1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬን ሳሮዊዋና የኦጎኒ ብክለት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 24 2008

ለሰዎች መብት በመታገሉ ፤ ስለአካባቢ ጥበቃ በመቆርቆሩ የሚታወቀዉ ናይጀርያዊ ኬን ሳሮ-ዊዋ በሥቅላት ከተገደለ ፣ከ6 ቀናት በኋላ 20 ዓመት ይሆነዋል። የመብት ተቆርቋሪዉ ሳሮ-ዊዋ ሼል የነዳጅ ማምረቻ ኩባንያ በትዉልድ አዉራጃዉ በኦጎኒላንድ ያደረሰዉን ከፍተኛ ጥፋት አስመልክቶ ለዓመታት ኩባንያዉን በመታገሉ ነበር ።

https://p.dw.com/p/1GzSa
Ölverschmutzung im Ogoni NDelta
ምስል DW/M. Bello

በዚያን ጊዜ ናይጀርያን ያስተዳድር በነበረዉ ወታደራዊ መንግሥት በስቅላት የተቀጣው። ሳሮ-ዊዋ የዛሬ ሃያ ዓመት ይታገልለት የነበረዉ ኦጎኒ አዉራጃ በአካባቢ ብክለት ዛሬም እጅግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆኑ ይነገራል።
በኦጎኒ አዉራጃ ቦዶ በሚባለዉ አካባቢ የሚገኙ ዓሣ አጥማጆች የዓሣ ማስገርያቸዉ ባዶ መሆኑ የየለት ክስተት ሆንዋል። በዓሣ ንግድ የሚተዳደረዉ ናይጀርያዊዉ ሲንባሪ ቦንዋ፤ ዓሳ ለማጥመድ ከቦዶ አካባቢ ተነስቶ ብዙ መጓዝ ይኖርበታል። በቦዶ መንደር ባለዉ ባህር ዓሣ የጠፋዉ በጎርጎሮዮሳዊ 2008 ዓ,ም እና 2009ዓ,ም በሺዎች የሚቆጠር በርሜል ነዳጅ ዘይት፤ የሼል የነዳጅ ዘይት አምራች ኩባንያ የነዳጅ ማመላለሻ ቧንቧ ተሸንቁሮ ዉኃ ዉስጥ በመፍሰሱ ነበር።

NO FLASH Ken Saro-Wiwa
ምስል picture-alliance / dpa


«ከሼል ኩባንያ የነዳጅ ዘይት ማመላለሻ ቧንቧ በፈሰሰዉ ነዳጅ ዘይት ምክንያት በመንደሩ ምንም ነገር መሥራት አልተቻለም። የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታዉ ወድሞአል። ከዚህ ቀደም በአካባቢዉ ከባህር ዉስጥ ለምግብ የሚሆነዉ ዉድ ቀንድ አዉጣ ሳይቀር ይገኝ ነበር። እንዲያ ዓይነቱ ጊዜ አሁን አልፎአል።»
በያዝነዉ የጎርጎርዮሳዊ 2015 ዓም መጀመርያ ላይ ሼል ኩባንያ አካባቢዉ ላይ ላደረሰዉ ከፍተኛ ዉድመት 83 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ከፍሎአል። ከዚህ ክፍያ ተጠቃሚዎቹ ግን ጥቂቶች ናቸዉ በማለት የአካባቢዉ ማኅበረሰብ ተወካይ ፒተር ሌኑ ይወቅሳሉ። እንደ ሌኑ በአካባቢዉ የሚኖረዉ ማኅበረሰብ የሚሠራዉ ሥራ እንኳ የለዉም።

Owens Wiwa demonstriert gegen Shell
ምስል picture-alliance/dpa


«ከሼል ኩባንያ ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት ኖሮን አያዉቅም፤ ምክንያቱም ለማኅበረሰቡ ስለማያስቡ። በተለይ ደግሞ በዚህ በቦዶ ያረጁ መሣሪያዎች እንኳን አልታደሱም። ራሳቸዉን የማኅበረሰቡ መሪ አድርገዉ የሰየሙ ጥቂት ቡድኖችን አሰባስበዉ ገንዘብ መስጠት የእነሱ ታዛዦች ያደርጓቸዋል።»
የዶይቼ ቬለዉ ዘጋቢ አድርያን ክሪሽ ከአካባቢዉ ብዙ ኪሎ ሜትር ሳይርቅ የሰብዓዊ ጉዳዮች ተቆርቋሪዉን የኬን ሳሮ-ዊዋን የመቃብር ቦታ ከወንድሙ ፕሪስን ሃሪ ሳሮ ዊዋ ጋር በመሆን ጎበኝቶአል። ኬን ሳሮ-ዊዋ በአጎኒ መንደር የሚገኙ ማኅበረሰቦች ከአካባቢዉ ከሚወጣዉ ነዳጅ ከሚገኘዉ የነዳጅ ዘይት ገቢ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ ለዓመታት ታግሎአል። ግን ከ 20 ዓመት በፊት ኬን ሳሮ-ዊዋ እና ጓደኞቹ በዚያን ጊዜ በነበረዉ የናይጀርያ ወታደራዊ መንግሥት ተገድለዋል፤ ምንም እንኳ የሞት ፍርዱ እንዲሻር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቃዉሞና ግፊት ቢደረግም። የኬን ሳሮ-ዊዋ ወንድም ለዚህ አድራጎት ሼል የነዳጅ አምራች ኩባንያን ተጠያቂ ያደርጋል።

Ölverschmutzung im Niger Delta Nigeria Afrika
ምስል picture-alliance/ dpa/dpaweb


« እንደኔ እምነት ሕይወቱን ለሁላችን ነዉ የሰጠዉ። ይህ ታድያ ለኦጎኒ ምን አስገኘ? በሚል፤ አንዳንዶች ምናልባት ይህን ማድረጉ አላስፈላጊ እንዳልነበር ይናገራሉ። ቢሆንም ቀስ በቀስ ዉጤት አስገኝቶአል። አሁን ኬን ያኔ እዉነት መናገሩን ሁሉም ያዉቃል። የሞተዉ፤ እዉነት በመናገሩ ነዉ። »
ሼል በኦጎኒ መንደር ያደረሰዉን የአካባቢ ብክለት ለማስወገድ 30 ዓመት እንደሚያስፈልግና አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠይቅ ምሁራን ይናገራሉ። በዚህ አካባቢ የነዳጅ ዘይት ያወጣ የነበረዉ ኩባንያ ደግሞ ሼል ብቻ ነበር።
የነዳጅ ዘይት አምራቹ ኩባንያ ሼል በኦጎኒ አዉራጃ ስላደረሰዉ ከፍተኛ የአካባቢ ብክለትና ቀዉስ ጉዳይ ማንሳት አይፈልግም። ይህ ቱጃር ኩባንያም ሆነ የናይጄርያ መንግሥት የደረሰዉን የአካባቢ ብክለት እንደሚቀርፉ በተደጋጋሚ ቃል ገብተዉ ነበር። ቢሆንም ግን እስካሁን ይህ ነዉ የሚባል የተሠራም ሆነ የሚታይ እቅድ አልታየም። የሼል ናይጀሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ የዉጭ ግንኙነት ኢጎ ዉሊ፤
« አካባቢዉን ለማጽዳት ከመንግሥት ጋር ሥራዉን በተቻለ ፍጥነት ለመጀመር እየሠራን ነዉ። መርዳት እንፈልጋለን። ርዳታዉንም ስንሰጥ የነዚህ ችግሮች መፍትሄ አካል በመሆን ነዉ።»
ዓሣ አስጋሪዉ ሲኒባሪ ቦንዋ ግን ለነዚህ ችግሮች በቅርቡ መፍትሄ ይገኛል ብሎ አያስብም። እንደ ሲንባሪ የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታዉ እጅግ ወድሟል። ማኅበረሰቡም ቢሆን አሸናፊ ተሸናፊ በሚል ለሁለት ተከፍሎአል። እንደ ሲንባሪ የኦጎኒ ላንድ የተፈጥሮ የነዳጅ ዘይት ሀብት በረከት መሆኑ ቀርቶ ርግማን ነዉ የሆነዉ።

Ölverschmutzung im Ogoni NDelta
ምስል DW/M. Bello


አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ