1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ ሙሉጌታ

ዓርብ፣ ግንቦት 11 2009

አዲስ ሙሉጌታ በጀርመን ሀገር ጥገኝነት ጠይቆ የሚኖር  ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ነው። ዛሬ ሌሎች ስደተኞች ከሀገሬው ሰው ጋር ተዋህደው እንዲኖሩ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል። ላበረከተው በጎ አድራጎትም በሚኖርበት ከተማ የሰላም ተሸላሚ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/2dC8R
Addis Mulugeta
አዲስ ሙሉጌታምስል Privat

ከሕብረተሰቡ ጋር ተዋህዶ መኖር ስኬታማ ሲሆን

በአሁኑ ወቅት የጀርመን ፖለቲከኞችን ከሚያሳስቡ ጉዳዮች አንዱ የስደተኞች ጉዳይ ነው።በተለይ ጀርመን የገቡ ስደተኞች የሚያኖሩበት ቦታ እና  ከሀገሬው ሕዝብ ጋር ቶሎ ተዋሕደው እንዴት መኖር ይችላሉ የሚለው ጥያቄ ያሳስባቸዋል። ስደተኝነትን ራሱ የቀመሰው ኢትዮጵያዊው አዲስ ሙሉጌታ ምላሽ አለው። ኢትዮጵያ በነበረበት ወቅት የእንግሊዘኛ መምህር ኋላም ጋዜጠኛ ሆኖ አገልግሏል። በዚህ ጀርመን ደግሞ ከመጣ ብዙም ሳይቆይ « ሀይም ፎከስ» የተባለ መፅሄት አቋቁሟል። በዚሁ መፅሔት ላይ ሌሎች ስደተኞች እና ራሱ አዲስ ይፅፋሉ። ጸኃፊዎች የሚያነሱዋቸው ሀሳቦችም በህዝቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድም ተቀባይነት አግኝተዋል። የስደተኞች መብት እና ህጎችም እንዲቀየሩ የበኩላቸውን አስተዋፅዎ አድርገዋል።ዛሬ ማንኛውም ስደተኛ በመላው ጀርመን መንቀሳቀስ ይችላል። ቋንቋም ሆነ በማንኛውም የከፍተኛ ተቋም ለመማር ብቃት ያለው ሰው መማር ይፈቀድለታል።

Projekt Digital Empowerment für afghanische Flüchtlinge
ጀርመን ውስጥ ባለፉት ሁለት አመታት በርካታ የሶርያ እና የአፍጋኒስታን ስደተኞች ተገን ጠይቀዋልምስል Getty Images/S. Gallup

አዲስ ይህንንም እድል ተጠቅሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን 2ኛውን ዲግሪ ይዟል። ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ ከመፅሔቱ በተጨማሪ እዛው ቩርዝቡርግ ከተማ ስደተኞች እና ጀርመኖች ተገናኝተው ሀሳብ የሚለዋወጡበት ካፍቴሪያም አቋቁሟል። ለዚህ ስራውም በአንድ አመት ውስጥ የቩርዝቡርግ ከተማ የሰላም ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። ዛሬ ቩርዝቡርግ በምትባለው የጀርመን ከተማ መዘጋጃ ቤት ውስጥ ይሰራል። እዛም በብዛት ከሶርያ፣ ከአፍጋኒስታን እና ከዩክሬይን የመጡ እና ወደ ከፍተኛ ተቋም መግባት የሚፈልጉ ስደተኞችን ይረዳል። መንገዱ ራሱ ያለፈበት ስለሆነ በሌሎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው።

Würzburg Reportage Flash Galerie 114
የቩርዝቡርግ ከተማ ምስል DW / Maksim Nelioubin

የ 33 ዓመቱ አዲስ ሙሉጌታ ካለፈው ዓመት አንስቶ ገበያ ላይ የዋለ መፅሀፍም አሳትሟል። ታሪኩም በራሱ እና በሌሎች የውጭ ሀገር ዜጎች የግል ታሪክ እና ተሞክሮ ላይ የተመረኮዘ ነው። ጀርመን ውስጥ ከፍለ-ግዛት፤ ክፍለ ግዛት ለስደተኞች ያለው አመለካከት ይለያይ እንጂ በአጠቃላይ ሀገሪቷ ለስደተኞች ብዙ ሕጋዊ መብት እና እድል ትሰጣለች።  ይህንንም እድል የተጠቀመው እና ዛሬ በሚገባ ከጀርመኖች ጋር አብሮ ለመኖር በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችለው ኢትዮጵያዊ አዲስ መጤዎች ማድረግ አለባቸው የሚለዉ አለ። አንደኛው ቋንቋ መማር ሲሆን ሌላው ወደ ጀርመን ለሚመጡ ስደተኞች ወሳኙ ነገር መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንዳለ ማወቁ ነው።

ከአዲስ ሙሉጌታ ጋር የነበረንን ቆይታ በድምፅ ያገኙታል።

 ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ