1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከለንደኑ የቡድን ሀያ ጉባዔ ምን ይጠበቃል?

ረቡዕ፣ መጋቢት 23 2001

በዋሽንግተን የመጀመሪያው የዓለም ፊናንስ ጉባዔ በዋሽንግተን ከተደረገ ከአራት ወራት በኋላ በነገው ዕለት በለንደን የሚካሄደው ሁለተኛው የቡድን ሀያ ሀገሮች ጉባዔ ዓለም አቀፉን የፊናንስ አውታር ለዘለቄታው ማጠናከር የሚቻልበትን ተጨባጭ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/HOU5
የአውሮፓው ኅብረትና ባጠቃላይ የቡድን 20 አባል አገሮች፣ምስል AP / CC_Marcin n_nc

ዋነኞቹ ኢንዱስትሪ እና በፈጣኑ የዕድገት ጎዳና ላይ የሚገኙት ሀያ የዓለም ሀገሮች ያሳልፉታል የሚባለው ውሳኔ በወቅቱ የተከሰተው ዓይነት የፊናንስ ቀውስ እንዳይደገም ያከላክላል ተብሎ ይታስቦዋል። ለፊናንሱን ቀውስ መፍትሄ ለመሻት እስካሁን ስለተደረገውና በለንደኑ ጉባዔም ይወሰዳል ስለሚባለው ርምጃ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ሄንሪክ በመ ላጠናቀረው ዘገባ አርያም ተክሌ፡

የቡድን ሀያ ሀገሮች ተደራዳሪዎች ባለፈው ህዳር አምስት በዋሽንግተን ጉባዔ ላይ በወጣው የተግባር ዕቅድ ላይ የሰፈሩት አርባ ሰባት ተጨባጭ ርምጃዎች ተግባራዊ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ሲደራደሩ ቆይተዋል። በተግባሩ ዕቅድ ውስት ከተጠቃለሉት ርምጃዎች መካከል ለተሻለ ዓለም አቀፍ የፊናንስ አውታር አስፈላጊው የመቆጣጠሪያውና በዋና ስራ አስኪያጆች ደሞዝ አከፋፈልም ላይ አዳዲስ ደምቦች ይውጡ የተባሉበት ሀሳቦች ይገኙባቸዋል። በታሪካዊው የዋሽንግተኑ ጉባዔ መሰረት፡ ከነዚህ ከቀረቡት ሀሳቦች መካከል ብዙዎቹ እስከትናንቱ ዕለት ድረስ በተግባር እንዲተረጎሙ ዕቅድ ነበር። በዚህም የተነሳ ታድያ የአውሮጳ ህብረት፡ የተመድ ወይም የደቡብ ምስራቅ እስያ መንግስታት የትብብር ድርጅት፡ ሁሉም የወደፊቱ የፊናንስ መዋቅር ምን ዓይነት መልክ መያዝ ይገባዋል ለሚለው ጥያቄ የበኩላቸውን መልስ ለማግኘት ሲጥሩ ሰንብተዋል። እንደ ጀርመናዊትዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ግልጹ የመቆጣጠሪያ ደምብ ወሳኝ ርምጃ ሊሆን ይችላል።

« የፊናንስ ገበያዎች በጠቅላላ፡ ምርቶችና ተሳታፊዎች፡ ለኪሳራ የተጋለጡት አክስየኖች፡ ተማኝ ወኪሎችና ሌሎች የግል አክስየን አቅራቢዎች ጭምር ቁጥጥር ሊደረግባቸውና መተዳደሪያ ደምቦችንም ሊያከብሩ ይገባል ብለን እናምናለን። ለዚህ አሰራር ገሀዳዊነትም የሚያስፈልጉት ዝርዝሮች ከወዲሁ መዘጋጀት እና የተግባሩ ዕቅድ ከፊል መሆን ይኖርባቸዋል። »

የአውሮጳ ማዕከላይ ባንክ ፕሬዚደንት ዣን ክሎድ ትሪሼ ደግሞ በፊናንሱ አውታር ላይ አጠቃላዩ ለውጥ ያስፈልጋል ባይ ናቸው፤ ምክንያቱም፡ አሁን የተከሰተው የፊናንስ ቀውስ በወቅቱ የሚሰራበት የፊናንስ አውታር በጠቅላላ ሊንኮታኮት የተቃረበና ትልቅ ችግር ሊቋቋም የማይችል መሆኑን አሳይቶዋልና።

የዋሽንግተኑ የተግባር ዕቅድ ማዕከላይ ነጥብ በፊናንሱ ገበያ ላይ ግልጹና ጠንካራው ተጠያቂነት የታከለበትን ግዴታ የማወቁ አሰራር ሊሻሻል ይገባል የሚሰኘው ነው። የፊናንስ ተቋማት፡ ለምሳሌ፡ ወረትና ለክስረት ለተጋለጡት አክስየኖች የሚያስፈልገውን የመክፈል አቅም በተመለከተ ከመጀመሪያው ንዑሱን ደምብ ማውጣት ይኖርባቸዋል። ይህ ግን የተቋማቱ መንበሮች ባሉባቸው ሀገሮች ውስጥ ሳይሆን አክስየኖቹ ለገበያ በሚቀርቡባቸው ሀገሮች ውስጥ ነው መውጣት የሚኖርበት። ይህ የማንቀሳቀሻው ገንዘብ የመቆጣጠሪያ ደምብ በወደሌለባቸውና ተጠያቂነት ወደተጓደለባቸው የካይማን ደሴቶችን ወደመሳሰሉ ቦታዎች የሚሸሽበትን አሰራር ያበቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በተለይ ለአሜሪካውያንና ለብሪታንያውያን መራራ ተሞክሮ ሆኖባቸዋል። ምክንያቱም፡ ሌሎች ባለፉት ጊዚያት ልጓም ያጣው ከበርቴያዊው ስርዓት የሚያስከትለውን ስጋት ሲጠቁሙ ሁለቱ ሀገሮች ጥቆማውን እንደዋዛ ነበር ያለፉት። ዛሬ ግን ሁኔታዎች ተለዋውጠው፡ አዲሱ የዩኤስ አሜሪካ ገንዘብ ሚንስትር ቲመቲ ጋይትነር ስለፊናንሱ ቀውስ ሲናገሩ ለየት ያለ አስተያየት ነው የሚሰማው።

« ለኪሳራ የመጋለጡን ሁኔታ ብሄራዊ ድንበሮች አይገድቡትም። በዓለም አቀፉ የፊናንስ አውታር ውስጥ እኩል የሚሰራበት በጣም ግልጽ የሆኑ የመቆጣጠሪያ መመሪያዎች እና ግልጽ ደምቦችን ማውጣት ይገባናል። ለዚህም በብሄራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረግ አንድ አጠቃላይ ለውጥ ያስፈልጋል። »

ይህን በተመለከተ ጀርመን ስጋት ይደቅናሉ የሚባሉ የገበያ ተሳታፊዎችና የፊናንስ ምርቶችን፡ ሲያስፈልግም የማስጠንቀቂያዎቹን ምልክቶች የሚያሳይ ካርታን ደጋግማ አቅርባለች። ከአንድ የተወሰነ የገንዘብ ብድር ያለፈ የብድር መጠን የሰፈረበት የዝርዝር መዝገብም ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ካርታ እንዲያጎለብትም ሀሳብ አቅርባለች። እርግጥ ለዚህ አስፈላጊ የሆነውን መረጃ መሰብሰቡ አዳጋች ሊሆን ቢችልም፡ በመጨረሻ አዲስ የዓለም የፊናንስ አውታር መቋቋምን ያስገኛል። ለዚህም ወሳኙ ርምጃ በነገው ዕለት በለንደን በሚከፈተው የቡድን ሀያ ጉባዔ ላይ እንደሚወሰድ ጀርመናዊትዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ከጥቂት ቀናት በፊትከብሪታንያዊው ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራውን ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ ተስፋቸው ገልጸዋል። የአውሮጳ ህብረት ኮሚስዮን ፕሬዚደንት ኾዜ ማኑዌል ባሮዞም ቢሆኑ ተመሳሳዩን ብሩህ አመለካከት ነበር ያሰሙት።

« ዛሬ ማህበራዊውን የገበያ ኤኮኖሚ መመሪያን መሰረት ላደረገ ዓለም አቀፍ የገበያ ኤኮኖሚ የሚበጀውን አዲስ የፊናንስ መተዳደሪያ መሰረትን መጣል ጀምረናል። የዚሁ ንቅናቄ ጀማሪም የአውሮጳ ህብረት ነው። »

ይህ ዓይነቱ ብሩህ አመለካከት በርግጥ ተግባር ሊተርጎም መቻል አለመቻሉ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። የሂሳብ ማወራረጃ ሰነዶች፡ የግል ወረት ቁጥጥር፡ የተቆጣጣሪ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ትብብርን በተመለከተ የፊናንስ ጠበብት በዓለም አቀፍና በብሄራዊ ደረጃ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የተወሳሰቡ ዝርዝሮችን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ አንጻር ዓለም አቀፉን የገንዘብ መርህ ድርጅት፡ አይ ኤም ኤፍን የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትአዲስ ሚና ግልጽ ሆኖ ቀርቦዋል። ለምሳሌ፡ አይ ኤም ኤፍ ቀውስ ከመከሰቱ በፊት አዝማሚያውን አስቀድመው በመገምገሙ ረገድ ጠንካራ ሚና እንዲይዙ ተወስኖዋል። በዚሁ መሰረትም፡ ቀውስ ለማስወገጃው ተግባር የሚያገለግል ተጨማሪ አምስት መቶ ሚልያርድ ዶላር የሚቀርብላቸው ሲሆን፡ ከዚሁ ገንዘብ ለምሳሌ ቀውስ ለገጠማቸው ሀገሮች ብድር ሊሰጡ ይችላሉ።

ሄንሪከ በኧመ፣

አርያም ተክሌ፣

ተክሌ የኋላ፣

Tekle Yewhala