1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉድድር ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት ቦታ 

Merga Yonas Bula
ሐሙስ፣ ጥር 3 2010

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለፕሬዝዳንትነት የሚቀርቡትን እጩዎች እየመረጠ ነው። «ስልታዊ» ያሉትን እቅዳቸውን ካቀረቡት 13 ሰዎች ዉስጥ ስምንቱ በእጩነት እንደተመረጡና እነሱም ለመስራት ያቀዱትን ነገ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ተገናኝተዉ ይወያዩበታል። በአመራረጡ ሂደት ላይ የሴቶች አለመሳተፍ ከፍተኛ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር።

https://p.dw.com/p/2qi0K
Äthiopien Universität Adis Ababa
ምስል picture alliance/robertharding/M. Runkel

xxxxxxxxxxxxxxxxxxx - MP3-Stereo

አንጋፋዉን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፕሬዝዳንትነት ከመጋቢት 2003 ዓ/ም ጀምሮ ሲመሩ የነበሩት ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ ነሃሴ 2009 ዓ/ም በኢንዶኔዥያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን  የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግኑኝነት ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ አሰማህኝ አስረስ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። መስከረም 30 ቀን 2010 የፕሮፌሴር አድማሱ ፕሬዝዳንትነት ስልጣን በይፋዊ መጠናቀቁን ተከትሎ እሳቸዉን ለመተካት ህዳር 16 ቀን 2010 ዓ/ም የስራ ማስታወቂያ መዉጣቱንም አክለው ገልጸዋል። ለፕሬዝዳንትነቱ ቦታ እጩ ለመሆን የሚፈልግ ግለሰብ እንዴት እንደሚመረጥ እና ምን ማሟላት እንዳለበት አቶ አስረስ እንደሚከተለው አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መረጣን ለማጠናቀቅ ቀኑ እንድ ነዉ ብሎ ለመናገር አሁን መረጃ የለኝም የምሉት ዳይሬክተሩ አቶ አሰማህኝ ግን የእጩዎች መረጣ ማብቂያ ጊዜዉ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት ከሚወዳደሩት ዉስጥ የጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያ ደሳለኝ ወንድም፣  በኢትዮጵያ ሲቭል ሰርቪ ዩንቨርሲቲ የሚያስተምሩት ዶክተር ፍቅሬ ደሳለኝ ይገኙበታል። እሳቸዉ ለዚህ ክፍት ስራ ቦታ መወዳደራቸዉ ሲሰማ አስተያየት ሰጭዎች ዶክተር ፍቅሬ የአቶ ሃይለማርያ ወንድም ስለሆኑ የአመራረጡ ሂደት ከንቅዘት የጸዳ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋታቸዉን በማህቨራዊ መገናኛ ገጾች ማጋራታቸውን ለመታዘብ ተችለዋል። ይሁን እንጅ ዶክተር ፍቅሬ ልምድና ብቃቱ ካላቸዉ  እንደማንኛዉም ዜጋ ለተከፈተዉ ስራ ቦታዉ ማመልከቻ ማስገባት መብታቸዉ እንደሆነ ዳይሬክቴሩ አቶ አሰማህኝ  ይናገራሉ።

ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንትነት ቦታ በሚደረገው ዉድድር ላይ ግን ሴቶች አለመሳተፋቸው  ብዙ እያነጋገረ ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ  በዩንቨርሲቲዉ ፌስቡክ ገፅ ላይ ጠለቅ ያለ ዉይይት ተደርጎ ነበር።  ሴቶች በተወዳዳሪ እጩነታ አለመቅረባቸውን በተመለከተ ተወያዮቹ  ላቀረቡዋቸው  ጥያቄዎች፣  ዩኒቨርሲቲዉ «ፈረሱን ወደ ወንዝ ልትወስደዉ ትችላለ፣ ግን እንድ ጠጣ ልታስገድደዉ አትችልም» የሚል መልስ መስጠቱ ብዙ ቅሬታ ፈጥሯል። ዳይሬክቴሩ አቶ አሰማህኝ እንደሚሉት ዩኒቨርሲቲው ሴቶች እንዲሳተፉ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር።

ወደ 11 ፕሬዝዳንቶች ከ67 ዓመታት በፊት የተመሰረተውን የአድስ አበባ ዩኒቨርሲቲን አስተዳድረዋል። ዩኚቬርስትዉ አሁን 2800 ሰራተኞች እንዳሉት እና  በግምት ወደ 52 ሺህ ተማሪዎች እያስተናገደ እንደሚገኝ አቶ አሰማህኝ አስታውቀዋል።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ