1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም በ2012

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2005

ሐምሌ ላይ የደቡብ ኮሪያዉ ድምፃዊ ያዜማት ሙዚቃ ከኮሪያ ልሳነ-ምድር ታልፋለች ብሎ ያኔ የገመተ ጥቂት ነበር።ባመቱ ማብቂያ ግን የዓለም ወጣት እንደ ብሔራዊ መዝሙሩ እያዜመ አዲሱን ዓመት ሊቀበል ዳንኪራ ይረግጥበታል።

https://p.dw.com/p/17BkF
Fireworks explode over and around the Sydney Harbour Bridge and Sydney Opera House during new year celebrations January 1, 2013. More than 1.5 million people were expected to line the foreshores of the harbour to watch the annual new year fireworks show. REUTERS/David Gray (AUSTRALIA - Tags: SOCIETY)
ሲድኒ 2013ን ተቀበለችምስል Reuters



አፍቃኒስታኖች፣ ፓኪስታኖች ሙታቸዉን ቀብረዉ፣ መሞቻ፣ መቀበሪያ፣ መሸሸጊያቸዉን ለአስራ-አንደኛ ዓመት ያሰላሰሉበት፣ኢራቆች እልቂት ጥፋትን የየዕለት ኑሯቸዉ አካል ያደረጉበት ዘጠነኛ ዓመት፣ ሶሪያዎች በዕልቂት ፍጅት ጥፋት ከቀዳሚዎቻቸዉ ለመቅደም የተጣደፉበት፣ ሊቢያ፣ የመን እና ናይጄሪያ ሶማሌዎችን ቀድመዉ፣ ቀዳሚዎችን የተከተሉበት ሁለተኛ ዓመት አበቃ።ግብፆች እየመረጡ፣ አደባባይን ሙጥኝ እንዳሉ፣ እስራኤል-ፍልስጤሞች እንደተገዳደሉ፣ አሜሪካኖች፣ ሩሲያዎች ቻይኖች እንደየፖለቲካቸዉ ወግ መሪዎቻቸዉን መርጠዉ ወይም ተመርጦላቸዉ፣ ዘንድሮን አምና ሊሉት ሠዓታት ቀራቸዉ።ከአዉሮጳ በመለስ ባለዉ ዓለም የተከናወኑ አበይት ክንዉኖችን ላፍታ ቃኝተን-እኛም ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለትን እንሸኘዉ።

ሚያዚያ ሁለት ሺሕ ሰወስት ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ እንደ ፊት አዉራሪ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር እንደ አጋፋሪ፣ ኢራቅ ላይ የለኮሱትን እቶን ግመት የአረቦች ሕዝባዊ አብዮት፣ የሶሪያ አዲስ ጥፋት ሊጋርዱት መሞከራቸዉ አልቀረም።

እስከ ነገ-ዘንድሮ የምንለዉ ዓመትም እንደ ስምንት ቀዳሚዎቹ ሁሉ ያቺ ጥንታዊቱ ሐብታም ሐገር የቦምብ ማሳ፣ የሞት-እልቂት አዝመራ፣ የአስከሬን መከመሪነቷን ያረጋገጠዉ ገና በመባቻዉ ነበር።

የመርከብ ሽርሽር የሚያዘዉትረዉ ሐገር ጎብኚ ኮስታ ኮንኮርዲያ የተባለችዉ መርከብ ኢጣሊያ ባሕር ላይ በመላተሟ የሞቱ የቆሰሉ ተንሸራሻሪዎችን ቁጥር ከሚቆጥሩለት መገናኛ ዜዴዎች አይን-ጆሮዉን እንደለገተ፣ከወደ አሜሪካ በተለይ ለሙዚቃ አፍቃሪዎች መርዶ ተሰማ።

ኤታ ጀምስ።ድንቅ ድምፃዊት ነበረች።አረፈች።ሰባ አራት ዓመቷ ነበር።ጥር አስራ-ሰወስት።

በኮስታ ኮንኮሪያ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር-አንድ ሁለት ሲባል፥ ሙታኑን ቀብሮ፣ ቁስለኞቹን ቆጥሮ እንዳለቀሰ፣ እየሞተ-የሚለቀስለት ኢራቃዊ ባስራ ላይ ተረኛ ሟች ቆስለኞችን አስቆጠረ።

አንድ አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳዉ ቦምብ ሐምሳ ሰወስት ሰዎች ተገደሉ።መቶ ሰላሳ ቆሰለ።

የአዉሮጳ ሕብረት፥ የኑክሌር ቦምብ ለመስራት ታሴራለች ከሚላን ኢራን ነዳጅ ዘይት ላለመግዛት ወሰነ።ጥር ሃያ-ሰወስት።ጥር ሃያ አምስት ካኑ የተባለችዉን የሰሜናዊ ናጄሪያን ግዛትን በተከታታይ ያሸበረዉ ቦምብ አንድ መቶ ሰማንያ አምስት ሰዉ ገደለ።አደጋዉን የጣለዉ ቦኩ ሐራም የተሰኘዉ ቡድን ነዉ ተብሎ ይታመናል።


ናጄሪያዊዉ አክራሪ ድርጅት የደረጀበት፣ ናጄሪያን በነ-ኢራቅ፥ በእነ-አፍቃኒስታን የጥፋት ጎዳና ለማጓዝ የፈለገበት ምክንያት አሳማኝ መረጃ ሳይገኝለት ጥር-አበቃ።ሁለት ሺሕ አስራ አንድን በሰልፍ፣ ምርጫ፣ ሸኝቶ ዘንድሮን በሰልፍ ምርጫ ለተቀበለዉ ግብፃዊ የካቲት የባተዉ ከመጥፎ ምልኪ ጋር ነበር።

የካቲት አንድ፣የሁለት እግር ኳስ ቡድናትን ግጥሚያ ለመመልከት ፖርት ሰኢድ ስታዲዮም የገባዉ የየቡድናቱ ደጋፊ ጎራ ለይቶ ይከታከት ገባ።ግብ ከሚቆጠር፣ ኳስ ከሚለቀምበት ሜዳ ሰባ-ዘጠኝ አስከሬን ተለቀመ።ቁስለኛዉ አንድ ሺሕ።

ሁለት የአዉስትሬሊያ ግዛቶችን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ አምስት ሰዉ ገድሎ በአስር ሺሕ የሚቆጠሩትን መግቢያ መዉጪያ አሳጥቶ ሲያስጨንቅ፣ ማዕከላዊ ፊሊፒንስን የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ አርባ-ስምንት ሰዉ ገደለ።በሺ የሚቆጠር አፈናቀለ።የካቲት ስድስት ነበር።

የካቲት አስራ-አንድ።ዩናይትድ ስቴትስ ሌላ መርዶ።ድምፃዊትና የፊልም ተዋኝ ዊትኒ ሁዊስተን ሞተች።

ተስረቅራቂ ድምፅ፥ አማላይ ዉበት አፈር ሆነ።አርባ ዘጠኝ አመቷ ነበር።አካዶ በተባለዉ የሜክሲኮ ከተማ በሚገኝ ወሕኒ ቤት የታሰሩ የሁለት ተፃራሪ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድናት አባላት ተጋጭተዉ አርባ-አራት እስረኞች የመገደላቸዉ ዜና ማዕከላዊ አሜሪካኖችን ጉድ-አሰኝቶ ሳያበቃ-የሁንዱራስ ወሕኒ ቤትን ያጋየ እሳት የሰወስት መቶ ስልሳ እስረኞች ሕይወት የመብላቱ አሳዛኝ ጉድ የሜክሲኮዉን ጉድ ዋጠዉ።


በሕዝባዊ አመፅ ከስልጣን የተወገዱትን የየመንን ፕሬዝዳት ዓሊ አብደላ ሳሌሕን የተኩት ምክትል ፕሬዝዳት አብድ ራቡሕ መንሱር አል-ሐዲ ለፕሬዝዳንትነት ምርጫ ብቻቸዉን ተወዳድሩ-አሸነፉም።የየመን አል-ቃኢዳ ለአዲሱ የሐሪቱ ፕሬዝዳንት ያስተላለፈዉ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ነበር።ቦምብ።


የካቲት ሃያ-አምስት።ሙካላ በተባለችዉ ከተማ የፈነዳዉ ቦምብ ሃያ-ስድስት ሰዉ ገደለ።ለቦምብ-ማ ማን እንደ ኢራቅ።አስራ-ሁለት የኢራቅ ከተሞች ባንድ ቀን፣ በተመሳሳይ ሰዓት እኩል ተሸበሩ።የሞተ፧ ስልሳ። የቆሰለ ሁለት መቶ።የካቲት ሃያ-ሰወስት።


መጋቢት ሁለት፣ኢንዲያና እና ኬንታኪ የተባሉትን የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች የመታዉ ሐይለኛ ማዕበል ሃያ-ሰባት ሰዉ ገደለ።ኮንጎ ሪፐብሊክ ርዕሠ-ከተማ ብራዛቪል ዉስጥ የጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘን የደረሰ ተከታታይ ፍንዳታ ሁለት መቶ ሐምሳ ሰዉ ገደለ።

ኮንጎዎች የከሰለ-አስከሬናቸዉን ሲለቅሙ ሩሲያዎች ፕሬዝዳንታቸዉን መረጡ።መጋቢት አራት።ከሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ጀምረዉ ሲሆንላቸዉ በፕሬዝዳንትነት፥ ሳይሆንላቸዉ በጠቅላይ ሚንስትርነት ከዓለም የምድር ገፅ አንድ-ሰባተኛዉን የምትይዘዉን ሰፊ፣የተፈጥሮ ሐብታም፣የጦር መሳሪያ ጉልበታም ሐገርን የመሩት ቭላድሚር ፑቲን እንደገና በፕሬዝዳትነት ተመረጡ።

የፑቲንን ዳግም መመረጥን፣ የምርጫዉ ሥርዓት፣ የድምፅ አሰጣጡን ሒደትና ዉጤት ተቃዋሚዎች በአደባባይ ሰልፍ ተቃዉመዉታል።


ምዕራባዉያን መንግሥታት ፈራተባ ባለ መግለጫ ተችተዉታል።ፑቲኒንን ግን አንዱም የሚያስጨንቅ አልሆነም።ግንቦት ሰባት፥- ክሬምሊንን እንደ ፕሬዝዳት ዳግም ተቆጣጠሩት።


እንደገና ኢራቅ፣ እንደ ገና ግድያ።ሐዲታ በተባለች ከተማ የሰፈሩ ፀጥታ አስከባሪዎችን የፖሊስ መለዮ ለብሶ የተቀየጠ አንድ ታጣቂ ሃያ-ሰባት ወታደሮችን ረሸነ።መጋቢት አምስት።እዚሕም እዚያም አራት-አምስት ሰዎች ከመገደላቸዉ ባለፍ የከፋ ግድያ-ጥፋት ሳይደርባት ጥርና የካቲትን ያለፈችዉ አፍቃኒስታን መጋቢት ላይ ደም-ጠጥቶ ደም ለሚጠማዉ ቆሌዋ አስራ-ስድስት ሰላማዊ ዜጎችዋን ገበረች።

ገዳዮች የአፍቃኒስታንን ሕዝብ «ከአሸባሪዎች ነፃ ለማዉጣት» የዘመቱት የአሜሪካ ወታደሮች ናቸዉ። መጋቢት አስራ-አንድ።በአምስተኛዉ ቀን የቱርክ ወታደሮች የሚያበሩት የኔቶ ሔሊኮብተር ካቡል አጠገብ መኖሪያ ቤቶች ላይ ተፈጥፍጦ አስር-ሰዎች ገደለ።ለአፍቃኒስታን ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት እንደ አስር ቀዳሚዎቹ ሁሉ አስከሬን እንዳስቆጠረ-ተጠናቀቀ።

የፕሬዝዳንት በሽር አል-አሰድን አገዛዝን በሰላማዊ ሕዝባዊ አብዮት ለመቃወም አምና መጋቢት የጀመሪያዉን የአደባባይ ሰልፍ ካደረገዉ የሆምስ ሕዝብ፥ ትግል የጀመረበትን የመጀመሪያ ዓመት ለመዘከር የታደለዉን ሥንትነት ማወቅ ሲበዛ ከባድ ነዉ።


ሕዝባዊዉ፣ ሰላማዊዉ ትግል ብልጭ ከማለቱ በጠመንጃ ዉጊያ በመዳፈኑ ጥፋት ቀድመዉ ከጠፉት አካባቢዎችና ሕዝብ አንዱ ግን በርግጥ ሰላማዊዉ ትግል ቀደሞ የተጀመረባትና የጀመሩት ሆምስና ሆምሶች ናቸዉ።


ሆምሶች የጀመሩት ትግል መጋቢት ላይ ዓመት ሲደፍን ከሶሪያዎች ዓልፎ፣ ዓለምን ለሁለት ገምሶ ዲፕሎማሲያዊ ድርድርን ከዉጊያ፣ ሽብርን-ከሽምገላ፣ ሰላም የማስከበር ዘመቻን ተፋላሚዎችን ከማሰልጠን-ማስታጠቅ ጋር በቀየጠ ተቃርኖ የሚያፋትገዉ የሶሪያ ምስቅልቅል፥ ከሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብ መግደሉ፣ አስር ሺዎች ማቁሰሉ፣ መቶ ሺሕዎች ማፈናቀል-ማሰደዱ ይዘገብ ነበር።

እልቂት ፍጅት ጥፋቱ፣ የዉጪዉ ሽኩቻዉም ከመጋቢት በሕዋላ እስካሁን በተቆጠሩት ምናልባትም በሚቀጥሉትም-የመቀጠሉ አሳዛኝ ምልክት የታየዉም ሆምስ ነበር።መጋቢት አስራ-ሁለት።የሶሪያ መንግሥት ጦር አርባ አምስት የሆምስ ነዋሪዎች መግደሉን ተቃዋሚዎች አስታወቁ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ላሕዳር ብራሒሚ ባለፈዉ ቅዳሜም ሰላማዊ መፍትሔ አሉ።


«ብቸኛዉ አማራጭ በእዉነት ገሐነብ ወይም ፖለቲካዊ ሒደት ከሆነ፥ እኛ ሁላችንም ለፖለቲካዊ ሒደት ያለ ዕረፍት መጣር ይገባናል።በጣም ከባድ ነዉ።በጣም የተወሳሰበ ነዉ።ግን ሌላ ምርጫ የለም።»

ቱርክን፣ አረቦችንና አዉሮጶችን አስከትላ አማፂያኑን የምትረዳዉ ዩናይትድ ስቴትስ ግን ሌላ ምርጫ አላት።በሽር አል-አሰድ መወገድ አለባቸዉ የሚል።ወደ በሽር አል-አሰድ የምታዘነብለዉ ሩሲያ ኢራንን በተዘዋዋሪ ከሩቁ አስከትላ፣ ቻይናን ከጎንዋ አቁማ የአሜሪካኖቹን ጎራ ትሞግታለች።

የደማስቆ ገዢዎችና አማፂያኑ ግን ይዋጋሉ።ሶሪያ ትጠፋለች።ሕዝባ ያልቃል።አማፂያኑ ባለፈዉ ቅዳሜ ብቻ ሁለት መቶ የመንግሥት ምርኮኛ ወታደሮችን ጨምሮ ሰወስት መቶ ሰዉ መግደላቸዉ ተዘግቧል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ እስካሁን ከአርባ ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።፣ ከሁለት መቶ ሺሕ በላይ ቆስሏል።ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተሰዷል።አራት ሚሊዮን ተፈናቅሏል።

የጠፋዉ ሐብት ንብረት በአስር ቢሊዮን ይገመታል።የጥንታዊቱ ሐገር በገንዘብ የማይተመኑ ቅርሶች ወድመዋል።እና----እንደገና ኢራቅ-እንደገና ሞት።አስር የኢራቅ ከተሞችን ባሸበረ የቦምብ ጥቃት ሐምሳ ሰዎች ተገደሉ።ሁለት መቶ አርባ ቆሰሉ።መጋቢት ሃያ ነበር።


የጓቲማላ ፍርድ ቤት በሺሕ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሁለት በተፈፀመ ጭፍጨፋ ተሳትፈዋል ያላቸዉን አምስት የቀድሞ የሐገሪቱ ሚሊሺያ ጦር ባልደረቦችን የሰባት ሺሕ ሰባት መቶ አስር ዓመታት እስራት ፈረደባቸዉ።ቀልድ ይመስላል።ግን እዉነት ነዉ።


መጋቢት ሃያ-ሁለት።የማሊ የጦር መኮንኖች የፕሬዝዳት አማዱ ቶማኒ ቶሬን መንግሥት ከሥልጣን አስወገዱ።እስልምና ሐይማኖትንና የቱዋሬግ ጎሳ ጥያቄን የተላበሰዉ ዉጊያ ጦርነት ታሪካዊቱ የሳሕል በረሐ ሐገርን ማጥፋቱም ተባባሰ።የምስራቅ አፍሪቃ ሐገራት ሶማሊያ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት ወደ ማሊ ጦር ለማዝመት ይዘጋጁ ገቡ።የቀድሞዉ
ሶማሊያ ፕሬዝዳት ግን ይሕን ሳያዩ አረፉ ተገላገሉ።

ኮሎኔል አብዱላሒ ዩሱፍ አሕመድ።ዚያድ ባሬ ሲደሰቱ እየሾሙ፥ እየሸለሟቸዉ፥ ሲከፉ እያሰሯቸዉ፥ ኮሎኔል መንግሥቱ ደስ ሲላቸዉ እያቀረቡ፥ እየረዱ-እየደገፏቸዉ፥ ሲቆጡ እያሰሯቸዉ፥ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሲፈልጓቸዉ እያሸሙ፥ ሳይፈልጓቸዉ እያሻሯቸዉ ነዉ-የኖሩት።የኢትዮጵያንም የሶማሊያንም አብያተ-መንግሥታት፥ ወሕኒ ቤቶችንም እኩል ያዉቋቸዉ ነበር።

ሰባ ስምት አመታቸዉ ነበር።ቀኑ-መጋቢት ሃያ-ሰወስት።የአብዱላሒ ዘመድ-ወዳጆች ሐዘን (ታእዚያ) እንደተቀመጡ የሞቃዲሾ ቲአትር በቦምብ ጋየ።የሶማሊያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳትን፥የሐገሪቱን የእግር ኳስ ፌደሬሽን መሪን ጨምሮ አስር-ሰዉ ተገደለ።ሚያዚም አራት አለ።

ሚያዚያ ሰባት፥ የቦምብ፥ ጥይት፥ ጥፋት ያልተለያት ፓኪስታን ተፈጥሮም-ጨከነባት።አንድ መቶ ሰላሳ ወታደሮችዋ በበቦረዶ ናዳ ተቀበሩ።በሁለተኛዉ ሳምንት ኢስላማባድ አጠገብ የመንገደኞች አዉሮፕላን ተፈጥፍጦ አንድ መቶ ሃያ-ሰባት ሰዎች ሞቱ።

የዓለም ወዝ አደሮች-ዓመታዊ ቀናቸዉን ሲያከብሩ፥ ለወትሮዉ በዓሉን ከማንም በላይ የሚያከብሩት የሞስኮና የቤጂንግ መሪዎች እንደ ካፒታሊስቱ ፈሊጥ የአስራ-አምስት ቢሊዮን ዶላር የንግድ ዉል ተፈራረሙ።

ግንቦት ሰባት ዓለም የቭላድሚር ፑቲንን በዓለ-ሲመት ከሞስኮ ሲከታተል፥ አፍቃኒስታን የሠፈረዉ የኔቶ የጦር አዉሮፕላን በጣለዉ ቦምብ አስራ-አራት ሠላማዊ ሰዎች ገደለ።ስድስት አቆሰለ።

ግንቦት አስራ-ሁለት።የጥንታዉያኑ የማያ ነገድ አዋቂዎች የቀመሩት የዘመን መቁጠሪያ ታሕሳስ ሃያ-አንድ፥ ሁለት ሺሕ አስራ ሁለት የአሮጌዉ ዘመን ማብቂያ፥ የአዲስ ዘመን መጀመሪያ እንጂ የዓለም ፍፃሜ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ መረጃ ተገኘ።

ታሕሳስ ሃያ-አንድ ምፅዓት፥ ቂያማ ወይም ፍፃሜ ነዉ በማለታቸዉ ጥሩ ገበያ ያገኙበት ወገኖች ግን አልተቀበሉትም። ፊልም፥ ሟርታቸዉን እንደቸበቸቡ ወሩ በወር ተተክቶ ታሕሳስ-ሃያ አንድ መጥቶ ሔደ።ዓለም እንደነበረች ነች።

ግንቦት አስራ-ሰባት።


ዶና ሰመር።አሜሪካዊቷ ድምፃዊት ሞተች።ስልሳ-አራት አመቷ ነበር።

ኢራቅ፥ የመን፥ ናጄሪያ በአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ፥ ፓኪስታን በደፈጣ ተዋጊዎች ጥቃት፥ አፍቃኒስታን በኔቶ ጦር ድንደባም፥ በቦምብ፥ ሶሪያ በአማፂያንና በመንግሥት ጦር ዉጊያ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎቻቸዉን ቀብረዉን፥ ሌሎችን ወደ ሚቀብሩበት ሌላ ወር ተሻገሩ።ሰኔ።ናጄሪያ።የአዉሮፕላን አደጋ መቶ ሐምሳ ሁለት ሰዉ ገደለ።

ባግዳድ፥አዲስ ወር፥ አዲስ ፍንዳታ፥ አሮጌ-እልቂት።ኢራቅ ለሰኔ ቆሌ ወሩ መግቢያ ላይ የሃያ-ስድስት፥ አጋማሹ ላይ የዘጠና ሰወስት፥ ማብቂያዉ ላይ የስላሳ-ሁለት፥ ዜጎቿን፥ሕይወት፥ የስድስት መቶ ሰዎቿን አካል ገበረች።አፍቃኒስታንም እንዲያዉ ነዉ።በተከታታይ የቦምብ ጥቃት አምስት የዉጪ ሐገር ሰዎችን ጨምሮ አርባ-አንድ ተገደሉባት።መቶዎች ቆሰሉ።ናጄሪያ ደግሞ በጥይት፥-ሃያ ሰወስት ሰዉ ተገደለ።

የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ደጋፊና ተቃዋሚ ጎሳ ታጣቂዎች ከቃዛፊ መገደል በሕዋላ ከፍተኛ ዉጊያ ያደረጉበት ወር ነበር።ሰኔ ሃያ-ብቻ አንድ መቶ አምስት ሰዎች ተገደሉ።ለግብፆች ግን ወሩ የዓመት ከመንፈቅ ትግላቸዉ ሁለተኛ ድል የታየበት ነበር።

በግብፅ የረጅም ጊዜ ታሪክ ፖለቲከኞች ለመሪነት ተወዳድረዉ ሕዝብ በድምፁ የሚፈልገዉን መረጠ።ሰኔ ሃያ-አራት።

የቀድሞዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አባል ዶክተር መሐመድ ሙርሲ በሚመሩት መንግሥት ሁሉም ግብፃዊ እንደሚወከል ቃል ገብተዉ ነበር።

ቃል-ተስፋዉ ግን ዳር አልዘለቀም።ወይም ተቀባይ አላገኘም።ፕሬዝዳት ሙርሲ በሙባረክ ዘመን የተሸሙ ጠቅላይ አቃቤ ሕግን በአምባሳደርነት መሾማቸዉ፥ የሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሥልጠን መቀነሳቸዉን፥ ከሁሉም በላይ ባለፈዉ ሳምንት የፀደቀዉን ሕገ-መንግሥት ረቂቅን በመቃወምና በመደገፍ ሰበብ-የግብፅ ሕዝብ ካደባባይ ሰልፍ ሳይለይ-ድምፁን እንደሰጠ አመቱ ተጠቃለለ።

ሰኔ-ሰላሳ።የዩናይትድ ስቴትስ ምሥራቃዊ የባሕር ጠረፍ ግዛቶችን የመታዉ አዉሎ ንፋስ-አስራ አምስት ሰዉ ገደለ።ማዕበሉ በተለይ የኤሌክትሪክ መስመሮችን በመበጣጠሱ፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኦሐዮ፥ የቨርጂኒያ፥ የሜሪላንድ እና የዲስትሪክት ኦቭ ኮሎምቢያ አካባቢዎች በቀን ጨለማ ተዋጡ።

ጥንት የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በአሸባሪነት የወነጀሏቸዉ፥ኋላ አሜሪካኖች የሚያደንቁ የሚደግፏቸዉ፥ እስራኤሎች እንደመሪ የሚያከብሯቸዉ፥ ፍልስጤሞች እንደ ጨካኝ የሚጠሏቸዉ፥ ከ1970ዎቹ ወዲሕ የካይሮ ገዢዎች እንደ ሰላም አርበኛ የሚያመወድሷቸዉ አንድ እስራኤላዊ ፖለቲከኛ ነበሩ።ይትሳቅ ሻሚር የሚባሉ።ድሮ እንግሊዞች ኢትዮጵያ ወይም ኤርትራ አስረዋቸዉ የነበሩ፥ ኋላ በኢትዮጵያዉያን አይሁዶች ዘንድ አጥብቀዉ የሚወደዱ ቁመተ አጭር፥ ደፋር ፖለቲከኛ መሪም ነበሩ።ብዙ እንዳወዛገቡ ብዙ ነረዋል።ዘጠና ሰባት አመት።ሰኔ-ሰላሳ ግን ሞቱ።

ሐምሌ ግም ከማለቱ ሕንድ፥ ባንግላዴሽ፥ ጃፓና፥ ቻይናን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ ብዙ መቶዎቹን ገድሎ፥ ብዙ ሺዎችን አፈናቅሎ-ሲጋመስ፥ ሩሲያንም በዉሐ እጁ አረጣጠባት።እና መቶ አርባ ሰዉ ገደለባት።የእስራኤል ሐገር ጎብኚዎችን አሳፍሮ ቡልገርስ ከተሰኘዉ የቡልጋሪያ አዉሮፕላን ማረፊያ ወደ ከተማ ይጓዝ የነበረ አዉቶቡስ በቦምብ ጋይቶ ስድስት እስራኤላዉን ተገደሉ።ሰላሳ ቆሰሉ። ሐምሌ-አስራ-ስምት።

ሰሜን ኮሪያ ለቀድሞ ገዢዋ ሞት ያጠለቀችዉን የሐዘን ማቅ-ለአዲሱ መሪዋ ሹመት ፌስታ አዉልቃ ቦረቀች።የሟቹ ታላቅ መሪ የኪም ጆንግ ኢል ልጅ፥ ኪም ጆንግ ኡን በማርሻል ማዕረግ የሐገሪቱ ላዕላይ መሪነትን ሥልጣን በይፋ ተረከቡ።የሃያ-ስምንት ዓመት ወጣት ናቸዉ።ሐምሌ አስራ-ስምት።

ፒዮንግ-ዮንግ በሹመት ሽልማት በተንበሸበሸች በሳምንቱ ገሚስ ሐገሪቱን ያጥለቀቀለዉ ጎርፍ ሰማንያ-ስምት ሰዉ ገደለ።ስድስት ሺሕ አፈናቀለ።

ከኢራቅ፥ ከአፍቃኒስታን፥ ከፓኪስታን፥ ከሶሪያ፥ ከየመን፥ ከናጄሪያ፥ ከማሊ፥ ከሊቢያ የእልቂት ፍጅት፥ ከሕንድ-እስከ ፊሊፒንስ፥ ከቻይና እስከ ኮሪያ፥ ከጃፓን እስከ ኢንዶኔዥያ፥ ከኔፓል እስከ ቬትናም ከደረሰዉ የተፈጥሮ መቅሰፍት፥ ከአሜሪካኖች የምርጫ ዘመቻ-ፋታ ዓለም ገለል ቀለል፥ ዘና የሚበልበት ድግስ አገኘ።ሐምሌ ሐያ-ሰባት።የበጋ የኦሎምፒክ ዉድድሮች በይፋ ተጀመረ።

«እንኳን ወደ ለንደን በደሕና መጣችሁ።»

አሉ የአዘጋጆቹ መሪ።

«የለንደን ዉድድሮች መጀመሩን አዉጃለሁ።»

ዳግማዊት ንግሥት ኤሊዛቤት።

ዉድድሩ ነሐሴ-አስራ ሁለት ተዘጋ።ኢትዮጵያዉያን በመሪያቸዉ፥ በርዕሠ ሊቃነጳጳሳታቸዉ ሞት ሐዘን ላይ ናቸዉ።ሰኔ ሃያ-አምስት።አሜሪካኖች ጨረቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በረገጠዉ እዉቅ ጠፈረተኛቸዉ ሞት ኢትዮጵያዉያንን መሠለ።ሰኔ ሃያ-አምስት።ኒል አርምስትሮግ ሞቱ።ሰባ-ሁለት ዓመታቸዉ ነበር።

አሜሪካ የሚኖር አንድ ግብፃዊ የሙስሊሞችን ነብይ የሚያንቋሽሽ ፊልም ማሳራጨቱ ያስቆጣዉ ሙስሊም የዓለም ርዕሠ-ከተሞችን በቁጣ እንዳተከተከ ነሐሴ-ተራዉን ለመስከረም ለቀቀ።መስከረም አስራ አንድ።አሜሪካኖች በሁለት ሺሕ አስንድ፥ ኒዮርክና ዋሽንግተን ላይ በአሸባሪዎች የተገደሉባቸዉን ዜጎቻቸዉን ሲዘክሩ፥ በመላዉ ዓለም የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የተለያዩ ጥቃቶች ዒላማ ሆነዉ፥ ወይም ከጥቃቱ ለማምለጥ ተከርችመዉ ዋሉ።

የቤንጋዚ-ሊቢያዉ ጥቃት ግን ለአሜሪካ ፖለቲከኞች ታላቅ ዉርደት ለፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መስተዳድር ደግሞ ሐያል ፈተና ነበር።የኤምባሲዉን ቅጥር ግቢ ያጋዩት ታጣቂዎች የአሜሪካዉን አምባሳደር ጄ. ክርስቶፈር ስቴቫንስን ጨምሮ አራት ዲፕሎማቶችን ገደሉ።

ሕይወት ግን ቀጠለች።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤም ተጀመረ።ሶማሌዎች አዲስ መሪ ሥለተመረጠላቸዉ በደስታ-ዓመቱን አጋምሰዉ መስከረምን ሲያሰሉ፥ በምሥራቅ አፍሪቃ ጦር የሚደገፈዉ የመንግስታቸዉ ጦር ሐምሳ የአሽባብ ደፈጣ ተዋጊዎችን መግደሉን አበሰረ-ወይም አረዳቸዉ።

ፓኪስታን፥-ካራቺና ላሆር የሚገኙ ሁለት ፋብሪካዎችን ያጋየዉ ቃጠሎ ሰወስት መቶ አርባ ሰዎችን ገደለ።የፋብሪካ ቃጠሎ ብዙ የባንግላዴሽ ዜጎችንም ገድላል። ከካቡል፥ ከባግዳድ፥ ከደማስቆ፥ከሌጎስ፥ ከሰነዓ ከሽብር-ጦርነት፥ ከሞት-ስደት ሌላ ሌላ ነገር ሳይሰማ መስከረም አበቃ።

ጃፓንና የቻይና በአንዲት ደሴት ይገባኛል ሰበብ የገጠሙት ዉዝግብ እንደናረ የባተዉ ጥቅምት የዩናይትድ ስቴትስ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የምርጫ ዘመቻ ይጋጋምበት ያዘ።ናጄሪያ የሃያ-የኮሌጅ ተማሪዎቿ ሕይወት ለታጣቂዎች የደም ጥማት ገብራ-የተቀበለችዉን ጥቅምት-የተሰናበተችዉ በቦምብ ፍንዳታ፥ በታጣቂዎችና በፀጥታ አስከባሪዎች ግጭት ከመቶ በላይ ዜጎችዋ ተገድለዉባት ነዉ።

ከጥቅምት፥-ሃያ አራት እስከ እስከ ሰላሳ የካረቢክ ሐገራትን፥ በሐማስን፥ ዩናይትድ ስቴትስንና ካናዳን የመታዉ ዉሽንፍር አዘል ማዕበል ሁለት መቶ ዘጠኝ ሰዉ ገደሎ፥ ብዙ ሺዎችን አፈናቅሎ፥ ሃያ ቢሊዮን ዶላር የተገመተ ንብረት አዉድሞ ወሩ ሲያበቃ-ገርገብ አለ።

የተፈጥሮዉ መቅሰፍት ረገብ ሲል፥ የአሜሪካ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች የምርጫ-ዘመቻ ሙግት ፉክክር ግን ጋመ።

አገረ ገዢ ሚት ሮምኒ።

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ።የአሜሪካ ሕዝብ ሕዳር ስድስት ድምፅ ሰጠ።ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ አሸነፉ።

የአረብ ሕዝባዊ አብዮትን ሒደት ዉጤት፥ የሶሪያዉን ጦርነት በቅርብ ርቀት ሲከታተሉ የቆዩት የእስራኤልና የፍልስጤም ፖለቲከኞች ደም ላስለመዱት ምድር ደም ሳያፈሱበት ዓመቱን ሊሰናበቱ አልፈለጉም።ሕዳር አስራ-አራት። እስራኤል ጓዳ ሠራሽ ሮኬቶች ተኮሱብኝ ያለቻቸዉን የሐማስ ደፈጣ ተዋጊዎችን ለማጥፋት ጋዛ ሠርጥ ላይ ዘመተች።

በሳምንቱ ተኩስ አቁም ተባለ።የእስራኤሉ የዓለም ምርጥ ጦር ጓዳ ሰራሽ ሮኬት ከታጠቀዉ ከሐማስ ሚሊሺያ ጋር ባደረገዉ ዉጊያ አሸናፊ ተሸናፊዉ አለየም።አንድ መቶ ስልሳ ፍልስጤሞች መገደላቸዉ፥ አንድ ሺሕ ያሕል መቁሰላቸዉ ግን እዉነት ነዉ።እስራኤሎች አራት ተገድሎባቸዋል። ሁለት መቶ አስራ-ዘጠኝ ቆስሎባቸዋል።

ለፍልስጤሞቹ ፕሬዝዳት ለማሕሙድ አባስ ግን ሕዳር የዲፕሎማሲ ድል የተመዘገበበት ወር ነበር።ሕዳር ሐያ ዘጠኝ-ኒዮርክ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ።በአብላጫ ድምፅ ፍልስጤምን ሐገር ያልሆነች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አደረጋት።ፍልስጤሞች የጋዛ ሐዘን-እንባቸዉን በኒዮኩ ዉሳኔ ፌስታ ተለቃለቁት።


ታሕሳስ። ዓመቱ ሊጠናቀቅ ዕለታት ሲቀሩት ብዙ ጋዜጠኝችንና የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎችን በማስገደል አቻ የሌለዉ ዓመት መሆኑ ተመሠከረ።በባለሙያ ጋዜጠኞች ግድያ ሶማሊያ አንደኛ ናት።አስራ-ስምት ጋዜጠኞች ተገድለዉባታል።በኢንተርኔት ዘጋቢዎች፥ በመገናኛ ዘዴዎች በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ሞት ግን አንደኝነቱን ሶሪያ ያለተቀናቃኝ ይዛዋለች።በድምሩ ስልሳ አምስት።ፓኪስታን አስር ጋዜጠኞች ተገድለዉባት-ሰወስተኛ ወጥታለች።

ዓመቱ የጊኒ ቢሳዉ፥ የማላዊ፥ የጋና፥ የኢትዮጵያ፥ መሪዎች ሞተዉበታል።የቬንዙዌላዉ ፕሬዝዳት ሁጎ ሻቬዝ ለዳግም መሪነት ተመርጠዉበት ግን በተቃራኒዉ አሁን ባመቱ ማብቂያ ታማዉ እያጣጠሩበት።

ሐምሌ ላይ የደቡብ ኮሪያዉ ድምፃዊ ያዜማት ሙዚቃ ከኮሪያ ልሳነ-ምድር ታልፋለች ብሎ ያኔ የገመተ ጥቂት ነበር።ባመቱ ማብቂያ ግን የዓለም ወጣት እንደ ብሔራዊ መዝሙሩ እያዜመ አዲሱን ዓመት ሊቀበል ዳንኪራ ይረግጥበታል።


ዘመን ለምትለዉጡ መልካም አዲስ ዓመት።

epa03505507 YEARENDER 2012 NOVEMBER Smoke rises after an Israeli air strike on an allegerd Hamas site in the south east of Gaza City, Gaza Strip, 17 November 2012. Israel has put 75,000 reservists on standby amid speculation of an impending ground invasion. EPA/MOHAMMED SABER +++(c) dpa - Bildfunk+++
ጋዛ ስትንድምስል picture-alliance/dpa
Palestinian President Mahmoud Abbas holds his hands to his face as U.S. President Barack Obama speaks during the 66th session of the General Assembly at United Nations headquarters Wednesday, Sept. 21, 2011. (Foto:Seth Wenig/AP/dapd)
አባስ-ተመድ ጉባኤምስል dapd
Egyptians hold posters supporting Omar Suleiman, Egypt's vice president in late January, during a rally in support of the ruling supreme council of the armed forces, SCAF, at Abbasiya Square, in Cairo, Egypt, Friday, Dec. 2, 2011. Islamists appear to have taken a strong majority of seats in the first round of Egypt's first parliamentary vote since Hosni Mubarak's ouster, a trend that if confirmed would give religious parties a popular mandate in the struggle to win control from the ruling military and ultimately reshape a key U.S. ally. Arabic read " We demand Suleiman to candidae for Presidency" , "dignity better than food", " Soleiman : Egypt in danger" . (Foto:Amr Nabil/AP/dapd)
ግብፅ-ምርጫምስል dapd
epa03203709 An Egyptian anti-riot soldier (C) gestures towards anti-military protesters during clashes at Abbassiya square, Cairo, Egypt, 02 May 2012. Media reports quoting medical sources state that at least nine people were killed in clashes between anti-military protesters and unknown attackers near the Defence Ministry in Cairo. Dozens of people were also injured in the clashes, which erupted when the assailants, whom the opposition called pro-government thugs, cracked down on the protesters. EPA/KHALED ELFIQI +++(c) dpa - Bildfunk+++
ግብፅ-ግርግርምስል picture-alliance/dpa
U.S. President Barack Obama and his family walk onstage during his election night victory rally in Chicago, November 6, 2012. (L-R) Daughters Malia, Sasha, First lady Michelle Obama and the President. REUTERS/Jason Reed (UNITED STATES - Tags: POLITICS ELECTIONS USA PRESIDENTIAL ELECTION)
ኦባማ-ከድል በኋላምስል REUTERS
Republican presidential nominee Mitt Romney waves before delivering his concession speech during his election night rally in Boston, Massachusetts, November 6, 2012.during his election night rally in Boston, Massachusetts November 7, 2012. REUTERS/Mike Segar (UNITED STATES - Tags: POLITICS ELECTIONS USA PRESIDENTIAL ELECTION)
አገረ ገዢ ራምኒምስል REUTERS
Titel: Al Mutanbi Straße in Bagdad Beschreibung: Denkmal von arabischen Dichter al Mutanbi Alle Bilder sind von DW Korrespondent in Bagdad (Munaf al-saidy), · wurden in 2012 aufgenommen, · wurden im Irak aufgenommen, · sind von DW honoriert, · Der Korrespondent (Munaf al-saidy) hat uns versichert, dass alle Bilder von ihm stammen. · Der Korrespondent (Munaf al-saidy) übernimmt daher die Verantwortung für alle Bilder. · Der Korrespondent (Munaf al-saidy) hat die Bilder mit verschiedenen Kameras aufgenommen.
ባግዳድምስል DW/M. Al-Saidy
Source News Feed: EMEA Picture Service ,Germany Picture Service Syria's President Bashar al-Assad (R) meets International peace envoy for Syria Lakhdar Brahimi in Damascus December 24, 2012 in this handout photograph released by Syria's national news agency SANA. Brahimi met with Assad in Damascus on Monday to discuss a solution to the country's 21-month-old conflict. Brahimi told journalists after the meeting that he discussed the situation in Syria overall and gave his views on how to solve the crisis. He said conditions in the country were still poor. REUTERS/Sana (SYRIA - Tags: POLITICS CIVIL UNREST) FOR EDITORIAL USE ONLY. NOT FOR SALE FOR MARKETING OR ADVERTISING CAMPAIGNS. THIS IMAGE HAS BEEN SUPPLIED BY A THIRD PARTY. IT IS DISTRIBUTED, EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS
ብራሂሚና አሰድምስል Reuters
©Christophe Petit Tesson/MAXPPP - 08/01/2012 ; AL MALIKIYE / DERIK AL MALIKIYE / DERIK ; SYRIA SYRIA - Le PYD, la branche syrienne du mouvement autonomiste Kurde PKK controle certaines villes a majorite kurde du nord est de la Syrie. Ici une manifestation dans la ville de Al Malikiye, renomme de son nom Kurde Derik, en soutien au dirigeant historique APO Abdullah Ocalan emprisonne en Turquie . PYD, Syrian branch of Kurdish autonomist movement PKK demonstrates in the street of Al Malikiye / Derik northern city of Syria to support their leader APO Abdula Ocalan on August 29, 2012. Le PYD, la branche syrienne du mouvement autonomiste Kurde PKK controle certaines villes a majorite kurde du nord est de la Syrie. Ici dans la ville de Al Malikiye, renommee de son nom Kurde Derik, les militants du PYD manifestent en soutien au dirigeant historique APO Abdullah Ocalan emprisonne en Turquie . PYD, Syrian branch of Kurdish autonomist movement PKK demonstrates in the street of Al Malikiye / Derik northern city of Syria to support their leader APO Abdullah Ocalan on August 29, 2012. *** Local Caption ***
ሶሪያምስል picture-alliance/dpa

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ













































































ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ