ካርዛይና ዩናይትድ ስቴትስ
ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2006የአፍጋኒስታኑ ፕሬዝዳንት ሃሚድ ካርዛይ ከአሜሪካን ጋር የፀጥታ ውል ላለመፈረም ማንገራገራቸው በአፍጋኒስታን ላይ የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን አስከትሏል ። ወታደሮቻቸውን አፍጋኒስታን ያዘመቱት የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ NATO አባል ሃገራት ካርዛይ ውሉን በአስቸኳይ ካልፈረሙ ሃገሪቱ የሚሰጣት የእርዳታ ገንዘብ ይቋረጣል ሲሉ እየዛቱ ነው ። የሃገሪቱ የፀጥታ ጥበቃም አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ማስጠንቀቃቸውን ቀጥለዋል ። ካርዛይ ግን ያስቀመጧቸው ቅድመ ግዴታዎች ሳይሟሉ ውሉን እንደማይፈርሙ አስታውቀዋል ። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ NATO የአፍጋኒስታኑ ፕሬዝዳንት ሃሚድ ካርዛይ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የፀጥታ ውል በአስቸኳይ እንዲፈርሙ ግፊቱን አጠናክሯል ። ይህ አጠቃላይ የፀጥታ ጥበቃ ውል አብዛኛዎቹ የውጭ ኃይሎች አፍጋኒስታንን ለቀው ከሚወጡበት እጎአ ከ 2014 በኋላ የአሜሪካን ወታደሮች አፍጋኒስታን መቆየት የሚያስችላቸው ስምምነት ነው ። ዩናይትድ ስቴትስና የNATO ባለሥልጣናት በተቻለ ፍጥነት አፍጋኒስታን ውሉን እንድትፈርም ይፈልጋሉ ። ይህ ተግባራዊ ካልሆነ ወደፊት በአፍጋኒስታንን ለማከናወን የታቀዱትን ሥራዎች እንደሚታጎሉ NATO እያስጠነቀቀ ነው ። የNATO ዋና ፀሃፊ አንደርስ ፎግ ራስሙሰን ከትናንት በስተያ ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ እንደተናገሩት ካርዛይ ውሉን አለመፈረማቸው መዘዞች አሉት ።
« ህጋዊ ስምምነቱ ካልተፈረመ ወታደሮችን አይሰፍሩም ፤ የታቀደው ድጋፍም ችግር ላይ መውደቁ አይቀርም ። »
ይሁንና የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት ሃሚድ ካርዛይ ውሉን ለመፈረም በተደጋጋሚ ልዩ ልዩ ቅድመ ግዴታዎችን ከማስቀመጣቸውም በላይ ስምምነቱን በሚያዚያ በሚካሄደው ምርጫ ለሚተካው ፕሬዝዳንት እንደሚተዉ አስታውቀዋል ። የአፍጋኒስታንና የዩናይትድ ስቴትስ ውል የተዘጋጀው አንድ ዓመት ከፈጀ ውዝግብና ጭቅጭቅ በኋላ ነበር ። ከዚያን ወዲህ ካርዛይ ውሉን ከመፈረማቸው በፊት ተጨማሪ ቅድመ ግዴታዎችን አቅርበዋል ። ከነዚህም መካከል በኽዋንታናሞ እስር ቤት የተያዙት አፍጋናውያን እስረኞች በሙሉ እንዲለቀቁ የቤት ለቤት አሰሳን የሚያካትቱ አፍጋኒስታን ውስጥ የሚካሄዱ ወታደራዊ ዘመቻዎች እንዲቆሙ የሚሉት ይገኙበታል ። የNATO አባል ሃገር ጀርመን ካርዛይ በጊዜ መጫወታቸውን አቁመው ውሉን እንዲፈርሙ አሳስባለች ። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ አፍጋኒስታን እርዳታ ለማግኘት የሚጠበቅባትን አሟልታ መገኘት እንዳለባት አስታውቀዋል ።
« ለኛ ግልፅ ነው ። ከ2014 በኋላም አፍጋኒስታንን ለመርዳት ዝግጁ ነን ። ለዛች አገር የሚቀርበው እርዳታ እንዲቀጥል ለማድረግ ቅድመ ግዴታዎች መሟላት አለባቸው ። በመሆኑም በመንግሥታቱ መካከል ለሚፈረመው የፀጥታ ትብብር ውል የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ በአንድነት መቆም አለባቸው ። »
ካርዛይ ውሉን በመገባደድ ላይ ባለው የጎርጎሮሳውያኑ 2013 መጨረሻ ማለትም እስከ ታህሳስ 22 ፣ 2006 ዓም ድረስ ካልፈረሙ የዩናይትድ ስቴትስም ሆነ የNATO አባል ሃገራት በጎርጎሮሳውያኑ 2014 መጨረሻ ወታደሮቻችን ሙሉ በሙሉ ከአፍጋኒስታን እናስወጣለን ሲሉ እየዛቱ ነው ። ይህ ብቻ አይደለም የውጭ ኃይሎች በብዛት ከአፍጋኒስታን ሲወጡ ከ 8 ሺህ እስከ 12 ሺህ የሚደርስ አሰልጣኝና አማካሪ ኃይል አፍጋኒስታን ውስጥ ለማስቀረት የተነደፈውን እቅድም እንሰርዛለን እያሉ ነው ። ራስሙሰን እንደሚሉት ሥልጠናው አለመሰጠቱ ችግር ሊያስከትል ይችላል ።
« አፍጋኒስታን ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና የሚሰጥ ኃይል ማስፈር ካልተቻለ በሃገሪቱ የፀጥታ ጥበቃ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊያደርግ መቻሉ ያሳስበኛል ። ከዚህ በተጨማሪም አፍጋኒስታን በምታገኘው የገንዘብ እርዳታም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊኖረው ይችላል ። »
በኔቶ ባለሥልጣናት አባባል የውጭ ኃይሎች ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ከወጡ አፋጋኒስታን በየዓመቱ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የምታገኘውን 8 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ልታጣ ትችላለች ። የውሉን ሰነድ ሎያ ይርጋ የተባለው የአፍጋኒስታን አዛውንቶች ምክር ቤት ባለፈው ወር አፅድቆታል ። ካርዛይ ግን ከሚያዚያ ምርጫ በፊት አልፈርምም በሚለው አቋማቸው እንደፀኑ ነው ። በጎርጎሮሳውያኑ 2011 አሜሪካን ኢራቅ ውስጥ የተወሰኑ ወታደሮቿን ለማስቀረት የሚያስችል ውል ላይ ማግኘት ባለመቻሏ ወታደሮቿን ከኢራቅ ለማስወጣት መገደዷ ይታወቃል ። በአሁኑ ጊዜ አፍጋኒስታን የዘመተው ኔቶ መራሹ የውጭ ኃይል 84 ሺህ ይደርሳል ።
ኂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ