1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከጦር አውድማ የዋሉት ህጻናት

ሰኞ፣ የካቲት 7 2008

ወደ 250,000 የሚጠጉ ህጻናት በአስራ አራት አገራት በጦር አውድማዎች ነፍጥ አንግበው ውጊያ ላይ ናቸው። ህጻናቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸዋል። ይገድላሉ፤ ይሞታሉም። ብዙዎቹ ካለ እድሚያቸው በውትድርና የተሰማሩት ከአማጺያን ጎን ቢሆንም ከመንግስታት የጦር ሰራዊቶች መካከልም አልጠፉም።

https://p.dw.com/p/1Hvo0
Südsudan Kindsoldaten
ምስል picture-alliance/dpa/AA/S. Bol

[No title]

ከአፍጋኒስታን እስከ የአፍሪቃዊቷ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመንግስታት እና አማጽያን መካከል አዳዲስ ግጭቶች እየተወለዱ፤የነበሩትም አስከፊ እና አሰቃቂ እየሆኑ ሲሄዱ በአስቸጋሪ የጦር አውድማዎች ለአቅመ-አዳም ያልደረሱ ህጻናት ተሰልፈዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በዓለም ዙሪያ ወደ 250.000 የሚጠጉ ህጻናት በውትድርና መሰማራታቸውን አስታውቋል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚቀሰቀሱት ግጭቶች ህጻናቱ ያለውዴታቸው ለውትድርና እንዲመለመሉ እያደረጋቸው ነው ያለው የተ.መ.ድ. ያለ ፍላጎታቸው ነፍጥ ያነገቡትን ህጻናት ለመታደግ ዓለም ጥረት ማድረግ አለበት ሲልም አስጠንቅቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ ባንኪ ሙን በቅርቡ በህጻናት እና የትጥቅ ትግል ላይ ይፋ ባደረጉት ዘገባ በ20 ሀገራት በተቀሰቀሱ ግጭቶች ውስጥ ተሳትፎ ከሚያደርጉ 57 አካላት መካከል 56ቱ ህጻናትን በውትድርና እንደሚያስታጥቁ ይፋ አድርገዋል። የተ.መ.ድ የሶማሊያው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን አሸባብ ከ1,000 በላይ ህጻናትን እንዳስታጠቀ አስታውቋል። በምዕራባውያኑ ድጋፍ የሚደረግለት የሶማሊያ መንግስት ህጻናትን ለውትድርና በመመልመል ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን እየጣሰ መሆኑን የህጻናት መብቶች ተሟጋች የሆኑት ራልፍ ቪሊንገር ይናገራሉ።
«ይህ አነጋጋሪ ጉዳይ ነዉ። በእርግጥም ስለዚህ ብዙ ተብሏል። ግን በቂ አይመስለኝም። ጫና ማድረግ ካስፈለገ በደንብ ጠበቅ አድርጎ መንገር ያስፈልጋል። ወይ ጉዳዩን ተቆጣጠሩት አለበለዚያ አብረን መሥራት አንችልም ማለት ይኖርብናል። ይህም ሶማሊያንም ይመለከታል። የሶማሊያ መንግስት ልጆችን ለዉትድርና መቅጠር አላቋረጠም። ይኼ በተ.መ.ድ. ሠነድ ውስጥም ይገኛል። ሁኔታዉን ካለመረዳት የተነሳ ይመስለኛል፣ ስለዚህ ለተፈጠረዉ ነገር ኃላፊነት ወስዶ አንድ ላይ አብሮ መስራት ይኖርብናል።»
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች እስከ 16,000 የሚደርሱ ታዳጊዎችን በግዴታ በግጭቱ ማሳተፋቸውን የተ.መ.ድ. ያወጣው ዘገባ ይጠቁማል። በሱዳን በተለያዩ ጊዜያት ብቅ የሚሉ ታጣቂ ቡድኖች ህጻናትን በውትድርና ላለማሳተፍ ስምምነቶች ቢፈርሙም ተግባራዊ አያደርጉትም። ዳርፉር በርካታ የሱዳን ህጻናት ለውትድርና የሚመለመሉባት ግዛት ናት። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣው ዘገባ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ህጻናት አሁንም በሱዳን መንግስት ጦር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁሟል።
«ይኽ በሱዳን እና በተለይ ደግሞ በደቡብ ሱዳን እጅግ መጠነ-ሰፊ ችግር ነው። ግጭቱ መባባሱ እስከቀጠለ ድረስ ልጆች ፈጽሞ ጥበቃ ማግኘት አይችሉም። በደቡብ ሱዳን የተሻለ መስሎ ነበር ግን አሁን ተመልሶ በአስከፊ መልኩ ጨምሯል። ይኽ በሁለቱም ሃገራት ግጭቶች ውስጥ ተሳትፎ የሚያደርጉ ኹሉንም አካላት የሚመለከት ነው።»
ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታጣቂ ኃይሎች መካከል አስሩ ህጻናትን ለውትድርና ይመለምላሉ ተብለው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ ውስጥ ተካተዋል። አብዛኞቹ ደግሞ በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኙ ናቸው። ሔግ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት የቆሙት የቀድሞው የትጥቅ ትግል መሪ ቶማስ ሉባንጋ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ህጻናትን ለውትድርና መመልመል ይገኝበታል።
«ልጆችን ለዉትድርና መመልመል በጦር ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ቢታወቅም በአለማቀፍ ደረጃ ግን ቁጥሩ እየጨመረ ነው። ይህን በተመለከተ አለማቀፍ ስምምነቶች አሉ፣ ለአብነት ያኽል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መብት ጥበቃ ድንጋጌ እና ሔግ የሚገኘው የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የሚመለከተው የሮም ስምምነት እንደሚሉት ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን በውትድርና መቅጠር በጦር ወንጀል ያስጠይቃል።»
የናይጄሪያው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሐራም ህጻናትን ለወሲብ ባርነት በመዳረግ፤የአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮ እንዲፈጽሙ በማስገደድ እና ለውትድርና በመመልመል የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። አፍጋኒስታን፤ሶርያ፤ኢራቅ እና የመንን በመሳሰሉ አገራት በተቀሰቀሱ ግጭቶች እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ህጻናት ተገደው በውትድርና የሚያገለግሉባቸው አገራት መካከል ይገኙበታል።
እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ

Nigeria Demonstration Bring Back Our Girls in Chibok
ምስል Reuters/A. Akinleye
Afghanistan Kindersoldat Symbolbild
ምስል picture alliance/Tone Koene