1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቷ የግእዝ መምህርትና ደራሲ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 16 2006

ሀሳብን በስፋትና በጥልቀት የመግለፅ አቅሙ እጅግ የዳበረ እንደሆነ ይነገርለታል፤ ጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ። አንዳንዶች ግእዝ ሞቷል መቀበር ብቻ ነው የቀረው ሲሉ ይደመጣል። ሌሎች ደግሞ የለም፤ ቋንቋው በቤተክህነትና በሌሎችም ቦታዎች አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው አልሞተም፤ እንደውም አሁን እያንሰራራ ነው በማለት ለማስረዳት ይሞክራሉ።

https://p.dw.com/p/1Bnm7
ምስል DW/ A.T.Hahn

በእርግጥ የግእዝ ቋንቋ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ቋንቋው እንዲያንሰራራ ማድረጉስ ጠቀሜታው ምንድን ነው? 11 የግእዝ ቋንቋ የመማሪያ መጻህፍት ያሳተመችው የግእዝ ቋንቋ መምህርቷ ወጣት ኖኃሚን ዋቅጅራን እንዲሁም የቋንቋው ምሁራንን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አነጋግረናል።

የቅኔውን ትርጓሜና አንድምታ የ28 ዓመቷ ወጣት ኖኃሚን ዋቅጅራ ወደ በኋላ ላይ በሠምና ወርቅ ከፍላ ታብራራልናለች። የግእዝ ቋንቋ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል በሚል ላቀረብንላት ጥያቄ ነበር ቅኔውን ያስደመጠችን። ወላጆቿ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኦሮሚኛ መሆኑን የተናገረችው ወጣት ኖኃሚት ዋቅጅራ በተለይ የግእዝ ቋንቋን ለማጥናት ያነሳሳት ምን እንደሆነ ስትገልጥ እንዲህ ትላለች።

ኖኃሚን ከአንደኛ እስከ አስረኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች የሚያገለግሉ 10 የተለያዩ የግእዝ ቋንቋ ማስተማሪያ መጸሐፍትን አሰናድታ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ አበርክታለች። ከእዚያም ባሻገር ማንኛውም ሰው የግእዝ ቋንቋን በቀላሉ መማር እንዲችል በሚልም «ማኅቶተ ጥበብ ዘልሣነ ግእዝ» ብላ የሰየመችውን አስራ አንደኛ መጽሀፏንም ለንባብ አብቅታለች።

ጥንታዊ የብራና ላይ ፅሁፍ
ጥንታዊ የብራና ላይ ፅሁፍምስል DW/ A.T.Hahn

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ፋኩልቲ የአማርኛ ትምህርት ክፍል ባልደረባ፣ የዲማ ጊዮርጊስ የቅኔ ምሩቅና መምህር፣ የሕግ ባለሙያው አቶ አበረ አዳሙ የወጣት ኖኃሚን ጥረትን አድንቀው የግእዝ ቋንቋ የበለጠ መጠናቱ ጠቀሜታ አለው ይላሉ። አያይዘውም የግእዝ ቋንቋን አውቆ የሚመራመራቸውን ምሁር የሚጠብቁ በግእዝ ቋንቋ የተፃፉ ከ500 ሺህ በላይ የብራና ላይ ጽሁፎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ገልጠዋል።

በእርግጥ የግእዝ ቋንቋ በኢትዮጵያ ፊት እንደተነሳው እዚህ ያለንበት ዘመን ላይ ብንደርስም በውጭ ሃገራት ግን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከረዥም ጊዜ አንስቶ ጥልቅ ጥናት እየተካሄደበት ይገኛል። የግእዝ ቋንቋን ማጥናት የሀገሪቱን ታሪክና ጥበብ በቀላሉ ለመረዳት እንደሚያግዝ ምሁራኑ ያምናሉ። አቶ አበረ ቋንቋው ዐሳብን ለመግለፅ ምን ያህል ምቹ እንደሆነ ሲያብራሩ በምሳሌ እያጣቀሱ ነው።

የግእዝ ቋንቋ ጠቀሜታን ተረድተው ቋንቋውን በጥልቀት ካጠኑ የውችጭሃገራት ሊቃውንት መካከል ለአብነት ያህል ጀርመናውያኑ እነ ሂዮብ ሉዶልፍና ኦገስት ዲልማንን መጥቀስ ይቻላል። ጣሊያናውያኑ ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒና ኢግናትሲዮ ጉዊዲ ለቋንቋው ያበረከቱት ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑ በታሪክ ድርሳናት ሰፍሮ ይገኛል። የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በግእዝ ቋንቋ ለመያዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት የሚያደርጉት ጋዜጠኛና ደራሲ ታደለ ገድሌ።

Älteste äthiopische Bibelhandschrift
ጥንታዊ የብራና ላይ ፅሁፍምስል DW/ A.T.Hahn

አቶ ታደለ የግእዝ ቋንቋ ትንሣኤው እየታየ ነው ቢሉም፤ መምህር አበረ ቋንቋው ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ጥሩ ደረጃ ላይ አለመገኘቱን ይገልፃሉ። እስኪ አሁን ደግሞ ወጣት ኖኃሚን ሐረር ከተማ ውስጥ ይገኝ ለነበረው ወንድሟ ቀደም ሲል በግእዝ ቋንቋ እየጻፈች በመምህሯ አሳርማ ትልከው ከነበረው ደብዳቤ የምታስታውሰው ምን ይመስል እንደነበር እናዳምጥ።

በነገራችን ላይ ኖኃሚን ደብዳቤውን በግእዝ ቋንቋ እየጻፈች እንድትልክለት የወንድሟ ማበረታቻ ወላጆቿ በቋንቋው እንድትዘልቅ ያደርጉላት የነበረው ከፍተኛ የሞራል ድጋፍ ቋንቋውን ይበልጥ ጠበቅ አድርጋ እንድትይዝ እንደረዳት ገልጣለች። ከእዛም አልፎ ዛሬ የግእዝ ቋንቋ ቢያንስ ላለመሞቱ በእሷ ትውልድ አብነት ሆና መነሳቷን ጠቅሳለች።

ጥንታዊ የብራና ላይ ፅሁፍ
ጥንታዊ የብራና ላይ ፅሁፍምስል DW/ A.T.Hahn

በአሁኑ ወቅት እንግሊዘኛ ሲጠቅሱ የተራቀቁ የሚመስላቸው በርካታ ሊቃውንት መበራከታቸውን የተቹት አቶ አበረ የኖኃሚን ጥረትን አድንቀዋል። አቶ ታደለ ገድሌም እንደ ኖኃሚን ዋቅጅራ ያሉ ወጣቶች ተጣጥረው ለግእዝ ቋንቋ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ሲያደርጉ ሊበረታቱ ይገባል ብለዋል።

የግእዝ ቋንቋ የበለጠ እንዲስፋፋ ምኞቷ እንደሆነ የተናገረችው መምህርት ኖኃሚን ዋቅጅራ ሊደረጉ የሚገባቸውን ጥረቶች ጠቁማለች።

የ28 ዓመቷ ወጣት መምህርት ኖኃሚን ዋቅጅራ በቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የማታው ትምህርት መርሀ-ግብር የ5ኛ ዓመት የሥነ-መለኮት ተማሪ ናት። በተጓዳኝ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የክረምት መርሀ-ግብር የልዩ ፍላጎት፤ ማለትም የብሬልና የምልክት ቋንቋ የስነ-ልቦና ትምህርት ክፍል 5ኛ ዓመት ላይ ደርሳለች።

በሁለቱም የትምህርት ዓይነቶች ዘንድሮ በዲግሪ ትመረቃለች። ቀደም ሲል በእንግሊዘኛና አማርኛ ቋንቋዎች የዲፕሎማ ተመራቂም ናት።

ወጣቷ መምህርት ወደፊት መስማት የተሳናቸውንና አይነስውራንን ግእዝ ለማስተማር ዕቅድ አላት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ