ከስደተኝነት እስከ ምክር ቤት አባልነት
ማክሰኞ፣ ኅዳር 25 2005
አሁን ለደረሱበት ሃላፊነት በመብቃት በጀርመን የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ናቸው ። ከ20 አመት በፊት ተገን ጠይቀው መኖር በጀመሩባት በጀርመን የህዝብ እንደራሴ የሆኑት የኮንጎው ተወላጅ ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ማንነታቸውንና እንዴት ፖለቲከኛ ለመሆን እንደበቁ ያስቃኘናል ።
ብሬመን በሰሜን ምዕራብ ጀርመን የምትገኝ የንግድና የኢንዱስትሪ ከተማ ናት ። በህዝብ ብዛት ከሰሜን ጀርመን ግዛቶች ሁለተኛውን ደረጃ ላይ ስትገኝ ከጀርመን ደግሞ 10 ኛ ቦታን ትይዛለች ። ከሰኔ 2004 አም አንስቶ ኤሎምቦ ቦላዬላ የክፍለ ግዛትነት ደረጃ ያላት የብሬመን ከተማ ምክር ቤት አባል ናቸው ። የ27 አመት ወጣት ሳሉ ነበር ከትውልድ ሃገራቸው ኮንጎ በያኔው አጠራሯ ከዛየር ወደ ጀርመን የተሰደዱት ። ጀርመን የመጡትም እጎአ በ1992 ነው ። ያኔ ተገን ጥየቃ ጀርመን የገቡት ቦላዬላ ከዛሬ 13 አመት አንስቶ የህንፃ ግንባታ መሣሪዎች መደብር የሽያጭ ክፍል ውስጥ ነው የሚሰሩት ። በጀርመን ከውጭ ዜጎች በእጅጉ የሚጠበቀውን ከህብረተሰቡ ጋር ተመሳስሎና ተቀራርቦ መኖርን ተግባራዊ አድርገው የብሬመን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ምክር ቤት አባል እስከ መሆን የደረሱት ቦላዬላ አሁንም የቀድሞው ሥራቸውን አልተዉም ። ወደ መደብሩ ጎራ ያለ አያጣቸውም ። ሰዉ ሁሉ ያውቃቸዋል ፤ ያደንቃቸዋልም ። ቦሎዮላ በተወከሉበት በብሬመን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በጀርመን የምክር ቤት መቀመጫ በመያዝ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ጀርመናዊ ናቸው ። ቦሎዮላ በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እሆናለው ብለው አልመውም አያውቁም ። ፓርቲያቸው ሶሻል ዲሞክራት በብሬመን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ለውድድር ካቀረባቸው ሰዎች ውስጥ የርሳቸው ስም ወደ ኋላ የሰፈረ ቢሆንም የብሬመን ህዝብ ስለፈለጋቸው መርጧቸዋል ። በቀጥታው ድምፅ አሰጣጥ ጥሩ ውጤት ካመጡት 6 የፓርቲያቸው እጩ ተወዳዳሪዎች አንዱ ለመሆን ቻሉ ። ቦሎዮላ እንደሚሉት ለዚህ ያበቃቸው ከሰዎች ጋር ያላቸው መልካም ግንኙነት ነው ።
« ከህዝቡ ጋር ጥሩ ተሞክሮ አለኝ ። ህዝቡ ፣ ስለ እኔ በጎ አመለካከት ነው ያለው ። ምናልባት ይሄ ደግሞ « ሁሉም ሰዎች ጥሩ ናቸው በሚለው በኔ አመለካከት ምክንያት ሊሆን ይችላል ። ያንንም አሳያለሁ ። መናገር የምችለው ከሞላ ጎደል አዎንታዊ ይዘት ያላቸው መሆናቸውን ነው ። »
የኮንጎው ተወላጅ ቦሎዮላ የህዝብ እንደራሴ ቢሆኑም አጀማመራቸው ግን ቀላል አልነበረም ። የትውልድ ሃገራቸውን ዛየር የአሁኗ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክን ከዛሬ 20 አመት በፊት ለቀው የወጡት ያለ ምክንያት አይደለም ። ያኔ በሥልጣን ላይ የነበሩት አምባገነኑ ሞቡቱ ሴሴሴኮ ለሃገሪቱ የረባ ነገር ባለመሥራት ኤኮኖሚዋን በማንኮታኮት የህዝቡ የኑሮ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል በማድረግ ስማቸው የሚነሳ መሪ ነበሩ ። ቦሎዮላ እጎአ በ1990 የሞቡቱ ሴሴኮን አገዛዝ በመቃወም ይካሄድ በነበረው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ተሳታፊ ነበሩ ። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ ምክንያት የሆናቸውም ተማሪ ሳሉ ከመምህራቸው ያገኙት ማብራሪያ ነበር ። ከመካከላችን
« ተማሪ ሳለሁ እጎአ በ1991 ነበር ዲሞክራሲ የሚለው ቃል መኖሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ። ያኔም መምህሬን ምን ማለት ነው ብዮ ጠየቅኋቸው ። እርሳቸውም አንድን አገር የሚያሳድግ ጥሩ የፖለቲካ ስርዓት ማለት እንደሆነ ፤ እያንዳንዳችን ሚኒስትር ወይም መምህር የመሆን እድል እንዳለን ፣ ተጨማሪ መንገዶች ሊሰሩልን እንደሚችሉ በግልፅ ነገሩኝ ። »
ይህ ገለፃም የወጣቱን የቦሎዮላ ልብ አነሳሳ ።እጎአ የካቲት 16 ፣ 1992 እሁድ እለት በሺህዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ሞቦቱን በመቃወም ሰልፍ ወጡ ። የታቀደው ሠላማዊ ሰልፍ እንደመሆኑ ህዝቡ ሲዘምር በዋና ከተማይቱ ኪንሻሳም ዝማሬው ያስተጋባ እንደነበር ቦሎዮላ ያስታውሳሉ ። ሆኖም የሰልፉ መጨረሻ አላማረም ። ደም ፈሰሰ ። ወታደሮች ተኩስ ከፍተው ቁጥራቸው ወደ 200 የሚጠጉ ሰልፈኞች ተገደሉ ። ቦሎልያም ተተኩሶባቸው ቆሰሉ ። በቀናት ውስጥ ሃገራቸውን ጥለው ሸሹ ። በሞስኮ በኩል አድርገው ጀርመን ገቡ ። ግን ጀርመን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም ። የመጀመሪያዎቹን አመታት ከዛሬ ነገ ወደ ሃገሬ እባረራለሁ ከሚል ስጋት ጋር ነበር ያሳለፉት ጀርመን የመቆየት መብታቸውን ለማስከበር 5 አመታት ወሰዶባቸዋል ። ጀርመን የመኖር ፈቃድ እስኪያገኙ ድረስ አንዳንዴ ማመልከቻቸው ተቀባይነት ሲያጣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የመቆያ ፈቃዳቸው እንደገና ሲራዘምላቸው ነው የቆዩት ። የ 3 ሺህ መራጭ ድምፅ አግኝተው ተመረጡ
በተወሳሰቡ መንገዶች ከሃገር የወጡት ቦሎዮላ በመጨረሻ ጀርመን ገቡ ። እንደ ተገን ጠያቂ ጀርመን የመቆየት መብታቸውን ለማስከበር ለአመታት ታግለዋል ። ከጎናቸው የቆመው ህዝብ ፣ በቤተክርስቲያንና በቤተክርስቲያን መዝምራን ቡድን ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጀርመን እንዲቆዩ ምክንያት እንደሆናቸው ይናገራሉ ።
አትሞ ,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
በትውልድ ኮንጎዋዊው ቦሎዮላ የመዘምራኑን ቡድን አቋቁመው በፖለቲካውም መሳተፍ ጀመሩ ። የውጭ ዜጋ ለሆኑ ተማሪዎች የተሻለ እድል የሚሰጥ ህግ እንዲወጣ ያቀረቡት ሃሳብ በብሬመን ፌደራዊ ምክር ቤት በሚገኙ የሥራ ባልደረቦቻቸው ዘንድ አድናቆት አትርፎላቸዋል ። በብሬመን የ ፓርቲያቸው የ SPD ፖለቲከኞች ያመሰግኗቸዋል ። በብሬመን ፌደራዊ ምክር ቤት የጀርመን ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ ሊቀመንበር ብዮርን ሸፐ ስለ ቦሎዮላ በጎ አስተያየት ነው ያላቸው ።
« የተለያዩ ሰዎች የሚገኙበት ቡድን ነው ። የተለያየ መነሻ ያላቸው ሰዎች ከሚገኙበት ቡድን ውስጥ ቦሎዮላ ቦታቸውን አግኝተዋል ። በመካከሉም የቡድኑ ሙሉ አባል ሆነዋል ። እስካሁን ሁሉም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው ። »
ሞቡቱ ከሞቱ 15 አመታት ተቆጥረዋል ። ሃገሪቱም የህግ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ መስመር ለመከተል እየሞከረች ነው ። ቦሎዮላም ካሉበት ከጀርመን የኮንጎን ሁኔታ ይከታተላሉ ። ህዝባቸው ምን ያህል ለአመታት በፖለቲከኞች ጭቆና ሥር እንደቆዩና የመንግሥት ባለሥልጣናትም አለአግባብ ሥልጣናቸውን ይጠቀሙ እንደነበር ታዝበዋል ። በቦሎዮላ እምነት ዲሞክራሲም ሆነ ፖለቲካ በቅጡ ሊጤን ይገባል ።
« ዲሞክራሲ ጨዋታ አይደለም ። ፖለቲካ ምኞት አይደለም ፤ እውነታውን መጋፈጥ እንጂ ።አማራጮችን ማወቅ ያስፈልጋል ፤ ገላጋይ ሃሳቦችንም ማመር እንዲሁ ። »
በኮንጎ ለውጥ ማምጣት ቦሎዮላ ለጊዜው ትኩረት የሰጡት ጉዳይ አይደለም ። ያ ከአሁን ወዲያ የርሳቸው አለም ሊሆን አይችልም ። ሆኖም ይላሉ የተወለዱበት የኖሩበት ሃገር መሄዳቸው አይቀርም ። የ SPD ው ፖለቲከኛ ቦሎዮላ ሲክ በተባለችው ከተማ የአናፂነት ሙያ ትምሕርት አጠናቀዋል ። ትምህርታቸውን ባጠናቀቁ በአመቱ በአንድ የግንባታ መሣሪዎች መደብር ውስጥ መሥራት ጀመረ ። እዚያ ሳሉም የሠራተኞች ማህበር ውስጥ ከ 2003 ጀምሮ በትጋት ሲሳተፉፍ ከቆየ በኋላ በ2009 የሠራተኞች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ ። በዚህ ጊዜም የኦዝለብስሃውዘን ከተማ የአንድ አካባቢ የ SPD ማህበር አባል ሆኑ ። በ 2011 የክፍለ ግዛትነት ደረጃ ላላት የብሬመን ከተማ ምክር ቤት አባልነት ከ41 እጩዎች ጋር ተወዳድረው በምክርቤቱ መቀመጫ ለመያዝ በቁ ። አሁን በምክር ቤቱ የውጭ ተወላጆች ከጀርመን ህብረተሰብ ጋር ተመሳስለው የሚኖሩበትን ጉዳይ የሚከታተል ፣ የፌደራልና የአውሮፓ ጉዳዮች አለም አቀፍ ግንኙነት የልማት ትብብር ኮሚቴ ተወካይ ናቸው ,። ሳሙኤል ቦሎዮላ በተባለው የሙዚቃ ስማቸወ የሚታወቁት ቦላዮላ በትርፍ ጊዜያቸው ከበሮ ይመታሉ ። እጎአ በ 2002 አም በመሰረቱት ድንበር አልባ በተባለው የመዘምራን ጓድ ውስጥም ይሳተፋሉ ።
ኤሎምቦ ቦላዬላ «ለጊዜው መቆም ተቀባይነት ይኖረዋል ሆኖም እስከ ለዘላለሙ መቀመጥ ግን ሐጢአት ነው» ይላሉ ። በጀርመን የውጭ ዜጎች ከህብረተሰቡ ጋር ተመሳስለው ለመኖር ፣ ሥራ አጥ ላለመሆን ፣ አድልኦንም ለመከላከልና የተሻለ የትምህርት እድል ለማግኘት የውሳኔ ሰጭ አካል መሆን ነው የተሻለው አማራጭ ። ርሳቸው እንደሚሉት ከውጭ ሆኖ ለውጥ የማምጣቱ እድል ዝቅተኛ ነው ። የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በቦላዬላ እምነት ቀጥተኛ ተሳታፊ ከሆኑ ብቻ ነው ። ስለዚህ ይላሉ ቦላዬላ ሰዎች በፖለቲካ እንዲሳተፉ ማበረታት ይገባል ። ቦላዬላ እጎአ ታህሳስ 28 ፣ 1965 ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ነው የተወለዱት ። አባታቸው የወንጌላዊያን ቤተክርስቲያን ሰባኪ ናቸው ። በ1998 ካገቧቸው ከባለቤታቸው አንጌላ ቦላዬላ ማርክዋርት 5 ልጆች አፍርተዋል።
ሂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ