1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዋሽንግተን-የአል-ቃኢዳ የሽብር ጥቃት ሥጋት

ዓርብ፣ ጳጉሜን 4 2003

«ኦስማ ቢን ላደን በተገደለበት ወቅት ከተሰበሰቡ የሥለላ መረጃዎች እንደተረዳነዉ አል-ቃኢዳ እንደ 9/11 ባሉ በታዋቂ ዕለታትና በዓላት ወቅት አደጋ ለመጣል ፍላጎት አለዉ።

https://p.dw.com/p/RktB

አለም-አቀፉ አሸባሪ ቡድን አል-ቃኢዳ ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች የተጠቃችበትን አስረኛ-ዓመት በምታስብበት በዚሕ ሰሞን ዳግም አደጋ ሊጥልባት ማቀዱን የሐገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ። የዩናይትድ ስቴትስ የሥለላና የፀጥታ ጉዳይ ባለሥልጣናት በየፊናቸዉ እንዳሉት አል-ቃኢዳ ሌላ አደጋ ለመጣል ማቀዱን የሚጠቁሙ መረጃዎች አሏቸዉ።የአሜሪካ ፌደራላዊ የምርመራ ቢሮ (FBI)የኒዮርክ ቅርንፍ ሐላፊ ጄኒስ ፌዳርችክ ትናንት ለጋዜጠኞች እንደነገሩት አል-ቃኢዳ በታዋቂ ዕለታትና በዓላት አደጋ ለመጣል እያሴሬ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ መስሪያ ቤታቸዉ ከደረሰዉ ቆይቷል።

«ኦስማ ቢን ላደን በተገደለበት ወቅት ከተሰበሰቡ የሥለላ መረጃዎች እንደተረዳነዉ አል-ቃኢዳ እንደ 9/11 ባሉ በታዋቂ ዕለታትና በዓላት ወቅት አደጋ ለመጣል ፍላጎት አለዉ።በዚሕ ሁኔታ፥ ዛሬ ማታ እዚሕ ሥለ ጉዳዩ ለመናገር በተሰባሰብንበት ሁኔታ ማለት ነዉ፥የአደጋ ሥጋት መኖሩን የሚጠቁም የተለየና ተጨባጭ ግን ያልተረጋገጠ መረጃ አለን።ሁል ጊዜ እንደምናደርገዉ የመስከረም አንዱ ጥቃት አስረኛ አመት እስከሚከበር ባለዉ ጊዜ ዉስጥ ተጨማሪ ዘገባ እንደሚኖረን አያጠራጥርም።»

ምክትል ፕሬዝዳት ጆ ባይደንም ይሕንኑ አረጋግጠዋል።ባይደን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት አል-ቃኢዳ የመስከረም አንዱ ጥቃት አስረኛ ዓመት በሚከበርበት ዕለት በተለይ በመኪና ላይ በተጠመዱ ቦምቦች አሜሪካን ለማሸበር ማቀዱ ተደርሶቦታል።ይሁንና ባይደን አክለዉ እንዳሉት የዉጪ አሸባሪዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመግባት ማቀዳቸዉን እንጂ መግባታቸዉን የሚጠቁም መረጃ የለም።ዩናይትድ ስቴትስ በአል-ቃኢዳ የተሸበረችበት አስረኛ አመት የፊታችን ዕሁድ ይከበራል።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ