ወጣቱና የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት
ዓርብ፣ ጥቅምት 1 2006ቤተልሔም ተሻገር እና ስያኔ አንለይ ሁለቱም አንድ የጋራ ዓላማ አላቸው። በተቻላቸው መጠን ስለ ሀገራቸው ታሪክ ማወቅና ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት ይፈልጋሉ። ፍላጎታቸውንም ዕውን በማድረግ ላይ ናቸው። አንዷ የሥራዋ ሁኔታ ይበልጥ ስላመቻቸላት ሌላኛዋ ደግሞ ሆን ብላ ጉዞዎችን በማቀድ እና በመተግበር ላይ ትገኛለች።
የቤተልሔም ሥራ ከቢሮ አያስወጣም። የ28 ዓመቷ ቤተልሄም በተመረቀችበት የሂሳብ አያያዝ ሙያ ተሰማርታ አዲስ አበባ ውስጥ ትሰራለች። በተቻላት መጠን ግን የሀገሯን ታሪካዊ ቦታዎች ለመጎብኘት ዕረፍት ትወስዳለች። ይህም አስፈላጊ ነው ብላ ታምንበታለች። እንደ ጀርመን ባሉ አገሮች በተለይ በትምህርት ቤት ወቅት በቡድን በመሆን ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት በፍላጎት ብቻ ሳይሆን በግዳጅ የሚሰጥ የትምህርት አካል ነው? ይህ በኢትዮጵያ እንደ ትምህርት ቤቱ እና አስተማሪው ጥረት ይለያይ እንጂ በቡድን ታሪካዊ ቦታዎች መጎብኘት አለ። ቤተልሔም ትምህርት ቤት ሳለች ቤተ መዘክሮች መጎብኘቷን ታስታውሳለች። አብዛኛውን ጊዜ ለተማሪዎች ጊዜ ነፃ መሆናቸው ወይም ለመጎብኘት መጠነኛ ክፍያ ብቻ መጠየቃቸው ተማሪዎችን ያበረታታል ትላለች ቤተልሔም።
ሌላኛዋ ወጣት ስያኔ አንለይ ፤ በአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ የ2ኛ ድህረ ምረቃ ተማሪ ናት። በአሁኑ ሰዓት መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ በትርፍ ጊዜዋ የሥራ ልምምድ ታደርጋለች። ሥራዋም ኢትዮጵያን እየዞረች ከሀገሯ ታሪካዊ ቦታዋች ጋ እንድትተዋወቅ መንገድ ፈጥሮላታል። ወጣቷ በምታገለግልበት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሥራ ድርሻዋ በትምህርት ላይ ያተኮረ ነው። ወደ ተለያዩ ከተሞች ስትሄድ ት/ቤቶችን መጎብኘት ከዋንኛ ሥራዋቿ አንዱ ነው። ስያኔ እንዴት አድርጋ ሥራ እና የሀገር ጉብኝቷን እንደምታዛምድ አጫውታናለች።
ሁለቱም ወጣቶች የሀገር ታሪካዊ ቦታዎችን ለማየት ስለሚያደርጉት ጥረት ነግረውናል። ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሰ