የግንባታ መሣሪያዎች ቁጥጥር
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 19 2009በኢትዮጵያ የግንባታዉን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ በሚል በግንባታ ሥራ ለተሰማሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከቀረጥ ነጻ የግንባታ እቃዎችን ወደ ሀገር ዉስጥ ማስገባት የተፈቀደ ነዉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች እድሉን በመጠቀም የሚያስገቧቸዉን የግንባታ መሳሪያዎችና ተሽከርካሪዎች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ለገበያ እንደሚያቀርቡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ይገልጻሉ። ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ አስተያት ሰጭ እንደሚሉት በግንባታዉን ዘርፍ የተሰማሩ አንዳንድ ባለሀብቶች ከቀረጥ ነጻ የሚያመጧቸዉን እቃዎች ወደ ገበያ በማስገባታቸዉ በሕጋዊ መንገድ ቀረጥ ከፍለዉ የሚሰሩትን እየጎዳ ነዉ።ጉዳዩን በተመለከተ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸዉ በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱራህማን ጀማል ችግሩ ሊኖር እንደሚችል ገልጸዉ ፤ በሚንስቴር መስሪያቤቱ አዲስ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ምዝገባና ቁጥጥር ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ከ 19 ዓመት በፊት በነበረ አዋጅና ደንብ አሁን ካሉ የግንባታ መሳሪያወችና ተሽከርካሪወች ነባራዊ ሁኔታ ያልተጣጣመ ስለነበር ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።
ስለሆነም ብዙዎቹ የግንባታ መሳሪያዎች ምዝገባ ሳይደረግባቸዉ ወደ ግንባታ ይሰማሩ ስለነበር በሕገ ወጥ መንገድ የግንባታ መሳሪዎቹን ወደ ገበያ ለማስገባት በር እንደከፈተ ገልጸዉ አሁን የሚወጣዉ ደንብ ግን ችግሩን እንደሚመልሰዉ አብራርተዋል።የኮንስትራክሽን እቃዎችን በአግባቡ መዝግቦ ለታለመላቸዉ ዓላማ መዋሉን ለመቆጣጠርም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮንስትራክሽን ኦዲት ክፍል መቋቋሙን ገልጸዋል። በዚህ ክፍል አማካኝነትም የሚሰሩ ግንባታዎችን ከንድፍ ሥራ ጀምሮ በመቆጣጠርና ክትትል በማድረግ ለግንባታዉ የሚያስፈልገዉን የግብአት መጠንና የግንባታ እቃዎች በባለሙያ እንዲወሰን በማድረግ ከፍጆታ በላይ የሆኑ የግንባታ መሣሪያወች ከቀረጥ ነጻ እንዳይገቡ መቆጣጠር ይቻላል ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።ባለሃብቶቹ ከሕግና ከደንቡ ዉጭ መንግስት የሰጣቸዉን ማበረታቻ በአግባቡ የማይጠቀሙና እድሉን ላልተገባ ጥቅም የሚያዉሉት ከሆነ በሕግ ሊጠየቁ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ