1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዳፋ

ዓርብ፣ ኅዳር 9 2009

የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ ወር አለፈው፡፡ በሐገሪቱ በተደረገዉ ህዝባዊ ተቃውሞ እና አመጽ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ወጣቶች እንደመሆናቸው ድንጋጌውን ተከትሎ እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎችም ዳፋው የበረታው በእነርሱ ላይ ሆኗል፡፡

https://p.dw.com/p/2Sv0x
Äthiopien Polizei
ምስል imago/Xinhua

ከእስር እስከ ስደት-ወቅታዊው የወጣቶች ዕጣ

ከአዲስ አበባ እስከ ነጆ፣ ከሰበታ እስከ ካራት፣ ከባህርዳር እስከ ካይሮ ያሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተመሳሳይ ቋንቋ ይናገሩ ይዘዋል፡፡ የሀገራቸው መንግስት እንደ ቬንዙዌላ፣ ቱርክ እና ፈረንሳይ ሁሉ የአስቸኳይ ጊዜ አውጆ “ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን እየጣርኩ ነው” ሲል ሰምተዋል፡፡ እነርሱ ዘንድ ግን መረጋጋት ጠፍቶ  በትንሽ በትልቁ መሸበራቸው በርትቷል፡፡ ትላንት ምሽት “ደህና እደር” ብለው የተለዩት፣ ወይም ቀን አብረው ውለው የተሰነባበቱት መታሰሩን እንደዋዛ መስማት እንግዳ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ጥያቄው “ነግ የኔ ተራ ይሆን?” ነው፡፡ 

መንግስትም ሺህዎች በየቦታው መታሰራቸውን አልካደም፡፡ አሁን ክርክሩ የቁጥር ብቻ ሆኗል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም የሚከታተለዉ ቦርድ ባለፈው ሳምንት እንዳሳወቀው ከአስራ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ በላይ ሰዎች በስድስት ማቆያ ቦታዎች ታስረዋል፡፡ የአዲስ አበባ፣ ነጆ፣ ሰበታ እና ባህርዳር ወጣቶች ግን በአካባቢያቸው ያሉትን ፖሊስ ጣቢያዎች፣ የቀበሌ እና ወረዳ ጽህፈት ቤቶች፣ ትላልቅ አዳራሾች እና መሰል ቦታዎችን ቆጥረው “በእነዚህ ውስጥ ያሉትስ ከቁጥር ገብተዋልን?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

በቅርባቸው የሚመለከቱት የሚያስፈራቸው ወጣቶች አንገታቸውን ደፍተዋል፡፡ የጓደኞቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው እና ዘመዶቻቸው ዕጣ እንዳይደርሳቸው ጥንቃቄ አብዝተዋል፡፡ ይፋዊ ሰዓት እላፊ ባይታወጅም ደንገዝገዝ ሲል ከቤት መከተትን መርጠዋል፡፡ አንድ ሺህ ሰዎች ታሰረውባት እንደነበር በይፋ በተነገረላት ሰበታ የሚኖረው የ10ኛ ክፍል ተማሪ ስሜቱን አንዲህ ይገልጸዋል፡፡ 

“ኢንተርኔት ተቋርጧል፡፡ ብዙ ነገር ነው ያለው፡፡ ያው በስጋት እና ፍራቻ ላይ ነው ያለነው፡፡ በፊት ወጥተን እንደፈለግን ቆይተን እንመጣለን፡፡ አሁንም ደግሞ 12 ሰዓት ጀምሮ ወደቤት እየገባን ነው ጌዜው አስቸጋሪ ስለሆነ፡፡ ብዙ ወጣቶች፣ ብዙ ሰዎች ናቸው የተያዙት፡፡ እኔ ራሴ የማውቃቸው ወደ 20 ሰው ይሆናሉ፡፡ የስብሰባ አዳራሽ ነበር፡፡ ያው እስረኛ በብዛት ስላለ እዚያ ገቡ፡፡ ድራጋዶስ የሚባል ቢሮ አለ፤ ለእስረኛ ነው የተጠቀሙበት” ይላል የሰበታው ወጣት፡፡

እንደ ሰበታ ሁሉ እስሩ የጠናባት ምዕራብ ወለጋም ያለው ስሜት ተመሳሳይ ነው፡፡ እንደ ኮማንድ ፖስቱ መረጃ ከሆነ ከቄለም ወለጋ፣ አርሲ፣ ምዕራብ አርሲ እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች ተይዘው ጦላይ ወታደራዊ ካምፕ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ቁጥር 4‚193 ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 136ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ስሙ እንዳይጠቀስ የሚፈልገው የ28 ዓመቱ የነጆ ከተማ ወጣት በመንግስት በይፋ ከተጠቀሰው ቁጥር ባሻገር በየቀበሌው እና በጊምቢ የታሰሩ ወጣቶች በርካቶች እንደሆነ ይገልጻል፡፡ “ሰው በየጊዜው ስለሚያይዝ ቁጥራቸውን ይህን ያህል ማለት ከባድ ነው” ይላል፡፡     “አዋጁ ከወጣ በኋላ ሁሉም በፍራቻ እየኖሩ ነው፡፡ ሁሌም ማታ ማታ ቤት ገብተው ሰው ወስደው እያሰሩ ነው፡፡ ወጣቶች እና የጠረጠሯቸው ሰዎች ሁሉም እስር ቤት ነው ያለው፡፡ በየቤቱ ሁሉም በፍራቻ የሚኖር ስለሆነ ሁኔታው በጣም አስፈሪ እና አስጨናቂ ነው፡፡ 12 ሰዓት ከሆነ እንደወፍ ሁሉም ወደ ቤት ነው የሚሰበሰበው እንጂ ወደ ውጪ የሚወጣ የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ውጭ መቆየት የለም፡፡ ካገኙ ይደበድባሉ፣ ያስራሉ፡፡ መንገድ ላይ ይዘውህ፣ ማን እንደበደበህ፣ የት እንደምትታሰር አይታወቀም፡፡ ዝም ብሎ አጥንቱን ሰባብረው ነው የሚለቅቁት፡፡ ከዚህ ከተረፍህ እስር ቤት ትገባለህ፣ ትበሰብሳለህ፡፡ ሁሉም ይሄን ፈርቶ ነው በጊዜ ወደቤት የሚገባው” ሲል የየነጆው ወጣት የወቅቱን ስጋት ያስረዳል፡፡ 

Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher

ሌሎች  ወጣቶች ደግሞ ስደት ገብተዋል፡፡ ገሚሶቹ ከከተማ ወደ ገጠር ወጥተዋል፡፡ ሌሎቹ ራቅ ወዳለ ቦታ ወይም ክልል መሄድ ይሻላል ብለው አድርገውታል፡፡ የባሰባቸው መጠለያቸውን ጫካ አድርገዋል፡፡ የ29 ዓመቱ የኮንሶ ተወላጅ ገጠር ከወረዱት ይመደባል፡፡ በዞን የመደራጀት ጥያቄያችን በኃይል ተደፍጥጧል የሚለው ይህ ወጣት ለእስር ሲፈለግ ካራት ከተማን ለመልቀቅ መገደዱን ይናገራል፡፡ 

“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀድሞ እኛ ላይ የሚፈጸመውን ነገሮች ወደ አዋጁ ውስጥ ለማስገባት ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በፊት የሚደረጉብን ነገሮች ናቸው አሁን ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ ውስጥ እየተደረገብን ያለው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመጣ ጀምሮም ነገሮች ብሰው ነው የተገኙት፡፡ ወጣት እንግዲህ ቢያዝ በጣም ይቀጠቀጣል፣ ይደበደባል፡፡ በጣም አሰቃቂ ነገሮች [ይደርሱበታል]፡፡ ወንዶች ከሆኑ ብልታቸው ስር ሃይላንድ በውሃ እያሰሩ ስፖርት ያሰራሉ፡፡ በጣም ኢ-ሰብአዊ ድብደባዎች ያደርጋሉ፡፡ ወጣቶችም በየጫካው ነው ያሉት” ይላል የኮንሶው ተወላጅ፡፡ 

“የእስር እና የድብደባ፣ በጥይትም የመግደል [ነገር አለ]፡፡ ባሉበት ሰውን  በዓይን ሲያዩ በሩጫ ያልቻሉትን በጥይት ነው የሚመቱት፡፡ አጋጣሚ አምልጦ የሄደ አምልጧል፡፡ በድንጋጤ የወደቀውም ተደብድቦ ነው፡፡ ለዚያ ነው እኔ ከከተማ ራቅ ብዬ ያለሁት፡፡ ቤተሰቦቼን እስካሁን ድረስ ሳላየቸው ነው ያለሁት፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ የእኔ ጓደኞች በስልክ ብቻ ነው አንዳንዴ ጊዜ የምንገናኘው” ሲል ከካራት ከተማ ተገድዶ የወጣበትን ምክንያት ያስረዳል፡፡    

የኮንሶ ወጣቶች ከክልላቸው አልፈው ድንበር ለመሻገር ጨክነዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ካይሮ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከኮንሶ የሚነሱ ወጣቶችን መቀበል ጀምረዋል፡፡ በሀሩር ምክንያት ለወራት ቆሞ የሰነበተው የሰሃራ በረሃ የስደተኞች አደገኛ ጉዞ ከሶስት ሳምንት በፊት ዳግም ሲከፈት ካይሮን ከረገጡት ውስጥ ከኮንሶ፣ ባህርዳር እና ጎንደር የመጡ ወጣቶች ይገኙበት ነበር፡፡

ከኦሮሞ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከዓመት በፊት ከሀገሩ የተሰደደው ቶፊቅ ረሽድ በካይሮ የአሮሞ በጎ ፍቃደኞች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ለስደተኞች የምክር አገልግሎት በሚሰጠው በዚህ ማህበር የሚመዘገቡ ወጣቶች ቁጥር ማሻቀቡን ይናገራል፡፡ ባለፉት ሳምንታት የታዘበውን ቀደም ሲል ከነበረው ጋር እያነጻጻረ ይተነትናል፡፡ ከኦሮሚያ አካባቢዎች ሌላ ከባህርዳር፣ ጎንደር፣ ኮንሶ እና አዲስ አበባ የተሰደዱ ወጣቶች አነርሱ ጋር መድረሳቸውን ይገልጻል፡፡    “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጀምሮ አብዛኞቹ እየመጡ ያሉት ከኦሮሚያ ነው፡፡ ድሮ አሁን ወደ ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር [UNHCR] ለመመዝገብ የሚሄዱት በሳምንት አምስት፣ ስድስት ሰዎች ቢሆኑ ነው፡፡ አሁን ግን በጣም እየበዙ ነው፡፡ የሚገርምህ ትላንት ራሱ ስምንት ሰው አስተናግጄ የመጣሁት፡፡ አሁን ካይሮ የሚገባው ስደተኛ በሳምንት ከ70 በላይ ነው፡፡ በተለይ ከ18 [ዓመት] በላይ ከ40 በታች ያሉት ናቸው በብዛት የሚመጡት” ይላል ቶፊቅ፡፡     

Äthiopische Volksgruppe der Oromos Protest
ምስል Getty Images/AFP

ሰሃራ በረሃን በድፍረት ከሚያቋርጡት ውስጥ ሁሉም ያሰቡበት አይደርሱም፡፡ ቶፊቅ በመሃል መንገድ ስለቀሩት ኢትዮጵያውያን ሲናገር ሀዘን ተጭኖት ነው፡፡ የበረሃውን ሙቀት መቋቋም አቅቷቸው እዚያው የሞቱ እንዳሉ ሁሉ ከግብጽ የድንበር ከተማ አስዋን ሲደርሱ ጥማቸውን ለመቁረጥ ብዙ ውሃ ጠጥተው እስከወዲያኛው ያሸለቡ እንዳሉ በመቆጨት ይገልፃል፡፡
ወጣቶቹን ህይወታቸውን እስከማጣት ያደረሳቸው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መንግስት የሚመለከታቸው በሌላ መነጽር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህብረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሀገሪቱን ፀጥታ ወደ ቀድሞው ስፍራው መልሷል ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

በሀገሪቱ በነበረው ተቃውሞ 90 በመቶው ተሳታፊዎች ወጣቶች መሆናቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቁጥጥር ስር የዋሉቱ ተቃውሟቸውን የሚገልጹበት ምቹ ምህዳር አለመኖሩን በግልጽ መናገራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት መንግስት የዴሞክራሲ ተቋማትን የማሳደግ ስራ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡ ወጣቶቹ ግን መጪው ጊዜ “ያበጠው የሚፈነዳበት” እንደሆነ ይተነብያሉ፡፡

“ከዚህ በላይ ሀገሪቱን አደጋ ላይ ይጥላል ብዬ ነው የምለው፡፡ ለምንድነው? አሁን አየኖሩ ያሉት የባለስልጣን ሰዎች ናቸው እንጂ ህዝቡ እየኖረ አይደለም፡፡ ህዝቡ እንዲህ ተጨቆኖ ከቆየ ወደ ባለስልጣናት ይመጣሉ፡፡ ከዚያ ግጭት ይፈጥራሉ ብዬ አስባለሁ” ሲል የየነጆው ወጣት በሌሎች ዘንድም የሚቀነቀነውን ሀሳብ ያጋራል፡፡ 

 የኢትዮጵያ ወጣቶች መጪው ጊዜ ብሩህ አንዲሆን ከተፈለገ መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ የወሰዳቸውን ዓይነት እርምጃዎች እርግፍ አድርጎ ጥያቄያቸውን በአግባቡ ይፈታ ዘንድ ይጠይቃሉ፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ