ኮንሶ በሰገን ዞን ሥር እንዲሆን መደረጉ ያስከተለዉ ቅሬታ ተባብሶ መቀጠሉ፤
ሐሙስ፣ መስከረም 26 2009ከስፍራዉ የተላከልን አንድ መልዕክት እንደሚያመለክተዉ ኗሪዎች ለስብሰባ ዉጡ የሚለዉን የመንግሥት ባለስልጣናት ትዕዛዝ አለመቀበላቸዉ በኮንሶ ዉጥረቱን አባብሶታል።
የኮንሶ አለመረጋጋት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን በዋትስአፕ ጥቆማ የላኩልን አድማጭ የመንግሥት ወታደሮች ከተማዋን ተቆጣጥረዉ ደስ ያላቸዉን ያስራሉ ይገርፋሉ፤ ከፈለጉም ይገድላሉ፤ ይላሉ። ባለስልጣናቱ ኗሪዎችን ለስብሰባ ዉጡ እያሉ መለፈፍ ከጀመሩ 7 ቀን ቢሞላም የሚፈለገዉን ያህል ህዝብ ባለመዉጣቱም ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ ማስገደድ እና በየቤቱም መግባት ጀምረዋል ሲሉም ይዘረዝራሉ። ሁኔታዉን እንዲያስረዱን በስልክ ያገኘናቸዉ የኮንሶ ኗሪ፤ እንደኗሪዉ ገለፃ በየቤቱ አሁን የሚገኙት ሕፃናት፤ ሴቶች እና አዛዉንት ናቸዉ። ወጣቶችም ሆኑ አዋቂ ወንዶች በአካባቢዉ አይገኙም፤ ጫካ ገብተዋል። እሳቸዉ ያሉትን እዚያዉ ደዉለን ያነጋገርናቸዉ ጫካ ዉስጥ ነን ያሉን አንድ ኗሪ ያረጋግጣሉ። ዋናዉ ግፊትም ይላሉ ያነሳችሁትን ጥያቄ ተዉት የሚል ነዉ፤ ያ ካልሆነ በሚል ተከትሏል ያሉት ዛቻም አለ።
የኮንሶ ሕዝብ ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ገመቹ ገንፋም ይህኑ ነዉ ያጠናከሩት። እሳቸዉም እንደሌሎች ወገኖቻቸዉ ጫካ ዉስጥ ለመኖር መገደዳቸዉ የገለፁት አቶ ገመቹ የባለስልጣናት እና የሕዝቡ ፍጥጫ ስብሰባ ዉጡ አንወጣም የሚለዉ መሆኑን ገልጸዋል። የሰዉ ቤት ንብረቱን ጥሎ ወደጫካ መሄድም ያስከተለዉ ሌላ ችግር መኖሩንም ይናገራሉ።
አቶ ገመቹ እና የኮንሶን ሁኔታ እንድንከታተል ጥቆማ ከላኩልን አድማጭ እንደተረዳነዉ አሁን በከተማዋ ሥራ የሚሠራዉ የኮንሶ ሃኪም ቤት ብቻ ነዉ። እዚያም ቢሆን ሃላፊዎቹ ሰሞኑን ታስረዉ ነዉ የተለቀቁት። ይህናን ሌሎች ያነጋገርናቸዉ ወገኖች የገለጹልንን ዝርዝር ችግሮች በመያዝ የአካባቢዉን ባለስልጣናት ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደርግናቸዉ የስልክ ጥሪዎች ባለመመለሳቸዉ፤ ሃሳባቸዉን ማካተት አልቻልንም።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ