1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓመፅ በሱዳን፥ስጋት በኬንያ፤ ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ መስከረም 18 2006

በሱዳን የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ዓመፅ ካርቱምን አልፎ መላ ሱዳንን አዳርሷል፤ ቢያንስ 30 ሰዎች ተገድለዋል። በኬንያ መዲና አሸባሪዎች ካደረሱት ጥቃት ወዲህ በነዋሪዎቹ በተለይም «ትንሿ ሞቃዲሾ» በሚባለው የናይሮቢ ሰፈር የሚኖሩ ሶማሌያውያን በስጋት ተውተውጠዋል። ከጥቃቱ ጀርባ በርካታ አወዛጋቢ ነገሮች መነሳት ጀምረዋል። ትኩረት በአፍሪቃ ይቃኛቸዋል።

https://p.dw.com/p/19pul
ምስል Reuters

ዓመፅ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምና በመላ ሀገሪቱ

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዖመር ኧል በሽር
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዖመር ኧል በሽርምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

የሚትጎለጎል ጥቁር ዳመና የሱዳን መዲና ካርቱምን ውጧታል። የቤንዚን ማደያዎች በእሣት ተያይዘው እየተንቀለቀሉ ነው። እዚህም እዚያም በየጎዳናዎቹ የመኪና ጎማዎች ይነዳሉ፤ የፀጥታ ኃይላት እንዳይጠጓቸው ለማድረግ በተቃውሞ ሰልፈኞቹ የተለኮሱ ናቸው። ፕሬዚዳንት ዖመር ኧል በሽር ባሳለፍነው እሁድ የወሰዱትን የቁጠባ ርምጃ በመቃወም ድንገተኛው ዓመፅ ዳግም መላ ሱዳንን አዳርሷል።

«ምጣኔ ሀብታችን ላይ የተጋረጠው ችግር ሶሥት ምክንያቶች አሉት። ወደ ሃገር የምናስገባው ወደ ውጭ ከምንልከው ይልቃል። ለፍጆታ የምናውለው ከምናመርተው በላይ ነው። የገንዘብ ሚንሥትር ከሚያስገባው የሚያወጣው በዝቶበታል። በርካቶች ለነዳጅ ፍጆታ ይሰጥ የነበረው ድጎማ መሰረዙ ድሆችን እንደሚጫን ይገልፃሉ። መርሳት የሌለባቸው ጉዳይ ግን በእርግጥም ጫናውን በድሆች ላይ እንዲጠነክር ያደረገው የምጣኔ ሀብቱ ቀውስ ነው። »


የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዖመር ኧል በሽር ነበሩ በአንድ የውይይት መድረክ ላይ የተናገሩት። ይህ ንግግራቸው ግን ሕዝቡን ከማረጋጋት ይልቅ አስቆጥቶ መዘዝ ነው የጠራባቸው። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን የቤንዚን ዋጋ በእጥፍ ማሻቀቡን፣ የመጓጓዣ ክፍያ መናሩን እንዲሁም ያንን ተከትሎ የዕለታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መጨመርን በመቃወም አደባባይ መዋል ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል።

በርካቶች የሱዳን መንግሥት ኅብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እየፈጠረ በሚያጋብሰው ገንዘብ ተቀናቃኞቹን ለሚወጋበት የጦር ሰራዊት ማደራጃ ያውላል ሲሉ ይነቅፋሉ። የዲሞክራሲ ተሟጋች አምጋድ ፋሪድ።

«የሱዳን ህዝብ በመላ፤ የዚህን ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ውሳኔዎችና የኅይል እርምጃውን ይቃወማል። መንግሥት የተቃውሞውን ወገን ለመጨቆንና ጦርነት ለማካሄድ ብዙ ገንዘብ ያወጣል። ይህን ትቶ ለምን ለህዝቡ ቤንዚንና መባልእት አያቀርብም?»

በሱዳን የዲሞክራሲ ታጋዮች፤ ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በፊት በዓረቡ ዓለም መቀጣጠል የጀመረው የፀደይ አብዮት ሱዳንም ደርሶ የረዥም ዘመን ገዢው የዖመር ኧል በሽር መንግሥትንም ማጋሉ አይቀርም የሚል ምኞት ሰንቀው ነበር። ሆኖም የኧል በሽር የፀጥታ ኃይላት በተቃውሞ ሠልፈኞች ላይ በወሰዷቸው ጠንካራ ርምጃዎች የተነሳ የዲሞክራሲ አቀንቃኞቹ ምኞት ሳይሳካ ቀርቷል። የሕዝባዊ ምክር ቤት ፓርቲ አባል ባሽር አደም ራሕማ የሚያክሉት ነገር አላቸው።

«መንግሥት ችግር ተጋርጦበታል፤ በጀቱ ክፉኛ ተናግቷል፤ የሚፈልገው ገንዘብ እየቦጠቦጠ የመንግሥት እና የባሽር ፓርቲ ወጪዎችን ብቻ መሸፈን ነው። ከእዚያ ባሻገር መንግሥት በዳርፉር፣ ደቡብ ኮርዶፋን እና በነጭ አባይ ግዛቶች ለሚመራው ጦርነት በርካታ ገንዘብ ያስፈልገዋል።»

በሣምንቱ መጀመሪያ ላይ በሱዳን ተቃውሞው ከተቀሰቀሰበት ቅፅበት አንስቶ በበርካታ የዓረቡ ሃገራት የተለመደ መፈክር በማስተጋባት ላይ ነው። «ሕዝቡ የመንግሥቱን መወገድ ይሻል» ሲሉ ሱዳናውያን በየአደባባዩ ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ናቸው። «ነፃነት፣ ሠላም እና ፍትኅ፤ ሕዝቡ ዓብዮት ይሻል!» የሚሉ መፍክሮች በጎረቤት ሀገር የሱዳን መዲና ካርቱም ውስጥ በተደጋጋሚ እያስተጋባ ነው። በሱዳን ኦምዱርማን ትናንትናም ከአርቡ ፀሎት በኋላ ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎች አደባባይ ወጥተው «ነፃነት፣ ነፃነት» ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል። ፖሊስ በወቅቱ ሰልፈኞቹን በአስለቃሽ ጢስ ለመበተን መሞከሩም ተዘግቧል።


ስጋት የዋጣት የኬንያ መዲና፤ ናይሮቢ

ዓመፅ በሱዳን
ዓመፅ በሱዳንምስል picture-alliance/dpa
ለናይሮቢ ጥቃት ሠለቦች መታሰቢያ
ለናይሮቢ ጥቃት ሠለቦች መታሰቢያምስል Reuters

ባሳለፍነው ሳምንት በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሰፊ የገበያ አዳራሽ አሸባሪዎች ጥቃት ካደረሱ በኋላ በርካቶች አሁንም ድረስ በስጋት ተውጠዋል። ከሶማሌ በተነሱ አሸባሪዎቹ በደረሰው ጥቃት ቢያንስ 70 ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል። የሶማሌው ኧል ሸባብ በኬንያውያን ላይ ሽብር የመንዛቱን ያህል ከደሙ ንፁህ የሆኑ ሠላማዊ ሶማሌያውያን ናይሮቢ ውስጥ በፍርሀት ተሸብበው ይገኛሉ።

ወደ ዌስት ጌት የገበያ ማዕከል የሚያቀናው ጎዳና አሁን ለተሽከርካሪዎች ክፍት ሆኗል። ላለፉት ቀናት ይህ መንገድ ተዘግቶ ነበር። አሁን ተዘግቶ የቆየው ዋናው መገንጠያ ብቻ ነው። ጥይት መከላከያ ልዩ ሠደሪያ አድርገው ወደ ገበያ አዳራሹ የሚገቡትን እና የሚወጡትን አንዳንድ ወንዶች እና ሴቶች እንቅስቃሴ ለመቃኘት የጓጉ አላፊ አግዳሚዎች ከርቀት ቆመዋል።

የሀገር ውስጥና የውጭ ሃገራት የአሻራ ባለሙያዎች ፍንጭ ፍለጋ
የሀገር ውስጥና የውጭ ሃገራት የአሻራ ባለሙያዎች ፍንጭ ፍለጋምስል Reuters

የጀርመን የወንጀል ምርመራ ጽ/ቤት በናይሮቢ የተከሰተውን ፍንዳታ ለሚያጠናው የኬንያው ቡድን ርዳታ ለማድረግ የፈንጂ አምካኝ ባለሙያዎቹን ልኳል። ከፍንዳታው በኋላ በርካታ ጥያቄዎች ማብቂያ የለሽ ጥያቄዎችን አጭረዋል።

«ከረዥም ጊዜ አንስቶ የታቀደበት ሳይሆን አይቀርም። መንግስት ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ቀደም ያለ መረጃ ሳይደርሰው እንዳልቀረ ጭምችምታዎች እየተሰሙ ነው። ሆኖም ያ ትክክል እንደሆነ ምንም ማረጋገጫ የለኝም።»

ሲል አንድ የጎዳና ሸቃጭ በከተማው የሚሰማውን ጭምጭምታ ተናግሯል። መላው የከተማው ነዋሪዎች አሸባሪዎቹ ጥቃቱን ለመፈፀም ምንያህል ሊዘጋጁበት እንደቻሉ እየተነጋገረበት ነው። ፈንጂዎች ቀደም ብሎ በገበያ አዳራሹ ውስጥ ሳይከማቹ አልቀረም ተብሏል። አንዳንድ ጋዜጦች የደኅንነት ሰዎች ጉቦ ሳይቀበሉ አይቀሩም ሲሉ ጥርጣሬያቸውን አሰምተዋል። በበርካታ የጥቃቱ ሠለባ ቤተሰቦች ዘንድ ሀዘን የመግባቱን ያህል አሁን ቀስ እያለ በኬንያውያን ዘንድ ቁጣ አለያም ጥላቻ እየተቀሰቀሰ ነው። ብዙዎች ምናልባትም ለዳግመኛ ጥቃት ናይሮቢ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የሶማሌያውያን ሰፈር ሴራ እየተጎነጎነባቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል።


በመዲናዋ አንደኛው ክፍል የሚገኘው ኢስሊ የተሰኘው ሰፈር ውስጥ በርካታ ሶማሌያውያን ስለሚኖሩ ሰፈሩ «ትንሿ ሞቃዲሾ» እየተባለም ይጠራል። በሶማሌ የሚገኙ እስልምና አክራሪ ቡድኖችን በመፍራት ሸሽተው የመጡ ሶማሌያውያን እርስ በእርስ በተያያዙ ቤቶችና በተቀጣጠሉ ታዛዎች ስር ተጠልለው ይገኛሉ። ይሁንና የኧል ሸባብ ታጣቂዎች በገበያ አዳራሹ ውስጥ ጥቃት ለመፈፀም ተዘጋጅተው እንደነበር አስቀድመው የሚያውቁ እና ቡድኑን የሚደግፉ ሶማሌያውያንም እዚሁ ሰፈር ውስጥ መሽገው እንደሚኖሩ ይነገራል።

Karte Afrikanische Union AMISON Einsatz

ከጥቂት ወራት አስቀድሞ ኬንያ ውስጥ በተደረገው የምርጫ ዘመቻ ይህን «ትንሿ ሞቃዲሾ» የተሰኘውን ሰፈር የማስወገድ ዕቅድ የምርጫ ቅስቀሳ ሆኖ ቀርቦ ነበር። እናም አሁን የሰፈሩ ነዋሪዎች የቁጣ ሰለባ እንዳይሆኑ ሰግተዋል።

«ሁኔታው አስጨናቂ ነው። ጥቃት ፈፃሚዎቹ ሙስሊሞች እንደሆኑ ተናግረዋል። ስለእዚህ ፖሊስ ወደ ኢስሊ መጥቶ በርካቶችን ማሰሩ አይቀርም። ፈርቻለሁ።»

«ጥቃቱ ዘግንኖኛል። ፖሊሶች ኧል ሸባብን ይደግፋሉ ሲሉ እኛን ነው ጥፋተኞች የሚያደርጉን። ግን እነሱ ይሄን ሁሉ ጭካኔ እየፈጠሩ ሙስሊሞች አይባሉም ። ያ ከእስልምና ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።»


አንዳንድ ተንታኞች ከናይሮቢው ጥቃት ጀርባ የሚገኙ አክራሪዎች በመዲናዋ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ከእንግዲህ በጥርጣሬ እየተያዩ እንዲኖሩ ለረዥም ጊዜ ሳያቅዱበት አልቀሩም ይላሉ። ወጣት ሶማሊያውያን ሙስሊሞች ከሚደርስባቸው ጫና አኳያ በቀላሉ ወደ ኧል ሸባብ ሊገቡ ይችላሉ ሲሉም ስጋታቸውን ይገልፃሉ። የኬንያው ጥቃት እስልምና አክራሪዎቹ ምን ያህል በዓለም አቀፍ ደረጃ መረባቸው የዘረጉ እንደሆነ ጠቋሚ ነው ተብሏል።

እንደ ኬንያ የደኅንነት ሰዎች ከሆነ ከሽብር ጥቃት ፈፃሚዎቹ መካከል የአሜሪካን ዜግነት ያለው ግለሰብ እና አንዲት እንግሊዛዊት ሴትም እንደሚገኙበት አስታውቀዋል። በኢስሊ የሚኖሩ በርካታ ሶማሌያውያን ለጥቃቱ ሰለቦች የተሰማቸውን ሀዘን ለመግለፅና ከተጎጂ ቤተሰቦች ጎን መቆማቸውን ለማሳየት ባለፉት ቀናት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። እናም ልክ እንደ ተቀሩት ኬንያውያን እና መላው ዓለም ሁሉ እነሱም በጥቃቱ እጅግ መደንገጣቸውንና ማዘናቸውን ለማሳየት ይፈልጋሉ። ከእዚያም ባሻገር ከሶማሌያ የመጡ ሙስሊሞች በአጠቃላይ አሸባሪዎች አለመሆናቸውን ግልፅ በማድረግም እራሳቸውን ለመጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ