ዓባይ: የግብጽ እና የኢትዮጵያ ንትርክ
ሰኞ፣ ሰኔ 10 2005
ግብፅን ለመጉዳት የሚፈልግ ማንም አፍሪቃዊ ሀገር የለም ያሉት የዩጋንዳው መሪ፤ ሙሴቬኒ፣ ግብፅ ጥቁር አፍሪቃን መጉዳቷን መቀጠል አትችልም፤ የአሁኖቹ የግብፅ መሪዎችም ከዚያ በፊት የነበሩት ፣ መሪዎች የሠሩአቸውን ስህተቶች ሊደግሙ አይገባም ሲሉ ምክር መለገሣቸው ተመልክቷል።
«ከግብፅ የሚሠነዘሩ መግለጫዎችን፤ በጋዜጦች ተመልክቼአለሁ።የሚበረታታውን የኢትዮጵያን ሥራ--ወይም ለኤሌክትሪክ ማመንጫ የሚሆነውን የግድብ ሥራ በተመለከተ ማለት ነው--። መላው አፍሪቃም እንዲህ ዓይነት ተግባር ነው ማከናወን የሚኖርበት ። አንድ የሚታይ ውጤት፣--የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ፣ በባለሁለት አኀዝ መጠን በማደግ ላይ ነው የሚገኘው። ስለዚህ ይጠቅማል ብለን የምንመክረው፤ አዲሱ የግብፅ መንግሥትና አንዳንድ በዚያው በግብፅ የሚገኙ ትምክሕተኛ ቡድኖች፣ ያለፉት የግብፅ መንግሥታት የሠሩአቸውን ስህተቶች እንዳይደግሙ ነው።»
የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት፤ ስሜታዊነትን ወደ ጎን በመተው በሠከነ አእምሮ መነጋገር፣ መወያየት እንደሚበጅ ከመጠቆማቸውም፤ ከጥቁር አፍሪቃ አንዳች ጉዳት ደርሶባት የማታውቀው ግብፅ፤ እርሷ ጥቁር አፍሪቃን መጉዳቷን ከአንግዲህ መቀጠል አትችልም ሲሉም አስገንዝበዋል።
««ስለዚህ ምክራችን፤ ከግብፅ የሚሠነዘሩት ትምክህተኛ መግለጫዎች እንዲቆሙና በዐባይ ወንዝ ተፋሰስ አገሮች ድርጅት በኩል ፣ በስሜት ሳይሆን በሰከነ አመለካከት መነጋገር፤ ውይይቶችንም ማካሄድ ተገቢ ነው።
ግብፅን መጉዳት የሚፈልግ አፍሪቃዊ የለም። እናም ፣ ግብፅ፣ ጥቁር አፍሪቃንና በምድር ሠቅ አካባቢ የሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራትን መጉዳቷን መቀጠል አትችልም።»
ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የጀመረችዉ የግድብ ግንባታ፤ የውኃ ፍሰቱን የሚቀንስ ከሆነ ግብፅ በሁሉም አማራጮች እንደምትጠቀም ያሰማቸውን ማስጠንቀቂያ ኢትዮጵያ « የሥነ አዕምሮአዊ ጦርነት » ስትል በማጣጣል፣ በሚሰነዘርባት ማንኛውም ርምጃ አንፃር ራስዋን እንደምትከላከል በማስታወቅ የግድቡን ግንባታ ለአፍታ እንኳ እንደማታቋርጥ ገልጻለች። የሁለቱ ሀገራት እሰጣ ገባ እስከምን ይሆን?መፍትሄዉስ? በስዊድን የሚገኘዉ ዘጋብያችን ቴዎድሮስ ምህረቱ በስቶክሆልም በዓለም አቀፍ የዉሃ ተቋም ጠበብት የሆኑት አንቶን እርልን አነጋግሮ ዘገባ ልኮልናል
ቴዎድሮስ ምህረቱ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ