ወጣቱ ተመራማሪ በጀርመን ዩኒቨርሲቲ
ዓርብ፣ የካቲት 1 2005በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተመራማሪነት አገልግሏል ወጣት ቴዎድሮስ ደበበ። አሁን ደግሞ የዶክትሬት ማዕረግ ሊያሰጥ የሚችለውን ምርምር ማለትም ፒ ኤች ዲውን ለመቀጠል እዚህ ጀርመን ሀገር ይገኛል። የቋንቋ ትምህርቱን የሚከታተለው ቦን ከተማ ውስጥ ነው። ያነጋገርኩት ግን አማካሪ ፕሮፌሰሩን ለማነጋገር ወደ ፊት ምርምሩን የሚያካሂድበት ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት የላይብዚሽ ከተማ ሄዶ ሳለ ነው።
የወጣት ቴዎድሮስ ጥናት የሚያተኩረው በዚህ ከሣንባ ውጪ በሚገኘውና ፈልጎ ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ በሆነው ቲቢ ዙሪያ ምርምር ማካሄድ ላይ ነው። በተለይ በኢትዮጵያና እያደጉ ባሉ ሀገራት ውስጥ ከሳንባ ውጪ የሚገኝ ቲቢን ፈልጎ ለማግኘት እጅግ አዳጋች ነው። ወጣቱ ተመራማሪ ያብራራል።
ወጣቱ እዚህ ከፍተኛ ትጋትን የሚጠይቅ ምርምር ላይ ለመሳተፍ ከማመልከቱ አስቀድሞ በርካታ ጥረቶችን አድርጓል። ፓስተር ኢንስቲትዩት ፈረንሳይ ሀገር ውስጥ በሚሰጠው የክትባት ስልጠና ላይ ባለፈው ዓመት ተካፍሏል። ከዚያም ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመልሶ ከሳንባ ውጪ የሚገኝ ቲቢን የሚመረምር መሳሪያ እንዲሁም ክትባቱን ለማግኘት ታላቅ አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችል የጥናት ዕቅድ ነደፈ። ጀርመን ሀገር ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተፃፃፈናም ላይብዚሽ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጥናቱን ለመቀጠል ዕድሉን አገኘ። ቴዎድሮስ «የሰው ልጆች ወደ እዚች ምድር ስንመጣ ያለምንም ምክንያት አይደለም» ሲል ይቀጥላል።
በእርግጥም ተግባራዊ ጥረት ካላከልንበት በስተቀር ማንኛውም ነገር ምንም ያህል ጊዜ በጥልቀት ደጋግመን ብናስብት በራሱ ጊዜ አንዲት ጋትም ቢሆን ፈቅ አይልም። ለዚያም ነው እዚህ ጀርመን ሀገር ሲመጣ አንድም የጀርመንኛ ቃል የማያውቀው ወጣት ቴዎድሮስ በሶስት ወራት ያላሰለሰ ጥረት ብቻ በቋንቋው መግባባት ደረጃ የደረሰው። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ አውሮጳ ሲደርስ ከተቀበለው ቀዝቃዛ የዓየር ጠባይ ባሻገር የማያውቀው ባህልና የቋንቋ ችግር ተደማምረው ተስፋ ወደ መቁረጡ ደረጃ አዳርሰውት ነበር።
ወጣቱ ያን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ አሁን ከሁሉ ነገር ጋር የተላመደ ይመስላል። እዚህ አውሮጳ የገና ሰሞን የተመለከተው የከተማ ገበያዎች በመብራቶች አሸብርቀው መታየታቸውና የህብረተሰቡ እንቅስቃሴ ያስገረመውን ያህል፤ የሰሞኑ የካርኒቫል ማለትም የፈንጠዝያ ባህሉም ሳያስደምመው አላለፈም። ከዚያ ሁሉ ባሻገር ግን ለሶስት ዓመት ግድም የሚዘልቀው ምርምሩን በትጋት ለመቀጠል ከወዲሁ ወገቡን ጠበቅ ማድረግ እንዳለበት ተረድቷል።
ወጣት ቴዎድሮስ ጥናት እና ምርምሩ ሰምሮለት ለእራሱም ለሀገሩም የሚጠቅመውን መሣሪያ እንዲፈለስም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ እየተመኘን ከወዲሁ እንሰናበታለን።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ተክሌ የኋላ