ኮንጎና የተመድ ባለሥልጣናት ጉብኝት
ማክሰኞ፣ መስከረም 28 2006
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባል ሐገራት አምባሳዳሮች በኮንጎ እና በሩዋንዳ የሚያደርጉትን ጉብኝት አጠናቀዉ አዲስ አበባ ገብተዋል።አስራ-አምስቱ የምክር ቤቱ አምባሳደሮች ኪንሻሳና፥ ጎማ ከኮንጎ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ኮንጎ ከሠፈረዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር፥ አዛዦች ጋር ተወያይተዋል።በጦርነቱ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችንም አነጋግረዋል።የዶቸ ቬለዉ ጋዩዉስ ኮዋኔ እንደዘገበዉ አምባሳደሮቹ ከጦር አዛዦቹና ከባለሥልጣናቱ ጋር ያደረጉት ዉይይት «ጣልቃ ገብ ብርጌድ» በተሰኘዉ በዓለም አቀፉ ጦር ተልዕኮ ላይ ያተኮረ ነበር።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝሩን አጠናቅሮታል።
አምባሳደሮቹ ከኒዮርክ-ኪንሻ፥ ከኪንሻ-ጎማ፥ ከጎማ-ኪጋሊ ብለዉ ዛሬን አዲስ አበባ ነዉ የዋሉት። በኪንሻ ቆይታቸዉ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪዎች ጋር ላጭር ጊዜ ተነጋግረዋል።የኪንሻሳዉ ንግግር ርዕሥ፥ የጉዟቸዉ ዓለማም አንድ ነዉ።ምሥራቃዊ ኮንጎና ጦርነቷ።ወዲያዉ ጦርነቱ ወደ ሚያወድማት ወደ ምሥራቃዊ ኮንጎ፥ «ሰሜናዊ ኪቩ» ግዛት ዋና ከተማ ዘለቁ።ጎማ።
ግዛቲቱን የሚያወድመዉ ጦርነት ለወትሮዉ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ማዕከላዊ መንግሥት እና በሩዋንዳና በዩጋንዳ ይታገዛሉ የሚባሉት የM23 አማፂያን ነበር።ከቅርብ ጊዜ ወዲሕ ግን የኮንጎ መንግሥት ጦር፥ ከመንግሥት ጦር የወገነዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር፥ በዉጤቱም ጦር ያዋጡት መንግሥታት እና የአማፂያን እና የአማፂያኑ ደጋፊዎች ዉጊያ ሆኗል።
ግዙፉን የዓለም ማሕበር የሚወክሉት አሥራ-አምስቱ አምባሳደሮች ኪንሻም፥ ጎማም ያደረጉት ዉይይትም አብዛኛዉ ዓለም ባንድ ጎራ በቆመበት ዉጊያ የሚያሸንፍበትን ጥቅል ሥልት ከማብሰልሰል ያለፈ አይደለም።እንግረ-መንገዳቸዉንም ጦርነቱ ያፈናቀላቸዉ ሰዎች ከተጠለሉበት መንደር ቢያንስ አንዱን መጎብኘታቸዉ፥ የተፈናቃዮቹን የሰሥቃይ-ሰቆቃ መስማታቸዉ በጨረፍታም ቢሆን መስማታቸዉ አልቀረም።
«ከሁሉም ሥፍራ የሚመጡ ነጮችን ሥንቀበል ኖረናል።እናንተ ግን ለኛ ሠላም የማምጣት ሥልጣን አላቸሁ ማለትን ሰማን።ባሎቻችን ሞተዋል።ልጆቻችን ተገድለዋል።እሕል ዉሐ ፍለጋ ከተንቀሳቀስን እንደፈራለን።አንዳዶቻችን በኤች አይ ቪና በሌሎች በወሲብ በሚተላለፉ በሽታዎች ተለክፈናል።»
አሉ አንዷ።ሌሎቹ አለቀሱ።የተቀሩት ተማፅኗቸዉን አወረዱት።
«እባካችሁ ሠላም እንዲወርድ እርዱን፥ ርዳታችሁን እንለምናለን፥ እንማፀናለን። ሠላም ሥጡን፥ ሠላም እንፈልጋለን።» እያሉ።
ለዋይታ-ለቅሶ ተማፅኖዉ፥ የወቅቱ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ፕሬዝዳትና የጎብኚዎቹ መሪ አምባሳደር ጌሪይ ኩዊንላን መልስ ሰጡ።
«የጉብኝታችን ዓላማ በካምፓላዉ የሰላም ሒደትና በአዲስ አበባዉ የመግባቢያ ዉል መሠረት የተገባዉ ቃል ገቢራዊነትን በአካል ለማረጋገጥ ነዉ።አሁንም ቢሆን ብዙ መሠራት ያለባቸዉ ነገሮች አሉ።ይሑንና ኮንጎ በተገቢዉ ጎዳና እየተጓዘች ነዉ።ሁላችሁም ፍላጎታችሁ እንዲሳካላችሁ እንመኛለን።»
ምሥራቃዊ ኮንጎ ከሚኖረዉ ከየሥድስቱ ሰዉ አንዱ ተፈናቃይ ነዉ።የመንግሥት ጦርም፥ አማፂያንም፥ተራ ሽፍቶችም ወንዱን ይገድላሉ፥ አለያም ለዉጊያ ያዘምታሉ።ሴቱን ይደፍራሉ። አምባሳደሮቹ ኪንሻሳን ሲጎበኙ የኮንጎ መንግሥት ቢያንስ አንድ መቶ ሰላሳ ሴቶችን አስገድደዉ መድፈራቸዉ የተመሠከረባቸዉን ወታደሮቹን ለፍርድ እንዲያቀርብ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ መጠየቃቸዉ ተዘግቧል።
አምባሳደሮቹ ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ ከአፍሪቃ ሕብረት ባለሥልጣናት ጋር ያደረጉት ዉይይት ዋና ርዕሥም የኮንጎ ጦርነት ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ