1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ ረሐብ እና የወሲብ ሽብር

ረቡዕ፣ ነሐሴ 10 2009

ኮንጎ በአሠሪ-ሠራተኛ ሕዝቧ ሳይሆን በገዳይ-አስገዳይ፤ በዘራፊ-ደፋሪ፤ተዋጊ ሚሊሺያዎችዋ ነዉ የምትታወቀዉ። የርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት ኮንጎ ልጃገረዶች፤ ወንድ ልጆች፤ ሴቶችና አቅመ ደካሞች የሚደፈሩባት፤ ደካሞች የሚታረዱ፤ እጅ እግራቸዉ የሚቀረጠፍባት ሐገር ናት።መድፈር እንደ ጠመንጃ፤ቆንጨራዉ ሁሉ  ጠላትን ለማስገበር እንደ ጥሩ መሳሪያ ይታያል

https://p.dw.com/p/2iLa3
Ostkongo Kongo Vergewaltigte Frauen von Luvungi
ምስል Simone Schlindwein

«የሚፈፀመዉን ግፍ መድፈር የሚለዉ ቃል አይገልፀዉም»

ኮንኮ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዉስጥ 8 ሚሊዮን ያሕል ሕዝብ ለረሐብ መጋለጡን የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት(FAO) አስታወቀ።ድርጅቱ እንደሚለዉ ጦርነትና ግጭት ያየለበት የምሥራቃዊ እና የማዕከላዊ ኮንጎ ሕዝብ ተረጋግቶ ማረስና ማምረት አልቻለም።የርስ በርስ ጦርነቱ ከ3,7 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተፈናቅሏልም።የመንግሥት ጦር እና የተለያዩ ሚሊሺያዎች በልጃገረዶች፤ በወጣት ወንዶችና ሴቶች ላይ የሚፈፅሙት  መድፈር እና ግፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ነዉ።ዝርዝሩን እነሆ።
ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንደ ረጅም ሥሟ ሁሉ፤-የማዕድን ሐብቷ ዓይነት-መጠንም ብዙ ነዉ።ሰፊ ናት።ለም።ማዕድን፤ደን፤አዉሬ እንስሳዋ በቅጡ ሥራ ላይ ቢዉል ገሚስ ዓለምን ይቀልባል።ለም መሬትዋ ብቻ አራሽ- አሳራሽ ቢያገኝ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያጠግባል።ከድፍን አፍሪቃ ሕዝብ የሚበልጥ ማለት ነዉ።

ሁሉም ግን ያዉ «ቢሆን ኖሮ» ምኞች ነዉ።ኮንጎ በአሠሪ-ሠራተኛ ሕዝቧ ሳይሆን በገዳይ-አስገዳይ፤ በዘራፊ-ደፋሪ፤ተዋጊ ሚሊሺያዎችዋ ነዉ የምትታወቀዉ። የርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት ኮንጎ ልጃገረዶች፤ ወንድ ልጆች፤ ሴቶችና አቅመ ደካሞች የሚደፈሩባት፤ ደካሞች የሚታረዱ፤ እጅ እግራቸዉ የሚቀረጠፍባት ሐገር ናት።
ደካሞችን መድፈር እንደ ጠመንጃ፤ቆንጨራዉ ሁሉ  ጠላትን ለማስገበር እንደ ጥሩ መሳሪያ ይታያል።
                         
«ከምሽቱ አራት ሰዓት ግድም እቤታችን መጡ እና ቀሰቀሱን።ልጆቹንና አባቴን በቆንጨራ ከተከቷቸዉ።እኔን አምስቱ እየተፈራረቁ ደፈሩኝ።ሲበቃቸዉ ቤቱን አነደዱት።»
ትላለች ሜሪ።ምሥራቃዊ ኮንጎ ጎማ ዉስጥ የተደፈሩ ሴቶች በሚጠለሉበት ቤት ከሚኖሩ ብጤዎችዋ አንዷ ናት።መጠለያዉን ያሰሩት ጁስቲን ማሲካ ናቸዉ።የተደፈሩ ሴቶችን መርዳት ከጀመሩ 15 ዓመታቸዉ ነዉ።ሜሪን የደፈሯት ታጣቂዎች ማንነት አይታወቅም።የመንግስት ወታደሮች፤በመንግሥት የሚደገፉ ሚሊሻዎች፤የመንግሥት ተቃዋሚ አማፂያን ሊሆኑ ይችላሉ።«ሁሉም አንድ ናቸዉ» ይላሉ ወይዘሮ ማሲካ
«አስገድዶ መድፈርን ሁሉም እንደ ጦር መሳሪያ ይቆጥሩታል።በየመንደሩ እየገቡ ያገኙትን ሴት ሁሉ ያጠቃሉ።ይሕን በማድረግ እርምጃቸዉን ማቆም በማይችሉ ጠላቶቻቸዉ ወንዶች ላይ የበላይነታቸዉን ያሳያሉ።»
ኦኖራታ ኪሴንዴ ደስተኛ መምሕርት፤ ባለትዳርና የአምስት ልጆች እናት ነበሩ።እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ2001 የሁቱ አማፂያን አፍነዉ ወሰዷቸዉ። ለእስራ-ስምንት ወራት እንደ ሰዉም፤እንደ አዉሬም፤እንደ እብድም፤ እንደ አረመኔም ተቻወቱባቸዉ።«ቆንጆ ነሽ ካሉ አለቀልሽ» ይላሉ የ49ኝ ዓመቷ ባልቴት።ከአጋቾቻቸዉ አምልጠዋል።ግን ሁሉን አይተዉ ሁሉን ያጡ የዕድሜ ልክ በሽተኛ ናቸዉ።
የሴቶች ሐኪም ዶክተር ዴኒስ ሙክዌንጌ እንደሚሉት የኮንጎ ታጣቂዎች በሴቶች ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ «መድፈር» ማለቱ በቂ አይደለም።
«ሥለመደፈር ሲነገር፤ በተደፈረችዉ ሴት ላይ ሥለተፈፀመዉ ነገር በዓዕምሯችን የምንስለዉ ምሥል አለ።እዚሕ ለሚፈፀመዉ ግን ቃሉ በቂ አይደለም።ምናልባት የወሲብ ሽብር ቢባል ሳይሻል አይቀርም።እኔ አላዉቅም ግን አዲስ ቃል መገኘት አለበት።ምክንያቱም እዚሕ የሚፈፀመዉን ግፍ መድፈር የሚለዉ ቃል አይገልፀዉም።»
ዶክተር ሙክዌንግ እንደሚሉት በተደፈሩ ሴቶች ላይ ከሚደርሰዉ ሥነልቡናዊ ሥብራት በተጨማሪ በመዉለጃ አካላቸዉ ላይ የሚደርሰዉ ጉዳት ከባድ ነዉ።አንዳዶቹ ከተደፈሩ በኋላ መዉላጃ አካላቸዉ ዉስጥ መርዝ ይጨመርባቸዋል።ሌሎቹ በጥይት ይመታሉ።የተቀሩት በማይድን በሽታ ይለከፋሉ።የወንዶቹም ቀፋፊ ነዉ።
 «ከጨረሱ በኋላ እማላዉቀዉ ሥፍራ ጣሉኝ።መንቀሳቀስ አልችልም።ያንን ከሚያደርጉብኝ ቢገድሉኝ ተመኝቼ ነበር።» ይላል እሱ።
የርዳታ ድርጅቶች እንደሚገምቱት ምሥራቃዊ ኮንጎ ከሚኖረዉ ከየአራቱ ወንድ አንዱ ተደፍሯል።ኮንጎ በተደፈሩ ሰዎች ቁጥር ከዓለም የመጀመሪያዉን ሥፍራ ይዛለች።እስካሁን በይፋ የታወቀዉ የሴቶቹ ቁጥር ብቻ 2 መቶ ሺሕ ደርሷል።ሚስጥራቸዉን የደበቁትን እና የወንዱን የቆጠረዉ የለም።ኮንጎ ዝናብ አላጣም።ወንዝና ሐይቅ በሽ ነዉ።መሬቱ ማዳበሪያ አይሻም።ግን ማን ይስራበት። ሰዉ ይተላለቃል።ተራበ።

Demokratische Republik Kongo Symbolbild Krieg Soldat Vergewaltigung
ምስል picture alliance/dpa
Ostkongo UNO patrouiliert jetzt Luvungi Blauhelme
ምስል Simone Schlindwein

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ