1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮንጎ እና የተ መ ድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ተልዕኮ

ሰኞ፣ ነሐሴ 26 1995
https://p.dw.com/p/E0lS

በሰሜን ምሥራቃዊ ኮንጎ የተሠማራው የአውሮጳ ኅብረት አጥቂ ቡድን በትናንቱ ዕለት በቁጥጥሩ የነበረውን የመጨረሻውን የጦር ሠፈር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ጓድ አስረክቧል። ለተወሰነ ጊዜ የተመደበው እና በፈረንሣይ መሪነት የተንቀሳቀሰው አጥቂ ጓድ ከመጀመሪያው አንሥቶ ተልዕኮውን በዛሬው ዕለት እንዲያጠናቅቅ ነበር የተወሰነው። ሞኑክ ሁለት የተሰኘው አዲሱ የተ መ ድ የኮንጎ የሰላም ተልዕኮ እአአ በ 1999 ዓም ከተሠማራው የመጀመሪያው የዓለሙ መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ቡድን የተጠናከረ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ይኸው አዲሱ ተልዕኮ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በሄማና በሌንዱ ጎሣዎች መካከል የቀጠለውንና ወደ ሀምሳ ሺህ ሰው የተደለበትን የርስ በርስ ውጊያ ማብቃት መቻሉ ማጠያየቁ አልቀረም።

የአውሮጳ ኅብረት አጥቂ ጓድ ተልዕኮውን ለአዲሱ የተመ ድ ሰላም አስከባሪ ቡድን የሚያስረክብበት ሂደት እክል አላጠውም። በሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን ላይ ጥገኛ ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአውሮጷ ውጭ ተልዕኮ ያካሄደው የአውሮጷ ኅብረት አጥቂ ጓድ ተልዕኮ በዛሬው ዕለት መጠናቀቅ ነበረበት። የተመ ድ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮም እስከዛሬዋ ዕለት እንዲጠናከር ነበር የተወሰነው። የአውሮጳ ኅብረት አጥቂ ጓድ በኮንጎ ያከናወነው ተልዕኮ፡ የፈረንሣይ መከላከያ ሚንስትር ሚሼል አሊዮ ማሪ እንዳስታወቁት፡ የተሳካ ነው። ይሁንና፡ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ጓዱ በሰሜን ምሥራቃዊ ኮንጎ የጀመረውን ተልዕኮ ያራዘመበት ድርጊት የፈረንሣዊትዋን መከላከያ ሚንስትር አነጋገር የሚፃረር ሆኖ ነው የተገኘው።

የተ መ ድ ወታደሮች በተሠማሩበት የኮንጎ የኢቱሪ ክፍለ ሀገር ውስጥ ባለፈው ግንቦት ወር ሁኔታዎች እየተበላሹና እአአ በ 1994 ዓም በርዋንዳ ወደተካሄደው ዓይነቱ የጎሣ ጭፍጨፍ እየተቀየረ በተገኘበት ጊዜ ነበር የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ለዚሁ አካባቢ አንድ ዓለም አቀፍ አጥቂ ጓድ እንዲዘጋጅ ያሳሰቡት። በዚሁ መሠረትም የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ እአአ ባለፈው ግንቦት ሠላሣ በአውሮጳ ኅብረት ተቆጣጣሪነትና በፈረንሣይ መሪነት አንድ አጥቂ ቡድን ወደኮንጎ እንዲላክ ውሳኔ አሳለፈ። ኦፐሬሽን አርቴሚ የተሰኘው የፀጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ተልዕኮ እአአ ሰኔ አሥራ ሁለት በይፋ ተግባሩን ጀመረ፤ እአአ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲቆይ የተወሰነው አጥቂ ጓድ የኢቱሪ ክፍለ ሀገር ርዕሰ ከተማ ቡንያ አየር ማረፊያን እንዲቆጣጠርና የከተማይቱን ሲቭል ሕዝብም እንዲከላከል ነው ኃላፊነት የተሰጠው።

የአውሮጳ ኅብረት አጥቂ ጓድ በቡንያ ጥብቁን የጦር መሣሪያ ዕገዳ ባሳረፈበት ድርጊት በርግጥ የከተማይቱን ፀጥታ ማስጠበቅ ተሳክቶለታል። ይሁንና፡ የውጊያው መንሥዔ፡ ማለትም በመሬት መብት ሰበብ የተፈጠረው የጎሣ ውዝግብ ሁኔታ አሁንም አልተቀየረም። ለዚህም በሌሎች አፍሪቃውያት ሀገሮች እንደሚታዩት ውዝግቦች ሁሉ፡ በኢቱሪ አካባቢ የተፈጠረውም ግጭት ተፋላሚዎቹ ወገኖች አልማዝ፡ ወርቅ፡ ቡና እና ነዳጅ ዘይትን የመሳሰለውን የክፍለ ሀገሩን የተፈጥሮ ሀብት ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ትግል ዋነኛው ምክንያት መሆኑ ይነገራል። ይህና ያካባቢ ሥልታዊ ጥቅሞች እአአ በ 1998 ዓም ጎረቤት ርዋንዳና ዩጋንዳ በኮንጎ ውዝግብ ጣልቃ እንዲገቡ ማድረጉ አይዘነጋም። ሁለቱ ሀገሮች ከዚያን ጊዜ በኋላ ለተፋላሚዎቹ ወገኖች የጦር መሣሪያና የጦር ሥልጠና ጣቢያዎችን በርዳታ ከማቅረባቸው ሌላ፡ በተለያዩ ጊዜ ከተለያዩት ተቀናቃኝ ቡድኖች ጋር ተለዋዋጩን ጉድኝት በመፍጠር ውዝግቡን ማባባሳቸውም የሚታወስ ነው። የርዋንዳና የዩጋንዳ ጦር አሁን በይፋ ከአወዛጋቢው የኮንጎ አካባቢ ከወጣም በኋላ ግን፡ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ በተፋላሚዎቹ ወገኖች አንፃር ጠንካራ ርምጃ ባለመውሰዱ፡ በአካባቢው ሁኔታ ላይ ለውጥ አልታየም።

በቡንያ ከተማ ብቻ የተወሰነው የአውሮጳ ኅብረት አጥቂ ጓድ ተልዕኮ ከከተማይቱ ውጭ የተስፋፋውን ግድያ አላስቆመም። አሁን በተወሰነው መሠረት፡ እአአ በ 1999 ዓም በኮንጎ የተሠማራው ሞኑክ ሁለት የተሰኘው አዲሱ የተ መ ድ የኮንጎ የሰላም ተልዕኮ ወደፊት አራት ነጥብ አምስት ሚልዮን ሕዝብ የሚኖርበትን የኢቱሪ ክፍለ ሀገር የመቆጣጠር ከባድ ኃላፊነት ይጠብቀዋል። ለዚህም፡ የተ መ ድ ካለፈው ስህተቱ በመማር፡ ከባንግላዴሽ፡ ከፓኪስታንና ከኔፓል የተውጣጡትንና በኮንጎ የተሠማሩትን የሰላም አስከባሪ ወታደሮቹን አሀዝ በጉልህ መጨመርና አቅማቸውንም ማጠናከር ይጠበቅበታል።