1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዋናው የኧል ቓኢዳ ተወካይ በመቅዲሹ መገደላቸው፣

ሰኞ፣ ሰኔ 6 2003

እ ጎ አ በ 1998 ዓ ም፤ በናይሮቢና ዳሬሰላም ፤ በአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ ብርቱ አደጋ በመጣል 240 ሰዎች ህይወታቸውን ላጡበት የአሸባሪዎች ጥቃት፣ አቅድ በማውጣት መሪ ሚና እንደነበረው የተነገረለት፤

https://p.dw.com/p/RTHU
ምስል picture-alliance/dpa

በምሥራቅ አፍሪቃ ዋናው የኧል ቓኢዳ ተጠሪ፣ የኮሞሮው ተወላጅ ፋዙል አብዱላ ሙሐመድ በጥብቅ በመፈላግ ላይ ሳለ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሌሊት መገደሉ ታውቋል።

በተገደለበት አውቶሞቢል ውስጥ፤ በዛ ያሉ የእጅ ስልኮች፤ «ላፕ-ቶፕ ኮምፒዩተር»፤ በዛ ያለ ገንዘብ ፣ እጅግ ዘመናዊ ልዩ ገመድ፤ በሶማልያ የሌሉ እጅግ ዘመናዊ የእጅ ቦንቦች፣ ሰነዶች ፤ ካርታዎችና የቤተሰብ ፎቶግራፍም ተገኝቷል።

ፋዙል አብዱላ ሙሐመድ እንዴት ተገደለ? የእርሱ መሞት ለሶማልያ መንግሥትና ለአሸባብ የሚኖረው ትርጓሜ ምን ይሆን? ተክሌ የኋላ፤ በመቅዲሹ፣ የ AFP ዘጋቢና የDW ተባባሪ የሆነውን ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሃጂ አብዲኑርን አነጋግሯል።

ዕድሜው ወደ 40 የተጠጋ ፣ የ 5 ቋንቋዎች ተናጋሪ ፣ ቢያንስ ፣ በ 18 የተለያዩ ስሞች ይጠቀም እንደነበረ የተነገረለት ፋዙል አብደላ ሙሐመድ ፣ ወይም «ሐሩን» ፣ በናይሮቢና ዳሬሰላም ብቻ ሳይሆን፤ እ ጎ አ በ 2002 ዓ ም፤ በዚያው በኬንያ አንድ ሆቴል ላይም አደጋ እንዲጣል ያበቃና 15 ሰዎች እንዲገደሉ ያደረገ እርሱ መሆኑን፤ ምዕራባውያን ባለሥልጣናት ይናገራሉ። አንዳንድ የጸጥታ ጉዳይ ጠበብት እንደሚያምኑት ከሆነ ሐምሌ 4 ቀን 2002 ዓ ም፣ በደቡብ አፍሪቃ የተካሄደውን የዓለምን የእግር ኳስ ዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያ፣ በዩጋንዳ መዲና በካምፓላ በሁለት ቦታዎች ማለትም በአንድ የኢትዮጵያ ሬስቶራንትና ኪያዶንዶ ራግቢ ክለብ በተሰኘው ማዕከል ይከታተሉ በነበሩ ሰዎች ላይ አጥፍቶ ጠፊዎች አደጋ ጥለው 74 ሰዎች እንዲሞቱና 70 ያህል እንዲቆስሉ በተወሰደው የሽብር ተግባርም እጁን ሳያስገባ አልቀረም። ታዲያ እነዚህን የመሳሰሉ ብርቱ የሽብር ተግባሮችን ሲያቀነባብር የነበረውና በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ሰው ባለፈው ማክሰኞ ማታ በድንገት በሶማልያ ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጥይት ተርከፍክፎበት ህይወቱ አልፋለች።

ወደ መቅዲሹ ብቅ ብሎ፣ የሞት ፅዋ ከመቅመሱ በፊት በደቡብ ሶማልያ ኧል ቃኢዳን ያንቀሳቅስ ነበረ ተብሏል። ሰኔ 7 ቀን ሌሊት ምናልባት ያልጠበቀው ሁኔታ ነበረ የገጠመው። የሶማልያ የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎችም እንዲሁ! ሙስጠፋ ሃጂ አብዲኑር---

«ይህ የዕድል ውጤት ነው። የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎችን በዚያች ሌሊት የገጠማቸው ማለት ነው። አላወቁም ነበር። ከፍተኛ ሥልጣን ያለው የኧል ቓኢዳ መሪ በዚያ መንገድ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ላይ በመፈንቀ ሌሊት ይገኛል ብለው ፈጽሞ ያልጠበቁት ሁኔታ ነበር።»

ፋዙል አብዱላና ሾፌሩ፤ ሙስጠፋ የደረሰውን መረጃ ጠቅሶ እንዳስረዳው ከሆነ፣ከሆነ ከደቡብ ሶማልያ ተጉዘው መቅዲሹ እንደገቡ መንገድ ሳይስቱ አልቀሩም ። በመሆኑም ሳያስቡት የሶማልያ መንግሥት፣ ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ከሚቆጣጠሩት የተከተረ መንገድ ይደርሳሉ። ግዴታ ተሠማርተው የነበሩት ፀጥታ አስከባሪዎች፤ ፋዙል አብዱላ ሙሐመድና ረዳቱ ሾፌር ይጓዙባት የነበረችውን መኪና አስቆሙና፣ የሶማልያ ተወላጅ የሆነውን አሽከርካሪ መጠየቅ ይጀምራሉ፤ ሾፌሩም ቢሆን ከኧል ቓኢዳ ጋር ግንኙነት የመሠረተ የአክራሪ እስላማዊ ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበረ ተብሏል። በዚያ ቅጽበት ታዲያ ምን ተፈጠረ?

«የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎቹ፣ መኪና ያሽከረክሩ የነበሩትን ሁለት ሰዎችእንዲቆሙ ሲጠይቋቸው፤ እተሳሳተ መንገድ መግባታቸውን ተገነዘቡና ፋዙላ አብዱላ መሐመድና ሾፌራቸው፤ ለመተኮስ ሞከሩ፤ ሆኖም የፀጥታ አስከባሪዎቹ ኃይሎች፤ ቀደሙና ሩምታ ተኩስ ከፍተው በመኪናይቱ ላይ ጥይት ሲያርከፈክፉ፣ ሁለቱንም ሰዎች ውስጥ እንዳሉ ገድለዋቸዋል። »

ከዚያ በኋላም ነበረ፣ የኬንያን ባለሥልጣናትና የአሜሪካን የስለላ ጠበብት በመጠየቅ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት የተደረገው። በዘር የማንነት መለያ ምርመራም ፤ሟቹ በትክክል የተጠቀሰው ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ አዳጋች አልነበረም። የሚገርመው የሌላ ሰው ስም ይዞ ፣ አፍሪቃ ውስጥ ሳይታወቅ ካገር -አገር ሲዘዋወር መቆየቱ ነበረ።

«ፓስፖርቱ ላይ የሠፈረው ስም፣ ዳናኤል ሮቢንሰን --ይላል። የሶማልያ መንግሥት፤ ባለሥልጣናት እንዳሉት ፓስፖርቱ የተዘጋጀው ታንዛንያ ውስጥ ነው። ታዲያ ከደቡብ አፍሪቃ ለቆ የወጣው ፓስፖርቱ ላይ የተደረገው ምልክት እንደሚጠቁመው እ ጎ አ መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ ም ነው። ስለዚህም በዚሁ በተጠቀሰው ወር ነው ወደ ሶማላያ የመጣው። በመጋቢት---ከመጋቢት በኋላ 2011 !ስለዚህ እንደልቡ ይዘዋወር ነበረ ማለት ነው፤ በአፍሪቃ አገሮች የመዘዋወር ዕድሉ ነበረው። ምክንያቱም ማንም ፤ ምን እንደሚመስል የሚያውቅ አልነበረምና!»

ከአል ቃኢዳው መሪ ኦስማ ቢን ላደን መገደል በኋላ፤ በአፍሪቃ የኧል ቓኢዳ፤ ከፍተኛ ሹም መደገም ፤ አሁን ለአሸባብም ሆነ ለሶማልያ መንግሥት ያለው ትርጓሜ ምንድን ነው?

«ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው 10 የሶማልያ መንግሥት ወታደሮች ሳይገደሉ አልቀሩም። እርግጥ መንግሥት ገና ማረጋገጫ መግለጫ አልሰጠም ፤ እኛ ያገኘነው ዜና እንደሚለው፤ አሸባብ ፤ መቅዲሹ ውስጥ ቢያንስ 3 ዐበይት ጥቃቶችን አካሂዷል። አንደኛው ጥቃት፤ ለሀገር አስተዳደር ሚንስትሩ ኅልፈተ ህይወት ሰበብ ሆኗል። ስለዚህ፤ አሁንም ቢሆን አደጋ የመጣል አቅሙ አላቸው። እርግጥ ነው ለቡድኑ ትልቅ ጉዳት ነው። ፋዙል አብደላን የመሰለ ከፍተኛ ሹም ነውና ያጡት!»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ