1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ውኃ የምትጠማው «የውኃ ማማ»-ኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ መጋቢት 13 2009

የምሥራቅ አፍሪቃ «የውኃ ማማ» እየተባለች የምትቆላመጠው ኢትዮጵያ እንደገና በድርቅ ትፈተን ይዛለች። የአገሪቱ የውኃ ሐብት ጊዜ እየቆጠረ የሚጫናትን የድርቅ እና የረሐብ ሥጋት ለመቋቋም አይበቃ ይሆን?

https://p.dw.com/p/2ZkXZ
Bildergalerie Ausstellung River Tales. Fotografische Narrative entlang des Nils
ምስል Brook Zerai Mengistu

ውሐ የምትጠማው «የውሐ ማማ»-ኢትዮጵያ


የኤል-ኒኞ የአየር ጠባይ ለውጥ ካስከተለው ድርቅ ያላገገመችው ኢትዮጵያ እንደገና የላ ኒኛ ሥጋት አጥልቶባታል። የቀንድ ከብት ሞት እና የውኃ እጥረት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መከሰታቸው ተሰምቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ መረጃ እንደሚጠቁመው 5.2 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ። 1.2 ሚሊዮን ሕጻናት፤ እመጫት እና ነፍሰ-ጡር እናቶች ተጨማሪ ምግብ ያሻቸዋል። 9.2 ሚሊዮን ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውኃ እጥረት ይገጥማቸዋል። ሌሎች 2.4 ሚሊዮን ቤተሰቦች ለቤት እንስሶቻቸው ድጋፍ ይጠብቃሉ። 300,000 ሕጻናት የተመጣጠነ ምግብ እጦት ይገጥማቸዋል። ከጎርጎሮሳዊው 2015-16 ባለው አንድ አመት በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ተከታታይ የእርሻ ሥራ አስተጓጉሏል። ሰብላቸው የወደመባቸው 10 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ ፈላጊ ሆነው ነበር። ድርቁ ጋብ ሲል የተከሰተው ከፍተኛ ዝናብ እና ጎርፍ የሰው ሕይወት አጥፍቷል። ከመኖሪያ ቀያቸውም አፈናቅሏል። በቀጣናው የአየር ጠባይ ላይ ለውጥ ያስከትላል የተባለለት ላ ኒኛ ለኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች እና ኑሯቸውን በተበጣጠሰ የእርሻ መሰረት ላይ ጥገኛ ላደረጉ ገበሬዎች ሥጋት ሆኗል። በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች 'የምሥራቅ አፍሪቃ የውሐ ማማ' ተብላ የምትቆላመጠው አገር ዜጎች እንደገና የድርቅ፤የመጠጥ ውሐ እና የግጦሽ ሳር እጦት ፈተና ከፊታቸው ተደቅኗል። 

Äthiopien Dürre Trockenheit
ምስል picture-alliance/dpa/S. J. Sia

አቶ አለሙ የአሳና የውሐ ሐብት ጥናት ባለሙያ ናቸው። በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ከ30 በላይ አመታት በመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ያገለገሉት አቶ አለሙ የዘርፉ አማካሪ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። አቶ አለሙ የስቶክሆልም የአካባቢ ጥናት ተቋም እና የአፍሪቃ ልማት ፈንድ ያዘጋጁት 'የውሐ እና ድሕነት ግንኘነት'ን የፈተሸ ጥናት አማካሪ ነበሩ። 

ጥናቱ ኢትዮጵያ የታሪኳ መለያ የሆነውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችል የውሐ እና የመሬት ኃብት እንዳላት ያትታል። በዚሁ ጥናት መሰረት አገሪቱ በአመት በአማካኝ 850 ሚሊ ሜትር ዝናብ የምታገኝ ሲሆን 13 በመቶው 'ሰማያዊ ውሐ' ተብለው የሚጠሩትን ወንዞች እና ሐይቆች ይቀላቀላል። በዝናብ መልክ ከሚገኘው ውሐ 3 በመቶው ብቻ ዝናብ ላይ ጥገኛ  ለሆነው ግብርና አገልግሎት ይውላል። ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ ለግብርናው ዘርፍ የሚውለው የዝናብ እና የመስኖ ውሐ መጠን ከፍ ማለት ይኖርበታል ሲል ጥናቱ ኃሳብ አቅርቦ ነበር።  በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የምትጠቀመውን ውሐ በአራት እጥፍ አሊያም በአመት ከምታገኘው ዝናብ 10 በመቶውን መጠቀም አለባት ብሎም ነበር። ኢትዮጵያ ግን እንደታቀደው በምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች አንዱ የሆነው የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አልቻለችም። 
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የልማት አጋሮቹ ባለፉት ጥቂት አመታት የመስኖ ግድቦችን የመገንባት ፍላጎት አሳይተዋል። ዘጠኝ የመስኖ ግድቦች መገንባት የጀመረው የኢትዮጵያ መንግሥት ግንባታዎቹን በታቀደላቸው የጊዜ ሰሌዳ እና በተቀመጠላቸው የገንዘብ መጠን ማጠናቀቅ ሲሳነው እየታየ ነው። ርብ፤መገጭ፤ተንዳሆ እና የከሰም የመስኖ ግድብ ግንባታዎች ወደ 13 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ እንደተደረገባቸው መንግሥት አስታውቋል። ሌላው አጠያያቂ ጉዳይ ይኸን ያክል ተጨማሪ ገንዘብ የወጣባቸው ግድቦች ከታቀደላቸው የጊዜ ሰሌዳ በላይ አምስት አመታት ወስደው እንኳ አለመጠናቀቃቸው ነው። የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌትሪክ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ለግንባታዎቹ መጓተትም የወጪ መናር የመስኖ ግንባታ ጥናቶቹን ተጠያቂ አድርጎ ነበር። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ የግንባታ ሒደቱን የሚቆጣጠሩ አካላት የብቃት ጉድለት እንደነበርም ይናገራሉ።  ከመስኖ ግድቦቹ መካከል የጎንደር ወረዳ አርሶ አደሮች ሕይወት ይቀይራል የተባለለት የመገጭ የመስኖ ግድብ ስራ ብቻ ከተያዘለት በጀት በላይ 3 ቢሊዮን ብር አስፈልጎታል። በሰሜን ጐንደር ዞን ከአራት ዓመት በፊት በ2.4 ቢሊዮን ብር ግንባታው የተጀመረው የመገጭ የመስኖ ግድብ ስራ ሰላሳ ሶስት በመቶ ላይ ብቻ መሆኑን የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በየሳምንቱ የሚያሳትመው በኩር ጋዜጣ ታኅሳስ 24 ቀን 2009 ዓ.ም እትሙ አትቷል። አቶ ብዙነህ የተጓተቱትም ሆኑ አዲሶቹ እቅዶች በኢትዮጵያ መንግስት የእድገት እና የለውጥ ሁለተኛ እቅድ ዘመን ይጠናቀቃሉ ሲሉ ይናገራሉ። 

Ägypten Äthiopien Damm am Nil
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

ዋተር ኤድ በተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥልታዊ ተንታኝ የሆኑት ሔለን ፓርከር የውሐ ሐብትን በሚጋሩ ዘርፎች እንዲሁም የላይ እና ታች ተፋሰስ ነዋሪዎች/አገራት መካከል ጥርጣሬ የሚፈጥረው የአጠቃቀም ጉዳይ ትኩረት እንደሚያሻው ያምናሉ። የብሪታኒያው ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም የኢትዮጵያን የውሐ አስተዳደር የፈተሸበትን ዘገባ በትብብር ያሰናዱት የጥናት ባለሙያዋ አገሪቱ የውሐ ሐብት መረጃዋን በአግባቡ ማጥናት እና መሰነድ እንዳለባት ይመክራሉ። አቶ አለሙ አሰና በበኩላቸው የኢትዮጵያ የውሐ ሐብት ልማት እቅዶችም ሆነ ግንባታዎች ነባሩን ማኅበረሰባዊ እውቀት ገሸሽ ሊያደርጉ አይገባም የሚል እምነት አላቸው። አቶ አለሙ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ የሚደረጉት ሥራዎችም እንደ የአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ሊቃኙ እንደሚገባ ያስረዳሉ።


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ