮዎቹ የኖቤል አሸናፊዎችን ስም ሰኞ ዕለት ይፋ አድርጓል። በጥገኛ ትሎች የሚከሰት ምርቀዛን በአዲስ ዘዴ ማከም እንደሚቻል ያስተዋወቁ እንዲሁም የወባ በሽታን ለመከላከል መድሐኒት ያገኙ ሣይንቲስቶች በሕክምና ተሸላሚ ሆነዋል።

በምንኖርባት ምድር በአንድ ወቅት ገዳይ ወይንም ለአካል ጉዳት ይዳርጉ የነበሩ አንዳንድ በሽታዎች ከእንግዲህ በሕክምና ሊወገዱ እንደሚችሉ ተገልጧል። በዘንድሮው የኖቤል ሽልማት እንደ ወባ፣ ዐይነ-ማዝ እና ዝሆኔ የመሳሰሉ በሽታዎች በሕክምና ሊድኑ እንደሚችሉም ተበስሯል።

በተለያዩ ዘርፎች በየዓመቱ የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት ዘንድሮም በሕክምናው ዘርፍ እመርታ ላሳዩ ሣይንቲስቶችና ተመራማሪዎች ሽልማት በመስጠት ተጀምሯል።የመድሐኒቶች ግኝት አንዳንዴ በሕክምናው ዘርፍ ለኖቤል ሽልማት የመብቃታቸው ጉዳይ አንዳችም ትንታኔ አያስፈልገውም። ለምሳሌ ግኝቱ ልክ እንደ ዘንድሮው የሚሊዮኖችን ሕይወት የሚታደግ ከሆነ።

የአየርላንድ ተወላጁ ዊልያም ሲካምፕቤል፣ ጃፓናዊው ሳቶሺ ኦሙራ እና ቻይናዊቷ ዩዩ ቱ
የአየርላንድ ተወላጁ ዊልያም ሲካምፕቤል፣ ጃፓናዊው ሳቶሺ ኦሙራ እና ቻይናዊቷ ዩዩ ቱምስል J. Nackstrand/AFP/Getty Images

ዘንድሮ በሕክምና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት የአየርላንድ ተወላጁ ዊልያም ሲካምፕቤል፣ ጃፓናዊው ሳቶሺ ኦሙራ እና ቻይናዊቷ ዩዩ ቱ ናቸው። ዊሊያም እና ሳቶሺ ለኖቤል ሽልማት የበቁት በጥገኛ ትሎች የሚከሰት ምርቀዛን በአዲስ ዘዴ ለማከም ላካሄዱት ምርመራቸው ነው። ቻይናዊቷ ዩዩቱ ደግሞ የወባ በሽታን ለመከላከል ያስችላል ያሉትን አዲስ ዘዴ አስተዋውቀዋል።

ሦስቱ ሣይንቲስቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ያስችል ዘንድ በተሐዋስያን ላይ ላደረጉት ምርምር እና አመርቂ ውጤት እንደተመረጡ ከኖቤል ኮሚቴ ዳኞች መካከል ኡርባን ሌንድሃል አስታውቀዋል።

«በካሮሊንስተቋም የኖቤል ኮሚቴ የዚህ ዓመት በሕክምና የኖቤል ተሸላሚችን ዛሬ ይሸልማል። ዊልያም ካምፕቤል እና ሳቶሺ ኦሙራ ጥገኛ ትሎች የሚያስከትሉትን ምርቀዛን በአዲስ ዘዴ ለማከም ላኪያሄዱት ጥረት በጋራ ተሸላሚ ሆነዋል። የሽልማቱ ግማሽ ደግሞ የወባበሽታንለመታገልአዲስ መድሐኒት ላገኙት ዩዩ ይሆናል።»

ዩዩቱአርተሚሲኒን የተሰኘውን የወባ መድሐኒት ያገኙት በባሕላዊ መንገድ ለሕክምና ይውል ከነበረ ቅጠል ነው። አርተሚሲኒን ፈዋሽነቱ እንደተረጋገጠለት ተነግሯል። ዩዩቱ ያገኙት የወባ መድሐኒት የተቀመመው በሣይንሳዊ አጠራሩ አርተሚስያ አኑዋ ከተሰኘ የቅጠል አይነት ነው። ይህን ቅጠል ቻያናውያን ለዘመናት ለባሕላዊ ሕክምና ይጠቀሙበት እንደነበር ይነገራል።

በቪየን ዩኒቨርሲቲየወባ ተመራማሪው ሚሻኤል ራምሃርተር «የአርተሚሲኒንን መድሐኒት መገኘት ታላቅ ስኬት» ብለውታል። የመድሐኒቱ አስተማማኝነትም መስክረዋል።

«አርተሚሲኒን የወባ ተሐዋሲን በፍጥነት በመግደል ታማሚው በፍጥነት ከትኩሳት እና ከበሽታው ምልክቶች ነፃ እንዲሆን የሚያስችል የመድሐኒት አይነት ነው። አርተሚሲኒን ከሌላ የወባ መድሐኒት ጋር በጣምራ ሲሰጥ የመፈወስ ኃይሉ ከፍተኛ ነው። ይኽም ካለፉት ዐሥር ዓመታት በላይ ዘላቂ ሆኖ ቆይቷል።»

ቻይናዊቷ ተመራማሪ በወባ የተጠቁ ሕፃናት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ምን እንደሚመስሉ በተደጋጋሚ ተመልክተዋል። እናም የትኛውንም መስዋዕት ያስከፍል ለእነዚህ ሕፃናት ፈውስ የሚሆን መድሐኒት ሳያገኙ እንቅልፍ እሰደማይወስዳቸው ለራሳቸው ቃል በመግባት ጥረት ማድረጋቸው ተገልጧል።

አዲሱን የወባ መድሐኒት ያገኙት ቻይናዊቷ ዩዩ ቱ
አዲሱን የወባ መድሐኒት ያገኙት ቻይናዊቷ ዩዩ ቱምስል Imago/W. Chengyun

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 ዓ.ም. አዲሶቹ ሣይንቲስቶች በእንግሊዝኛው (The New Scientist) ታዋቂ የሣይንስ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ «ከምንም በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ለሥራዬ ነው። ያም በመሆኑ የግል ሕይወቴንም ቢሆን መስዋዕት ለማድረግ ቆርጬ ነበር» ሲሉ ነበር የተናገሩት። በእርግጥም ተመራማሪዋ የወባ መድሐኒቱን ለማግኘት የአራት ዓመት ሕፃን ልጃቸውን ለጠባቂ በመስጠት ረዥም ጊዜያቸውን በቤተ-ሙከራ እስከማሳለፍ ደርሰውም ነበር።

ወባ በዓለማችን እጅግ ገዳይ ከሚባሉ የበሽታ አንይነቶች አንዱ ነው። እጎአ በ2013 ብቻ ወደ 600 ሺህ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። አብዛኞቹ የወባ ሰለባዎች አፍሪቃውያን ናቸው።

ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ በሚገኘው በርንሃርድ ኖኅት የመድሐኒት ምርምር ተቋም ተመራማሪው ዩኡርገን ማይ የአርተሚሲኒን መገኘት ጠቀሜታው ላቅ ያለ እንደሆነ ገልጠዋል።

«በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ወባን ለመከላከል ተመራጩ መድሐኒት አርተሚሲኒን ነው። ባለፉት ዓመታት ወባን በመከላከል የተገኘው ስኬት ያለ አርተሚስኒን የማይታሰብ በሆነ ነበር።»

በቻይናዊቷ ሣይንቲስት የተገኘው አዲሱ የወባ መድሐኒት ብቻውን ወባን ያጠፋል ማለት እንዳልሆነ በርንሃርድ ገልጠዋል። ይልቁንስ የአርተሚሲኒን ዋሽነቱ ከሌሎች መድሐኒቶች ጋር ተጣምሮ ሲሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።

በእርግጥ አዲሱ የወባ መድሐኒት ወባን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ቢኖረውም በአንዳንድ አካባቢዎች መድሐኒቱን የሚቋቋሙ ተሐዋስያን ተገኝተዋል። ለአብነት ያህል በደቡብ እስያ በሚገኙ ሃገራት፤ በታይላንድ፣ ሚያንማር፣ ካምቦዲያ እና ላዖስ ድንበሮች አዲሱን የወባ መድሐኒት የሚቋቋሙ ተሐዋስያን መገኘታቸው ተጠቅሷል።

የወጻ በሽታ በተለይ በአፍሪቃ ሚሊዮኖችን ጨርሷል።
የወጻ በሽታ በተለይ በአፍሪቃ ሚሊዮኖችን ጨርሷል።ምስል picture-alliance/dpa

«አዎን፤ ትንሽ ቅር የሚለው መድሐኒቱን የሚቋቋሙ ተሐዋሲያን መገኘታቸው ነው። በደቡብ እስያ የሚገኙ ሃገራት፣ የዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መድሐኒቱን የሚቋቋሙት ተሐዋሲያን ከተጠቀሱት አካባቢዎች አልፈው እንዳይሄዱ ጥረት እያደረጉ ነው። ምናልባትም ወባን በአካባቢዎቹ በመከላከል ማጥፋትም ይቻል ይሆናል። ያኔም መድሐኒት መቋቋም የሚችሉት ተሐዋስያን ባሉበት ይወሰናሉ። እንዲያም ሆኖ ግን በሌሎች ክፍላተ ዓለም በተለይም መድሐኒቱ እጅግ አስፈላጊ በሆነባት አፍሪቃ አርተሚስኒን ከሌሎች መድሐኒቶች ጋር በጣምራ መሰጠቱ ውጤቱ እጅግ ከፍተኛ ነው።»

የኖቤል ተሸላሚው ጃፓናዊው ሳቶሺ ኦሙራ
የኖቤል ተሸላሚው ጃፓናዊው ሳቶሺ ኦሙራምስል Getty Images/Y.Shimbun

በዚህም አለ በዚያ ግን እነዚህ አርተሚስኒን መድሐኒትን መቋቋም የሚችሉት ተሐዋስያን ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመቱ ባለቡት ማጥፋት ያስፈልጋል ተብሏል።ቻይናዊቷ ተመራማሪን ለኖቤል ሽልማት ያበቃው አዲሱ አርተሚስኒን የወባ መድሐኒት በማንኛውም መንገድ ለብቻው መሰጠት እንደሌለበትም ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

በሕክምናው ዘርፍ የኖቤል ሽልማቱን ገሚስ ያሸነፉት ዊልያምሲካምፕቤልእና ሳቶሺኦሙ ያገኙት መድሐኒት በቆላማ አካባቢዎች የሚከሰቱ በሽታዎችን የሚፈውስ መሆኑ ተገልጧል። መድሐኒቱ ዐይነ-ማዝ፣ እንዲሁም እጅ እና እግርን እጅግ የሚያገዝፈው በተለምዶ «ዝሆኔ» የሚባለው በሽታን ሊያድን ይችላል ተብሏል። በቆላማ አካባቢዎች የሚከሰቱት እነዚህ በሽታዎች በታዳጊ ሃገራት የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠቃሉ። በሽታዎቹ የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች በመባልም ይጠራሉ። እነዚህ በሽታዎች የሚፈውሰው መድሐኒት አቬርሜስቲን እንደሚባል ታውቋል።

የወባ መድሐኒት ያገኙት ቻያናዊቷ ሣይንቲስትን ጨምሮ ሦስቱ ተመራማሪዎች በሕክምና ላደረጉት የላቀ አስተዋጽዖ በጋራ 855,000 ዩሮተሸልመዋል። በኖቤል የሽልማት አሰጣጥ ደንብ መሰረት ከየዘርፉ ለሽልማት የሚመረጡ ተሸላሚዎች እያንዳንዳቸው ስምንት ሚሊዮን የስዊድን ክሮነር ማለትም 855,000 ዩሮ ያገኛሉ። በአንድ የሽልማት ዘርፍ ከአንድ በላይ ተሸላሚ ካለ ገንዘቡ ለአሸናፊዎቹ ይከፋፈፈላል።

የኖቤል ሽልማት የተቋቋመው በስዊድናዊው በጎ አድራጊ እና ሣይንቲስት አልፍሬድ ኖቤል ፍላጎት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1895 ነበር። የመጀመሪያው ስነሥርዓት ከ6 ዓመታት በኋላ በ1901 ተከናውኗል። የዘንድሮ የሣይንስ ዘርፍ የኖቤል ኮሚቴ የሚመራው በሴቶች ነው።በ የአንድ ቀን ልዩነት የሚበሰረው ሽልማት በሕክምና ጀምሮ፣ በፊዚክስ፣ ከዚያም ኬሚስትሪ ወይንም ሥነ-ቅመማ፣ ስነ-ጽሑፍ፣ ብሎም የሠላም ኖቤል ዘርፍ ድረስ ዘልቆ በኢኮኖሚ ዘርፍ ሽልማት በመስጠት ይጠናቀቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ