1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክሮኤሽያ 28 ተኛዋ የአውሮፓ ህብረት አባል

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2005

ከ12 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ባለፈው ሳምንት ሰኞ የቀድሞዋ የዩጎዝላቪያ ግዛት ክሮኤሽያ 28 ተኛዋ የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን በቃታለች ። የአውሮፓ ህብረት እንዳለው ክሮኤሽያ ማሻሻያዎች እንድታደርግ የተሰጧትን የቤት ሥራዎች አሟልታለች ።

https://p.dw.com/p/194i4
ምስል Reuters

የቀድሞዋ የዩጎዝላቭያ ግዛት ክሮኤሽያ ባለፈው ሳምንት ሰኞ 28 ተኛዋ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገር ሆናለች።የአውሮፓ ህብረት በዩሮ ቀውስ በተጠመደበት በዚህ ወቅት ላይ ክሮኤሽያ ህብረቱን በመቀላቀሏ በአንዳንድ ወገኖች እንደ ተጨማሪ ዕዳ ስትታይ ሌሎች ደግሞ ጥቅሙ የጋራ መሆኑን ያስረዳሉ ።
« አውሮፓን አዲስ ዲሞክራሲያዊ ፣ ፖለቲካዊ ባህላዊና ሌሎች እድገቶች ማግኛ አዲስ እድል አድርገን ነው የምናየው ። ለአውሮፓ የወደፊት እጣ ፣ ለአውሮፓ ሠላም ና ለአውሮፓ ብልፅግና ይህን ፅዋ አነሳለሁ »ክሮኤሽያ ሰኔ 24 ፣2005 ዓም በጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 1 ፣ 2013 ዓም የህብረቱ አባል መሆንዋ በተከበረበት ሥነ ስርዓት ላይ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢቮ ዮሲፖቪች ለሃገራቸውና ለአውሮፓ ህብረትም መልካም ምኞታቸውን የገለጹበት ንግግር ነበር ። ክሮኤሽያ የህብረቱ 28 ተኛ አባል የሆነችበት ዕለት በመዲናይቱ በዛግሬብ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተገኙበት በደመቀ ሥነ ስርዓት ነበር የተከበረው ማዕከላዊ ና ደቡብ ምስራቅ አውሮፓ የምትገኘው ክሮኤሽያ በሰተሰሜን ምሥራቅ ሃንጋሪ በምስራቅ ሰርቢያ በስተደቡብ ምሥራቅ ቦስኒያ ሄርዞጎቪና ፣ በደቡብ ምሥራቅ ሞንቴኔግሮ ፣ በስተደቡብ ምዕራብ የአድሪያቲክ ባህር ፣ በሰሜን ምዕራብ ደግሞ ስሎቬንያ ያዋስኗታል ። የቆዳ ስፋቷ 56 594 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው ። ከዚህም የየብሱ ስፋት 56 ሺህ 414 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሲሆን የተቀረው ደግሞ ውሐ ነው ። አገሪቱ የ4 ሚሊዮን 280 ሺህ ህዝብ መኖሪያ ናት ።

Kroatien wird EU-Mitglied
ምስል Reuters

ከህዝቧ አብዛኛው ክሮአቶች ናቸው ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዩጎዝላቭያ ሪፐብሊክ መስራችና የፌደራል ግዛቱም አካል የነበረችው ክሮኤሽያ እጎአ ሰኔ 1991 ነበር ራሷን ከዩጎዝላቪያ በመገንጠል ነፃነትዋን ያወጀችው ። በ1992 የተመድ እውቅናን አገኘች ። ምንም እንኳን ክሮኤሽያ በ1991 ራስዋን ከዩጎዝላቪያ ብትገነጥልም የነፃነቱ ትግል ከዚያ በኋላም ለ 4 ዓመትት ወስዷል ። ክሮኤሽያ ለአውሮፓ ህብረት አባልነት የሚያበቃውን ሂደት የጀመረችው እጎአ በ2001 ነበር ። ያኔ ከህብረቱ ጋር የመረጋጋትና የማህበር ስምምነት በመፈረም አንድ ብላ የጀመረችው ክሮኤሽያ እጎአ ከ2003 ዓም አንስቶ የውጭ ፖሊሲዋ የአውሮፓ ህብረት አባልነትን እውን ማድረግ ላይ እንዲያተኩር አደረገች ። በዚያው በ2003 ዓም ክሮኤሽያ የአባልነት ማመልከቻ ብታስገባም በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተፈፀሙ የጦር ወንጀሎችን ለማጣራት ከተቋቋመው ፍርድ ቤት ጋር የነበራት ግንኙነትና ከስሎቬንያ ጋር የነበረው የድንበር ውዝግብ ድርድሩ በታሰበው ፍጥነት እንዳይጓዝ መሰናክል ሆኑ ። ከስሎቬንያ ጋር የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ በ2009 ተፈታ ። ታህሳስ 2011 የክሮኤሽያ የአባልነት ድርድር ተጠናቆ ታህሳስ 9 ፣ 2011 ከህብረቱ ጋር መቀላቀል የሚያስችላትን ውል ፈረመች ። ከ12 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ባለፈው ሳምንት ሰኞ የቀድሞዋ የዩጎዝላቪያ ግዛት ክሮኤሽያ 28 ተኛዋ የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን በቃታለች ። የአውሮፓ ህብረት እንዳለው ክሮኤሽያ ማሻሻያዎች እንድታደርግ የተሰጧትን የቤት ሥራዎች አሟልታለች ። የህብረቱ የመስፋፋት ጉዳይ ኮሚሽነር ሽቴፋን ፍዩለ ።
« ክሮኤሽያ ማሻሻያ ለማድረግ ቃል የገባችባቸውን ጉዳዮች በአስተማማኝ ዘላቂናና መልሶ በማይታጠፍ መንገድ ለማሳካት በቅታለች »

EU-Beitritt Kroatien Herman Van Rompuy und Ivo Josipovic ARCHIVBILD
የክሮኤሽያ ፕሬዝዳንትኢቮ ዮሲፖቪች ና የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት ኽርማን ቫን ሮምፖይምስል picture-alliance/dpa


ከአንድ ሳምንት በፊት የአውሮፓ ህብረት አባል የሆነችው የክሮኤሽያ ኤኮኖሚ በአመዛኙ በአገልግሎት ሰጭው ዘርፍ ላይ የተመሰረተ ነው ፣ ኢንዱስትሪ ና ግብርና 2ተኛውን ደረጃ ሲይዙ ፤ ቱሪዝም በተለይ በበጋ ወራት ከፍተኛ ገቢ የምታገኝበት መስክ ነው ። ሃገሪቱ አገር ጎብኝዎችን በመሳብ ከዓለም 18ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። የክሮኤሽያው የአድሪያቲክ ባህር ዳርቻ ከ1 ሺህ የሚበልጡ ውብ ደሴቶችና መገኛ ነው ። መንግሥት ከኤኮኖሚው የተወሰነውን ክፍል ይቆጣጠራል ። ከክሮኤሽያ የንግድ አጋሮች ዋነኛው የአውሮፓ ህብረት ነው ። ክሮኤሽያ እጎአ ከ 2ሺህ አንስቶ በመሰረተ ልማት በተለይም በትራንስፖርት ዘርፍ ከሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ጋር የሚያገናኙ መስመሮች በመዘርጋት ላይ አትኩራ ነበር ። ትንሽቱ ክሮኤሽያ ህብረቱን መቀላቀሏ በብዙ ዜጎች አመለካከት የህዝቡን ኑሮ ሊለውጥ የሚችል ትልቅ እድል ተደርጎ ተወስዷል ። ይሁንና የሃገሪቱን የኤኮኖሚ ይዞታ በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ክሮኤሽያ የአውሮፓ ህብረት አባል በመሆንዋ የህዝቡ ህይወት ወዲያውኑ ይሻሻላል ማለት እንዳይደለ ከወዲሁ እያስገነዘቡ ነው ። ክሮኤሽያ ከብዙ ዓመታት ድርድር በኋላ ፣ አውሮፓ ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ በተዘፈቀበት በዚህ ወቅት ላይ የህብረቱ አባል መሆኗ ከብዙ አቅጣጫ አስተያየት እየተሰጠበት ነው ። የክሮኤሽያው ፕሬዝዳንት ደግሞ ምንም እንኳን ሃገራቸው በዚህ ወቅት ላይ አባል ብትሆንም የገንዘብ ቀውሱ በጋራ መፍታት የሚቻልባቸው መንገዶች እንዳሉ ይጠቁማሉ ።


« እንኳን ደህና መጣችሁ እንደተባልን ተሰምቶናል ። ሁል ጊዜ ግን ራሴን አንድ ጥያቄ እጠይቃለሁ ይኽውም የገንዘብ ቀውሱ ስረ-መሠረት በራሱ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ወይስ በተወሰኑ የህብረቱ አባል ሃገራት ውስጥ ነው ያለው ? እንደሚመስለኝ የገንዘብ ቀውሱ የተፈጠረው በአንዳንድ ሃገራት የኢኮኖሚ አያያዝ ነው ። ግሪክ ያለ የአውሮፓ ህብረት ምን ሊገጥማት እንደሚችል ራሴን እጠይቃለሁ ። ቀውሱን ለብቻ ከመጋፈጥ ይልቅ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በአንድ ላይ መቋቋም የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ ። »
ባለፉት 5 ዓመታት የክሮኤሽያ የኤኮኖሚ እድገት አዝጋሚ ነበር ። በዚህ የተነሳም ክሮኤሽያ የገንዘብ ቀውስ ህብረቱን ግራ ባጋባበት በዚህ ወቅት ላይ ሌላ ችግር ይዛ እንደገባች አዲስ አባል ሃገር እየተቆጠረችም ነው ። ትንሽቱ ክሮኤሽያ ሌላዋ የህብረቱ ራስ ምታት እንዳትሆን ከወዲሁ ስጋታቸውን የሚሰነዝሩ አልጠፉም ። የክሮኤሽያው ፕሬዝዳንት ግን የሃገራቸውን ኤኮኖሚ ወደ ቀድሞ ይዞታ ለመመለስ ተጨባጭ እቅዶች ነድፈናል ይላሉ።

Kroatien 20 Jahre Unabhängigkeit
ምስል picture-alliance/dpa


«ኢኮኖሚው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ያስፈልገዋል ። ባለወረቶች ፣ አዳዲስ የስራ ቦታዎች ያስፈልጉናል ። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ የሥራ አጡ ቁጥር ከፍተኛ ነው ። ይህ ትልቁ የማህበራዊ ፖለቲካና ኤኮኖሚያዊ ችግር ነው ። መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግላቸው የተወሰኑ ፕሮጀክቶች አሉ ። በመሠረተ ልማትና በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ወደፊት እየተራመድን ነው ። ከአውሮፓ ህብረት ብቻ ሳይሆን ከዛ ውጭ ቻይናና ዩናይትድ ስቴትስን ከመሳሰሉ 3ተኛ አገሮች ና ከሌሎችም ሃገራት ባለወረቶች ጋር እየተደራደርን ነው ። »
ምንም እንኳን ክሮኤሽያ ኢኮኖሚዋን ይበልጥ ለማሳደግ ልዩ ልዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ብታቅድም በሃገሪቱ ሙስና በአሳሳቢነት የዘለቀ ችግር ነበር ። እጎአ በ2007 የአውሮፓ ህብረት አባል የሆኑት ሮማንያ ና ቡልጋርያ ሙስናን ለመዋጋት በጀመሩት ጥረት ባለመግፋታቸው እስካሁን ፣ ዜጎች ያለ መግቢያ ፈቃድ በአባል ሃገራት መዘዋወር የሚያስችላቸው ድንበር አልባው የሸገን ስምምነት አባል መሆን አልቻሉም ። ክሮኤሽያ ግን በዚህ በኩል ስጋት ሊኖር አይገባም እያለች ነው ። የክሮኤሽያው ፕሬዝዳንት ከዶቼቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሁን ህዝቡ ስለ ሙስና ያለው አመለካከት ተቀይሯል ፣ የአውሮፓ ህብረትም በዚህ በኩል ስጋት ሊኖረው አይገባም ብለዋል ።
«እንደሚመስለኝ በተለይ ሙስናን በተመለከተ የተገኙት ለውጦች የሚቀለበሱ አለመሆናቸውን መረዳት አለባቸው ። እኛ ሙስና እንደተንሰራፋበት ሃገር ነበር የምንቆጠረው ። አዎን ችግሩ ነበረ ። አሁንም እንደ ሌሎች ሃገራት የሙስና ችግር አለብን ። ሆኖም ስለ ሙስና የነበረው አስተሳሰብ ተቀይሯል ። አሁን ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ሌሎች ለጉዳዩ ጀርባቸውን አይሰጡም ስለዚህ ዋና ዋናዎቹን የሙስና ጉዳዮች ብንመለከት አብዛኛዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ። ብዙዎቹ ከአውሮፓ አገራት ጋር የተገናኙ ናቸው ። ስለዚህ በጋራ እናከናውነው »

Kroatien wird EU-Mitglied
ምስል Reuters



እንደ ክሮኤሽያ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ሪፐብሊክ ተገንጥለው የራሳቸውን መንግሥታት በመሰረቱት ሃገራት መካከል ብዙውን ጊዜ በጠላትነት የመተያየት አዝማሚያ አለ ። በአውሮፓ ህብረት አባልነት ከቀድሞዋ የዩጎዝላቪያ ግዛቶች ሁለተኛዋ የሆነችው ክሮኤሽያ ይህን አዝማሚያ ለማለዘብ እንደምትጥር ነው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት የተናገሩት ።
« ከራሳችን ነው መጀመር ያለብን ። በምርጫ ዘመቻ ወቅት በሁለት ጉዳዮች ላይ ነበር ያተኮርኩት ። አንደኛው የአውሮፓ ህብረት አባልነት ሲሆን ሌላው ደግሞ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት ማሻሻል ነበር ። የአሁኑን ሁኔታ ከዛሬ 5 ና 10 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ስናነፃፅረው ባለፉት ዓመታት በጣም ተሻሽሏል ። በርካታ ስምምነቶች ላይ ደርሰናል ። በብዙ ጉዳዮች ላይ እንተባበራለን ።እርግጥ ነው አሁንም መፍትሄ ያላገኙ ጉዳዮች አሉ ። መንግስታቱ ችግሮቹ መፍትሄ እንዲገኝላቸው ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ። »
የክሮኤሽያ የአውሮፓ ህብረት አባል መሆን ተስሚነትዋን ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ለደህንነትዋም ጠቃሚ ነው ። ሃገሪቱ አሁን ዲሞክራሲያዊ መርሆችን ከሚያራምዱ አገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች ። ክሮኤሽያ የሚፈለጉባትን ቅድመ ግዴታዎች ከ 3 እስከ 5 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የጋራው ሸርፍ ዩሮ ተጠቃሚ ለመሆን አቅዳለች ። የክሮኤሽያ ፕሬዝዳንት እንዳሉት ሃገሪቱ የአውሮፓ ህብረት አባል በመሆንዋ ብዙ የሚያሰራት እድል ከፊቷ ይጠብቃታል ። ያ ማለት ግን ችግሮቿ በሙሉ ይቃለላሉ ማለት አይደለም ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ