1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያና በምርጫ ሳቢያ፧ ገና እልባት ያላገኘው ውዝግቧ፧

ዓርብ፣ ጥር 16 2000

የኬንያ የተቃውሞው ወገን መሪ ራይላ ኦዲንጋ፧ የመጪው ሳምንት የአፍሪቃ ኅብረት መሪዎች ጉባዔ፧ ባለፈው ወር በተካሄደው ፍትኀዊነቱ አጠራጣሪ በሆነው ምርጫ አሸንፌአለሁ ለሚሉት ምዋይ ኪባኪ ዕውቅና እንዳይሰጥ በዛሬው ዕለት አሳስበዋል።

https://p.dw.com/p/E0Zj
ምስል AP
ከጥር 22-24,2000 ዓ ም አዲስ አበባ ውስጥ የሚሰበሰቡት የአፍሪቃ መሪዎች፧ ኦዲንጋ እንደሚሉት፧ ኪባኪን በፕሬዚዳንትነት ከማወቅ መቆጠብ፧ መልእክተኞችን እንዳይልኩም መከልከል ይጠበቅባቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፧ በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን የተያዘው ሽምግልና እንደቀጠለ ሲሆን፧ ውዝግቡም ጋብ አለማለቱ ታውቋል። ዝርዝሩ....
ኦዲንጋ፧ በምርጫው በተወሰደ የማጭበርበር ተግባር ድል ተነጥቄአለሁ ባይ ናቸው። ተጭበርብሯል የተባለው ምርጫ ባስከተለው ውዝግብና ሁከት ሳቢያ፧ 800 ያህል ሰዎች መሞታቸውና ሩብ ሚሊዮን የሚሆኑ ከቀየአቸው መፈናቀላቸው ታውቋል። በምርጫው ማግሥት አንስቶ ውዝግቡ እየተባባሰ በሄዳባቸው ሳምንታት፧ የደቡብ አፍሪቃው የእንግሊዝ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ፧ ዴዝመንድ ቱቱ፧ አንዳንድ የአፍሪቃ መሪዎችም ለመሸምገል ጥረት አድርገው ነበር። አሁን የሽምግልናው ተግባር ለቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ለኮፊ አናን ሆኗል የተተወው። ኮፊ አናን፧ ትናንት የተሳካላቸው ጉዳይ ቢኖር፧ በውዝግብ ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ፖለቲከኞች፧ ፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪንና የተቃውሞውን ወገን መሪ ራይላ ኦዲንጋን በተናጠል ከማነጋገራቸውም ሌላ ሁለቱን አንድ ላይ አቀራርበው የእጅ ሰላምታ እንዲለዋወጡ ማብቃታቸው ነው። ውዝግቡን ለመፍታት፧ ሽምግልናቸው እስካሁን እንዳልተሳካ ነው የሚነገረው። ተስፋቸው ግን አለመሟጠጡን ራሳቸው፧ የቀድሞው የተ. መ. ድ. ዋና ጸሐፊ አናን ሳይጠቁሙ አላለፉም።
«ችግሩን ለማስወገድ፧ ወደ ሰላማዊ መፍትኄ የሚያደርሱ አንዳንድ እርምጃዎችን መወሰድ ጀምረናል ብዬ አስባለሁ። እንደምታዩትም ሁለቱም መሪዎች አብረው በሚሠሩበት መንገድ ላይ ትኩረት ሰጥተው ለመወያየት ነው እዚህ የተገኙት።«
ይሁንና ኬንያ ውስጥ የቀጠለው የኃይል እርምጃ አናን እጅግ አላሳሰበም አይባልም። ፖሊስ ትናንት እንዳስታወቀው፧ ሞሎና ናኩሩ በተባሉት በስምጡ ሸለቆ በሚገኙት ከተሞች በተፈጠረ ግጭት ሰባት ሰዎች ተገድለዋል። በተጨማሪ ስድስት ሰዎች፧ አንድ የፖሊስ መኮንን ጭምር ቆስለዋል። አናን ባለፈው ረቡዕ፧ ኬንያ ሲገቡ፧ በየጎዳናው የሚታይ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲገታ፧ የተቃውሞው ወገን መሪ ራይላ ኦዲንጋ ትእዛዝ ቢያስተላልፉም የፖለቲካ መፍትኄ እስካልተገኘ ድረስ፧ ህዝቡ እርምጃ ሊወስድ የሚችልበት እርምጃ በእንጥልጥል ላይ እንዳለ ነው የጠቆሙት። ለውዝግቡ መፍትኄው፧ የእርሳቸው አዲስ የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን ማግኘት አለመሆኑን ያስረዱት ኦዲንጋ፧ ለሰላምና ፍትኅ በበኩላቸው ከመጣር እንደማይቦዝኑ ነው ያረጋገጡት።
«የኔ ቡድን አባላትና እኔ ለቀውሱ መፍትኄ መፍትኄ ለመሻት እንደምንጥር ለመላ ኬንያውያን ቃል እገባለሁ። ሁሉም እንዲታገሥና ሁላችንም ሁልጊዝ ለምናምንበት ሰላም፧ በወንድማማችነት መንፈስ እንዲቆም እጠይቃለሁ።«
የተጭበረበረ መሆኑ በይፋ በተነገረለት ምርጫ አሸናፊ መሆናቸውን ያሳወጁት ምዋይ ኪባኪ፧ በበኩላቸው ለህዝብ ያሰሙት ንግግር፧ ኦዲንጋ ካሉት የተለየ መልእክት ያለው አልነበረም።
«ለኬንያውያን በመላ የማቀርበው ተማጽኖ፧ እንዲረጋጉና መፍትኄ ለማግኘት በምንጥርበት ሰዓት ከሁከት እንዲቆጠቡ ነው። አንድነታችንና ቁርጠኛነታችን ፈተናውን ለመቋቋም እንደሚያስችሉን፧ እምነቱ አለኝ።«