ወባ-የወባ ትንኝ ንክሻ ለሞት ሲዳርግ
የወባ በሽታ ግንባር ቀደም ገዳይ በሽታ መሆኑ ይነገርለታል። በየዓመቱ በወባ በሽታ ሳቢያ ከአንድ ቢሊዮን ሰዎች በላይ ይሞታሉ።
የወባ ትንኝ ስትነክስ
በአፍሪካ አደገኛዋ ትንኝ 6 ሚሊሜትር ርዝመት ያላት የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ናት። በዚህ በሽታ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ያህል ሰዎች ይሞታሉ። በሽተኛውም ተመላልሶ በሚመጣ ትኩሳት እና ማንቀጥቀጥ ይሰቃያል። በሽታው በተለይ ህፃናትን ቶሎ ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
መነሻው ትንኟ ናት
አንድ ቢንቢ ወባ የተያዘን ሰው ከነከሰች፤ የወባ አስተላላፊውን ተውሃሲ ትወስዳለች። ይህንንም ሌላ ጤነኛን ሰው በመንከስ ታስተላልፋለች። ባለሙያዎች ይህንን ጥገኛ ተህዋሲ እዚህ ምስል ላይ በአረንጓዴ ቀለም ያሳያሉ። በመጀመሪያ ተህዋሲው በወባ ትንኟ ሆድ ውስጥ ይባዛና አረንጓዴው ነጥብ እንደሚያመላክተው ወደ የምራቅ ማውጫ ዕጢው ሄዶ ይጠራቀማል።
የወባ አስተላላፊ ተህዋሲ ለምርምር
የወባ በሽታን የሚያስተላልፈው ተህዋሲ በሳይንሳዊ አጠራሩ ፕላስሞዲዮም ይባላል። ባለሙያዎች የወባ አስተላላፊ ተህዋሲን የተሸከመችውን ትንኝ የምራቅ ማውጫ ዕጢ ለምርምር ተግባር በማውጣት አስተላላፊውን ተህዋሲ ይወስዳሉ። ምስሉ ላይ በቀን በኩል ትንኟ ስትሆን በግራ ደግሞ የተላቀቀው የምራቅ ማውጫ ዕጢዋ ይታያል።
የወባ ትንኝ -ሰው-የወባ ትንኝ
የሰው ልጅ የወባው ጊዜያዊ መኖሪያ ሲሆን የመጨረሻው መኖሪያ ራሷ ትንኟ ናት። ሰው ውስጥ በሽታ አስተላላፊው ተህዋሲ የሚያድገው በመጀመሪያ ጉበት ውስጥ ከዛም በቀይ የደም ሴል ውስጥ ነው። ከዚያም ከተውሃሲው የተወሰኑት ዓንስት እና ተብዓት ሴል ሆነው ያድጋሉ። እነዚህን ቢንቢዋ መልሳ ትወስድ እና በውስጧ ማሳደጓን ይቀጥላለች። በዚህም የርባታው ሂደት ይጠናቀቃል።
የወባ አስተላላፊ ተህዋሲ እንቅስቃሴ
ጠመዝማዛ የሆኑት የወባ አስተላላፊ ተህዋሲያን በዙር ይንቀሳቀሳሉ። እንደሚታየው ባለሙያዎች በአንድ ጠርሙስ እና ፈሳሽ ውስጥ ሲያስቀምጧቸው እንቅስቃሴያቸውን መመልከት ይቻላል። የተህዋሲያኑ ቀለም ቢጫ ሲሆን ሰማያዊው ቀለም እንቅስቃሴያቸውን ያሳያል። ተህዋሲያኑ ፈጣን ናቸው። አንዷን ዙር ለመጨረስ 30 ሰከንድ ብቻ ነው የሚፈጅባቸው።
ከንክሻው በሽታው እስከሚታይበት ጊዜ ድረስ 12 ቀናት ያልፋሉ
በሽታ አስተላላፊው በመጀመሪያ በሰው ጉበት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት ይቆያል። በዚህ ወቅት በወባ ትንኝ የተነከሰው ሰው ምንም ዓይነት የተለየ ስሜት አይታየውም። ለመጀመሪያ ጊዜ ህመም የሚሰማው ተህዋሲያኑ ጉበቱን ለቀው ቀይ የደም ሴሎቹን መጉዳት ሲጀምሩ ነው።
የወባ በሽታ በደም ውስጥ
ተህዋሲዎቹ በቀይ የደም ሴል ውስጥ ለመራባት ከ1-3 ቀናት ይፈጅባቸዋል። ያኔም የደም ሴሎቹ ይሞቱና በርካታ ያደጉ የወባ በሽታ አስተላላፊዎች እና መርዝ ያዘሉ ነገሮች ይወጣሉ። ኃላም በሽተኛው ከፍተኛ ትኩሳት ይይዘዋል። በሽታውን ደም ወስዶ በማይክሮስኮብ በማጉላት ለማወቅ ይቻላል። ተህዋሲያኑ ሃምራዊ ቀለም ስለሚይዙ በሽታውን ቶሎ ለመለየት ይቻላል።
በምድር ሰቅ አካባቢ
ወባ የሞቃታማ አካባቢ በሽታ ነው። ሙቀት እና እርጥበት ባለበት ቦታ በሙሉ ቢንቢዎች ይገኛሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሽታው ይበልጥ ሳይስፋፋ አልቀረም። አዲስ ጥናቶች ደግሞ ሌላ ውጤት ነው ይዘው የመጡት። በዚሁ መሰረት ባለሙ ሙቀት መጨመር የተነሳ ርጥበት ያላቸው ቦታዎች ስለሚደርቁ የበሽታው መራቢያ ቦታ ቀንሷል።
አጎበር ህይወት አትራፊ ነው
የወባ በሽታን ለመከላከል ወሳኙ ጨርሶ በቢንቢ አለመነከስ ነው። ለዚህም የተለያዩ ቅባቶች ትንኟን ለማራቅ ይረዳሉ። አጎበር መጠቀም ሕይወት ሊያድን ይችላል። ጥሩ መከላከያ ነው።
ፀረ የወባ በሽታ መድሀኒት
የወባ በሽታ በተስፋፋበት አካባቢ ሰዎች ህንድ ሞምባይ እንደሚደረገው የትንኝ ማጥፊያ መርዝ ይረጫሉ። ከሚረጩት መካከል እንደዚህ አይነት DDT አንዱ ነው። DDT የወባ ትንኝን ለማጥፋት ፍቱን ቢሆንም ጤና እና አካባቢን ይጎዳል።
በሽታውን ፈጥኖ መለያ ምርመራ
ደም በመውሰድ የሚደረግ ፈጣን ምርመራ በሽታውን ለመለየት ይረዳል። የድንበር የለሽ የሀኪሞች ድርጅት ሀኪሞች ፤አንዱ የማሊ ሕፃን በወባ መያዙን አረጋግጠዋል። ወዲያው መድሀኒት የተሰጠው ሕፃን ከሁለት ቀናት በኋላ ተሽሎታል። እንደዚህ አይነት ፈጣኑ ምርመራ ግን ሁሌ አስተማማኝ አይደለም።
የትግሉ አዳጋችነት
መድሃኒቱ በደም ውስጥ ያሉት ተህዋሲያን እንዳይባዙ ይረዳል። ችግሩ ግን ተህዋሲዎቹ ከጊዜ በኋላ መድሀኒቱን ይላመዱታል። እንደ ክሎሮኪን ያሉ መድሃኒቶች በአንዳንድ አካባቢዎች ጨርሶ አይሰሩም። በዛ ላይ ፤ ኃይል የሌላቸው የሀሰት መድሃኒቶችም እየሰሩ ትንኞቹ መድሀኒቱን የሚለምዱበት ሁኔታ ፈጥሮዋል። ፀረ ወባው ትግል ውጤታማ እንዲሆን አዲስ መድሀኒት መስራት ብቻ ነው።
ክትባት እንደ አማራጭ?
የወባን በሽታን የሚከላከል ክትባት እስካሁን አልወጣም። ባለሙያዎች ግን በትጋት እየተመራመሩ ይገኛሉ። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ ተስፋ ሰጪ ፍንጭ ታይቷል። ምናልባትም ከ 2015 ጀምሮ ክትባቱ በገበያ ላይ ሊውል ይችላል። ይሁንና መድሀኒቱ ከ 30- 50 ከመቶ የመከላከል አቅም ብቻ ነው የሚኖረው።