ዋሽንት ተጫዋቹ ኤርሚያስ ናደው
ሐሙስ፣ ሐምሌ 24 2006ወጣት እና የአዲስ አበባ ከተማ ልጅ የሆነው ኤርሚያስ ናደዉ እንደቀልድ የተማረዉ ዋሽንት ጨዋታ ዛሬ መተዳደሪያዉ መሆኑን ይናገራል። ኤርሚያስ «ዋሽንት መጫዎቴ ለባህሌ ያለኝን ትኩረት አጠንክሮታል» ይላል።
የ25 ዓመቱ ኤርሚያስ እና ዋሽንት የተዋወቁት በአጋጣሚ ነበር። ከዛም ዋሽንት መጫወቱን ሊገፋበት ወሰነ። በወቅቱ የሚያውቀው የኪቦርድ መሣሪያ አስተማሪውን ነበርና ወደዛው አቀና። ትንሽም ስለ ዋሽንት ተማረ።
ኤርሚያስ ከዋሽንት ጋር ቢተዋወቅ እና ለመጫወት ቢሞክርም፤ የከተሜ ልጅ መሆኑ ብዙ ገፍቶ እንዲቀጥል መጀመሪያ ላይ እልድ አልሰጥ ብሎት እንደነበር ነው የሚናገረው።
አንዳንዶች ዋሽንት ይዞ ስለሚጫወት ልጅ ሲያስቡ፤ በአይምሮዋቸው ተፀርፆ የተቀመጠ አንድ ነገር አለ።ይህም አጠር ያለ ቁምጣ ያደረገ ፣ ጥላ ላይ አንድ ዛፍ ስር ተጠልሎ ከቀርቀሀ የተሰራ ዋሽንት የሚነፋ ሰው ነው። ስለሆነም ኤርሚያስ ከመድረክ ሲወርድ ግራ የሚጋቡ ተመልካቾች አይጠፉም። ከጊዜ ጋር ግን ምስሉ ብቻ ሳይሆን የዋሽንቱም አይነት ተቀይሯል።
ኤርሚያስ ስራዬ ብሎ ባይዘውም እንደ ሦስተኛ የሙዚቃ መሣሪያ ባህላዊ ክራርም ይሞክራል። ከሌሎች መሣሪያዎች ሁሉ ዋሽንትን የመረጠበትን ምክንያት አጫውቶናል።
ኤርሚያስ በባህል የምግብ አዳራሾች ብቻውን የሚጫወተውን ዋሽንት ለጊዜው በCD መልክ ለማውጣት እቅድ በሀሳብ ደረጃ ቢቆይም በድምፅ እየተጫወተ በለበያ ሊያውል ያሰበው ነጠላ ዜማ አለው። ዝግጅቱን በድምፅ ዘገባ ያገኙታል።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ