1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክትባት የማዳረሱ ጥረት

ማክሰኞ፣ የካቲት 22 2008

ከአምስት ዓመታት በታች የሆኑ ሕፃናት መከላከል በሚቻል በሽታዎች ህይወታቸዉ በአጭሩ እንዳይቀጭ የሚደረገዉ ጥረት ዉጤት እያሳየ መሆኑ ይነገራል። ለዚህም በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሰዉ ሕፃናትን የሚያጠቁ በሽታዎችን ለመከላከል የሚሰጡ የተለያዩ ክትባቶች ሽፋን በመጨመሩ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1I4lM
Symbolbild Kinder Impfung Afrika Archiv 2014 Bangui
ምስል AFP/Getty Images/M. Medina

ክትባት የማዳረሱ ጥረት

በተቃራኒዉ አሁንም አፍሪቃ ዉስጥ ከአምስት ሕፃናት አንዱ ገዳይ በሽታዎችን የሚከላከሉለትን ክትባቶች ማግኘት እንዳልቻለ የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል።

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም ለሕፃናት ክትባት የማዳረሱ ሽፋን 57 በመቶ ብቻ እንደነበር ነዉ ድርጅቱ ያስታወሰዉ። ከ14ዓመታት በኋላ 80 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት ክትባት ማግኘት መቻላቸዉ ቢገልፅም አሁንም የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ ሁሉም ልጆች በተገቢዉ ወቅት እነሱን ከሚያጠቁ በሽታዎች ለመከላከል ክትባት እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነዉ የዓለም የጤና ድርጅት ያሳሰበዉ። የተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም እስከ 2013 ድረስ ክትባት በመዳረሱ በመላዉ ዓለም 15,6 ሚሊየን ልጆች በኩፍኝ ከመሞት ማትረፍ እንደተቻለ በመረጃዉ ያሳያል። እንደUNICEF አፍሪቃ ዉስጥ ብቻ በኩፍኝ ምክንያት ይደርስ የነበረዉ የሕፃናት ሞት 86 በመቶ ቀንሷል። እንዲያም ሆኖ አሁንም ልክ የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ ከአምስት ልጆች አንዱ አስፈላጊ የሆኑ ክትባቶችን ማግኘት እንዳልቻለ UNICEFም ያረጋግጣል። እስካሁንም አፍሪቃ ዉስጥ በተለይም ከሠሃራ በስተደቡብ ቴታነስን፣ ተቅማጥንም ሆነ ትክትክን ለመከላከል የሚያስችሉ ክትባቶችን ያገኙ ሕፃናት 77 በመቶ ብቻ ናቸዉ።

Unicef Logo

ባለፈዉ ሳምንት ለሁለት ቀናት አዲስ አበባ ላይ በሚኒስትሮች ደረጃ በሽታን አስቀድሞ መከላከል ስለሚያስችሉ ክትባቶች ጉባኤ ተካሂዷል። በጉባኤዉ ከተሳተፉት አንዱ በUNICEF ኒዮርክ የክትባት ጉዳዮች ዋና አማካሪ ዶክተር ሮቢን ናንዲ ስኬቶችና ጉድለቶች ተገምግመዉበታል ያሉት ይህ ጉባኤ አዎንታዊ እንደነበር ነዉ የገለፁልን፤

«አዎ ስብሰባዉ አዎንታዊ ነበር ብዬ አስባለሁ። በርካታ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሮች ተካፍለዉበታል። መከላከያ ክትባቶችን በተመለከተ ብዙ ጉዳዮች ተነስተዉበታል፤ አሁን የት ላይ እንገኛለን የሚለዉን ጨምሮ ማለት ነዉ። በተለይ ደግሞ ከዚህ አስርተ ዓመታት የክትባት ማዳረስ ጥረት በኋላ አፍሪቃ ዉስጥ ከአምስቱ ልጆች አንዱ ክትባት ማግኘት አለመቻሉን በተመለከተ ሚኒስትሮቹ ተገኝተዉ ይህ ለምን ሆነ? ሁኔታዉንስ ለማሻሻል ምን መደረግ አለበት? የሚለዉን የቅስቀሳ ሃሳብ በማንሳት ሥራዉ ገና አለማለቁን ማመላከት መቻሉ በጣም ጠቃሚ ነዉ።»

እርግጥ ነዉ ይላሉ ዶክተር ሮቢን ናንዲ የልጅነት ልምሻ ወይም ፖሊዮን ጨርሶ ከአፍሪቃ ማጥፋትን ጨምሮ በርካታ ስኬቶች ተመዝገበዋል። በኩፍኝ ምክንያት ከሚሞቱት መካከል 86 በመቶዉን ማዳን መቻሉም ሌላዉ በመከላከያ ክትባት የተገኘ አዎንታዊ ዉጤት መሆኑንም አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ሥራዉ ገና አላለቀም ይላሉ፤

«መሠረታዊዉ ነገር ግን አሁንም ሥራዉ ገና አላለቀም። ከአምስት ልጆች አንዱ ክትባት አሁንም ማግኘት አልቻለም። ስለዚህ ይህን ክፍተት ለመሙላት የተለያዩ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሮች ከሌሎች የመንግሥት አካላት ጋር ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? እናም የተለያዩ ቡድኖች ነበሩ፤እስካሁን ያልተዳረሳቸዉን ልጆች መድረስ የሚችሉ እኩልነትን የሚመለከቱ ቡድኖች አሉ፤ የልጅነት ልምሻ ላይ የተገኘዉን የስኬት ዉጤት እንዴት ማስቀጠል ይቻላል፤ ክትባቱንስ ዘላቂነት ባለዉ መንገድ በመቀጠል እንደኩፍኝ ያሉትንም ለመከላከል እና ለማጥፋት ክትባቱን እንዴት ማዳረስ ይቻላል የሚለዉም ያነጋገረ ነጥብ ነበር።»

Liberia Catherine Browne mit Baby
ለክትባት የተሰለፉ ላይቤሪያዉያን እናቶችና ሕፃናትምስል DW/J. Kanubah

ሌላዉ ክትባትን የተመለከተዉ የሚኒስትሮች ጉባኤ ሃገራት በቂ ገንዘብ ለዚሁ ተግባር መመደብ እንደሚኖርባቸዉ አንስቶም አፅንኦት ሰጥቶታል። በአብዛኛዉ የአፍሪቃ ሃገራት ከበሽታ ስለመከላከል የሚንቀሳቀሱ መርሃግብሮች ክትባትን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም አካትተዉ መሥራታቸዉን በምሣሌነትም በወባ በሽታ ለሚጠቁ አካባቢዎች አጎበር የማዳረስ እና ቫይታሚን Aን የማቅረብ እንቅስቃሴያቸዉን እንደመልካም እድል እንደሚቆጠር ዶክተር ሮቢን ናንዲ አመልክተዋል። ክትባቱን በማዳረሱ ተግባርም በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች በቂ ስልጠና የተሰጣቸዉ የህክምና ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎችም ክትባቱን መስጠት እንዲችሉ የማድረግ እቅድም ተነስቶ ጉባኤዉ ተነጋግሮበታል። ከዚህም ሌላ ከፍተኛ ጥራት ያላቸዉ ክትባቶችም ከከተሞች ወደገጠር አካባቢ በብዛት የሚዳረሱበት መንገድም ተወስቷል። ጉባኤዉ ከዚህም ሌላ ስለአዳዲስ ግኝቶች እና ቴክኒዎሎጂዎችም ተወያይቷል። ምንም እንኳን ክትባትን የማዳረሱ ጥረትና እንቅስቃሴ ሰፊ ዉይይት ቢደረግበትም እንደድንበር የለሽ ሃኪሞች ያሉ ዓለም አቀፍ የግብረ ሠናይ ድርጅቶች በብዛት መቅረብ እየቻለ ዋጋቸዉ እጅግ እየተወደደ ለተጠቃሚ ሃገሮች እንቅፋት ሆኗል ያሉት የዋጋ መወደድ ጉዳይ በዚህ ጉባኤ ትኩረት አላገኘም ሲሉ ይተቻሉ። ድርጅቱ ጉባኤዉ በሚካሄድበት ዕለት ባወጣዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ባለፉት ዓመታት የአፍሪቃ ሃገራት በአቅማቸዉ ይሸምቱት የነበረዉ ክትባት አሁን 68 በመቶ ዋጋ ጨምሮ ታይቷል ሲል ተችቷል። ድርጅቱ ነገሩን በምሣሌ ያጠናክራል ለምሳሌ የክትባት መርሃግብርን በገንዘብ ከሚደግፈዉ ጋቪ ከተሰኘዉ ተቋም ከንዘብ ባለማግኘቷ ኮንጎ ብራዛቪል በቀጣይ ዓመታት ክትባት ለዜጎቿ ማቅረብ ከፈለገች 80 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ይጠብቃታል፤ አንጎላ ደግሞ የ1,52 በመቶ ይጨምርባታል። ሌሎች ከተጠቀሰዉ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ የማያገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ለክትባት ማዉጣት ይጠበቅባቸዋል። ዶክተር ሮቢን ናንዲ የዋጋ መወደዱ ጉዳይ በጉባኤዉ ላይ ብዙም ባይሆን መነሳቱን በመጠቆም ድንበር የለሽ ሃኪሞች የጠቀሳቸዉ ነጥቦች እዉነትነት አላቸዉ ይላሉ።

Logo Medecins Sans Frontieres Ärzte ohne Grenzen MSF
ምስል picture alliance /Ton Koene

«የMSF አቋም ትክክል ይመስለኛል፤ በየትኛዉም ሃገር አንድ ልጅ ለማስከተብ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፤ በተለይ ደግሞ አፍሪቃ ዉስጥ የዛሬ ሃያ ዓመት አካባቢ ከነበረዉ ጋር ስናነፃፅረዉ አሁን ዉድ ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ አፍሪቃ ዉስጥ የክትባቱ መርሃግብር በርካታ አዳዲስ ክትባቶችንም ጨምሯል። ስለዚህ የክትባቱ ዓይነት በመጨመሩ ምክንያት ዋጋዉም ከፍ ማለቱ ያልተጠበቀ ሊሆን አይችልም። UNICEF ከተጓዳኞች እና ከክትባት አምራቾች ጋር ሲለሚሠራ የክትባቶች ዋጋ በተመጣጣኝ ደረጃ ላይ መቆየት መቻሉን ለማረጋገጥ ይሞክራል። እናም ምንኳ እንኳ የተለመዱት የኩፍኝ እና የልጅነት ልምሻ ክትባቶች አንዱ ከአንድ ዶላር ባነሰ ዋጋ ቢቀርቡም፤ አዳዲሶቹ የክትባት ዓይነቶች ለምሳሌ ሕፃናትን ከሳንባ ምች የሚከላከለዉ ክትባት ከሶስት ዶላር በላይ ያወጣል። እዉነት ነዉ የዋጋ ጭማሪዉ ይታያል፤ ባጠቃላይ በአንድ ሀገር የጤና የገንዘብ ድጋፍ ሲታይ ከወጪዉ ጥቂቱ ነዉ የሚሆነዉ።»

በዚያም ላይ ይላሉ UNICEF እና ጋቪ ለአዳጊ ሃገራት ክትባት የሚቀርብበትን ዋጋ አስመልክተዉ ያደረጉት ድርድር በበለፀጉት ሃገራት ለአንድ ክትባት ከሚወጣዉ ገንዘብ ጋር ሲተያይ በጣም ያነሰ ነዉ። ለምሳሌ የጠቀሱትም የሳንባ ምች መከላከያ ክትባት ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ለአንድ ጊዜ 18 ዶላር መሸጡን ነዉ።

UNICEF ም ሆነ የዓለም የጤና ድርጅት በዚህ ወቅት ከጠቀሷቸዉ እንከኖች በተለይ አፍሪቃ ዉስጥ አንዱ አሁንም ከአምስት አንዱ ሕፃን ክትባት ማግኘት አልቻለም የሚለዉን ነዉ። በዚህ ከቀጠለም መዳን ለሚችሉ በሽታዎች መከላከያ የሚሆን ክትባት በማጣት አምስት ዓመታቸዉን ሳያከብሩ የሚቀጩ ልጆች ቁጥር እንደታሰበዉ ሙሉ በሙሉ ላይቀንስ ይችላል። እናም ክትባቱን ለሁሉም ልጆች ለማዳረሱ ጥረት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች የትኞቹ ይሆኑ ለሚለዉ ዶክተር ዶክተር ሮቢን ናንዲ እንደየሃገራቱ መሰናክሉ መለያየቱን ይዘረዝራሉ።

«በአንዳንድ ሃገራት የተወሰኑት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ በሌሎቹ ጋር ደግሞ እንዲሁ ሌላ ዓይነት እንቅፋት ይኖራል። በጥቅሉ ከበሽታ የመከላከል ጥረትን ስንመለከት ዋነኛ ከሚባሉት ማነቆዎች አንዱ አቅርቦት ነዉ። የክትባት አቅርቦቱ የማይደርሳቸዉ ልጆች አሉ። ይህ ምናልባት ስኬታማ ካልሆነ የክትባት አስተዳደር ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ክትባቱ መቀመጥ የሚገባዉን የሙቀትና ቅዝቃዜ ሁኔታ በወጉ ባልተከታተለ የግንኙነት ሰንሰለት ችግር ሊሆን ይችላል፤ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ በቂ ያልሆነ የአገልግሎት አቅርቦትም ያጋጥማል፤ ይህም ማለት ክትባቱ አለ ነገር ግን በአድራሽና እና በማጓጓዣ ችግር አምስተኛ ያልነዉ ልጅ ክትባቱ ሳይደርሰዉ ይቀራል። እናም በርካታ አቅርቦቱን የሚያደናቅፉ ምክንያቶች ይኖራሉ።»

Deutschland Gesundheit Impfung Schweinegrippe
ምስል AP

ይህ ብቻ አይደለም ሁሉም ልጆች ክትባት እንዳያገኙ የሚያደርገዉ እንቅፋት። በአንዳንድ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ራሱ ለክትባት የሚሰጠዉ ግምት እና ከጥርጣሬ በመነሳት የሚነዛዉ የተሳሳተ መረጃ ወላጆች ልጆቻቸዉን በተገቢዉ እድሜ ክትባት እንዳያገኙ እንዲያደርጉ ይገፋፋል። ዶክተር ሮቢን ናንዲ ኅብረተሰቡን ስለክትባት ጠቃሚነት በማስረዳት አቅርቦት እና ፍላጎትን ማጣጣም እንደሚገባ ያነሳሉ።

«ኅብረተሰቡን ስለበሽታ መከላከያ ክትባት ጠቃሚነት በቂ ግንዛቤ እንዲኖረዉ በማድረግ ለልጆቹ ክትባት እንዲፈልግ ማስተማር ያስፈልጋል። ልጆች በስንት ዓመታቸዉ የትኛዉን ክትባት መዉሰድ እንዳለባቸዉ ማስረዳት ይኖርብናል። ኅብረተሰቡ ክትባት ወደመጠየቁ ደረጃ ሲሸጋገር ደግሞ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ መንገዱን ያመቻቻል ብዬም አስባለሁ። ይህም ማለት የትኛዉን የክትባት ዓይነት ለልጃቸዉ መዉሰድ እንዳለባቸዉ ካወቁ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ይሻሉ ማለት ነዉ።»

የልጆችን ህይወት በአጭሩ የሚቀጩ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገዉ ጥረት ክትባትን ማዳረስን በዋናነት መሠረት ያደረገ ነዉ። አሁንም በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ሁሉም ህፃናት ክትባት እንዲያገኙ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ