1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እግር ኳስ ተጫዋቹ ዳዊት በሻህ

ዓርብ፣ ጥር 17 2005

ዳዊት በሻህ ለሶስት ሳምንት ያህል ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋ ሲለማመድ ቆይቷል። ለብሔራዊ ቡድን ተጫዋችነትም ታጭቶ ነበር።

https://p.dw.com/p/17Qsj
Bild 2 Dawit Beshah trainiert mit Euskirchner TSC 2012 Zulieferung : Lidet Abebe
ምስል www.paulduester.com

ባለፈው ሰኞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋ ደቡብ አፍሪቃ ላያ ያካሄደዉን ጨዋታ ዳዊት በሻህ ከዚሁ ከጀርመን ተከታትሎታል። « ከወንድሜ ጋ ሆኜ ነው የተከታተልኩት። ቀይ ካርድ አግኝተውና ወደ ኋላ ቀርተው እንደነበር ከግምት ስንከት፤ አንድ ለአንድ መውጣት ጥሩ ውጤት ነው። ጥሩ ተጫውተዋል። የመጀመሪያውን ግጥሚያ አለመሸነፍ ወሳኝ ይመስለኛል።»

ከኢትዮጵያዊ አባት እና ከጀርመናዊ እናት የተወለደው ዳዊት «ኦይስኪርሽነር TSC» ለሚባል የጀርመን የእግርኳስ ቡድን ይጫወታል። ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያውያኖች ለሚጫወቱበት ለጀርመኑ ኢትዮ-ኮሎኝ እና የቶሮንቶው ቡድን።ታድያ ዳዊት ከሁለት ወር በፊት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመሰለፍ እድል አግኝቶ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ ከሌሎቹ ተጫዋቾች ጋ ሲሰለጥን ቆየ። የ25 ዓመቱ ወጣት ደቡብ አፍሪካ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ስለሚሰለፍበት ግጥሚያ ሲያስብ ግን ያልጠበቀውን ነገር ሰማ። ከዚያም ጉዞው ወደ ጀርመን ሆነ። ለምን? «ጥሩ ጥያቄ ነው። ለመመለስ ግን ቀላል አይደለም። ከስፖርት ያለፈ ብዙ ነገሮች ሚና የተጫወቱ ይመስለኛል። የተነገረኝ ክለቡ እንዳልጫወት መወሰኑን ነው። ምክንያት ሊኖራቸዉ ይችላል። እኔ ግን አልገባኝም። ያልጠበኩት ቢሆንም የተባለዉን መቀበል ነው።»

ዳዊት እና የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በአንድ ላይ የተነሱት ፎቶዎች በአዲስ አበባ በየቦታው ተለጥፈው ይገኛሉ። አለመጫወቱን ዳዊት ሲሰማ ዜናውን እንዴት ተቀበለው?

«አዎ ኀዘኑ ከፍተኛ ነበር። ያልጠበኩትም ነው። የወዳጅነት ጨዋታ ከመካሄዱ ሁለት ቀን በፊት እንደማልጫወት ሲነገረኝ አዘንኩ። ምክንያቱም ብቃቴን በጨዋታ ማሳየት እችላለሁ ብዬ ጠብቄ ነበር። ልምምድ አንድ ነገር ነው ግጥሚያ ደግሞ ሌላ! ይሁንና ይህ የሆነው ከሳምንታት በፊት ነበር። ኀዘኑን ተወጥቼዋለሁ።»

Bild 1 Dawit Beshah mit der Nationalmannschaft Wann wurde das Bild gemacht?: 2012 Wo wurde das Bild aufgenommen?: Äthiopien Das Bild wurde durch Dawit Beshah gestellt. Zulieferung : Lidet Abebe
ዳዊት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋምስል Fotobiniam

ዳዊት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ብድን ጋ ሲለማመድ የመጀመሪያው አይደለም። ገና በ19 ዓመቱ በጎርጎሮሳዊዉ 2006 ዓ,ም ለብሔራዊ ቡድን ተጫዋችነት ታጭቶ ነበር። ያኔም ሳይሳካ ቀረ።

«የጨዋታ ፈቃድ ጎድሎ ነበር። የፓስፖርት ችግር። ያኔ የኢትዮጵያ ፓስፖርት እንዳወጣ ተፈልጎ ነበር። ለዛ ደግሞ የጀርመኑ ፓስፖርቴን ማስረከብ ነበረብኝ። ያ ደግሞ የሚሆን አልነበረም።»

ይህ ችግር በአሁኑ መፍትሄ ያገኘ ይመስላል። ዳዊት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ ዜጐችን ተጠቃሚ በሚያደርገው ቢጫ ካርድ አማካኝነት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተመረጠ መሰለፍ ይችላል።

«ከተመለስሁ ሁለት ሳምንት ሆነኝ። ወዲያው እጫወትበት በነበረው «ኦይስኪርሽነር TSC» ልምምዴን ቀጥያለሁ። በርግጥ ሰሞኑን በጣለው በረዶ የተነሳ ሜዳ ላይ መጫወት አይቻልም። እንዲያም ቢሆን ብቻ ወደ ልምምድ ተመልሼያለሁ።»

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፈው ሰኞ ያሳየው ግጥሚያ በርግጥም ጠንካራነት የተሞላ ነበር። አምና ሻምፒዎና የሆነው የዛምቢያ ቡድን 55 ደቂቃ ሙሉ የተጫዋች ቁጥር በሜዳው ላይ ኖሮት እንኳ ተጨማሪ ግብ ሊያስቆጥር አልቻለችም። ዳዊትን በስድስት አመት ውስጥ ምን አይነት ለውጥ እንዳየ ሲገልፅ « ከበፊት ቡድን 2 ተጫዋቾች ብቻ ነበሩ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማደጉ ግልፅ ነው። ያለበለዚያ ማጣሪያውን ሊያልፍ አይችልም ነበር። ያኔ ገና ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ለማለፍ ነበር ልምምዱ። አሁን ማጣሪያውንም አልፈው ነበር። ከተማው ውስጥ ሌላ አይነት ተሞክሮ ነው ያለው። ከያኔው የሚወዳደር አይደለም።»

በሰኞው ጨዋታ ከዛምቢያ ይልቅ በኢትዮጵያውያኖቹ ዘንድ የቡድን ስራ ተስተውሏል። ዳዊት አብሯቸው በነበረ ጊዜ የታዘበው ነገር አለ?

«በርግጥ ልክ ነው። እኔ እንደ አዲስ ተጫዋች ነው የተቀላቀልኳቸው። በጥሩ ሁኔታ ተቀብለውኛል። ልጆቹም አስቀድመው እንደሚተዋቀቁ፣ ብዙ ነገር በጋራ እንደተወጡ፣ እንዳሳለፉ እና ማጣሪያውን እንዳለፉ ተመልክቼያለሁ። ይህ ደግሞ ያጣምራል።»

ዳዊት ከቡድኑ ጋ ሲለማመድ ከጨዋታ ባሻገር አማርኛውን እንዳዳበረ ይናገራል። «መሻሻል ይገባዋል። የተወሰነ ያህል ይገባኛል። መናገር ግን ትንሽ ይከብዳል። ይሁንና ኢትዮጵያ በነበርኩበት ጊዜ ምንም እንኳን ሌሎቹ እንግሊዘኛ ቢችሉም አማርኛ ሲለሚያወሩ መነጋገር ግድ ይል ነበርና ከጊዜ ጋ እየተሻሻለ ነው።»

ኢትዮጵያ ከቡርኪና ፋሶ ቡድን ጋ ሊገጥም ከሁለት ሰዓታት ያነሰ እድሜ ቀርተውታል። ዳዊትም ከጓደኞቹ ጋ ተሰብስቦ ጨዋታውን ሊከታተል አስቧል። ለብሔራዊ ቡድኑ ቡርኪና ፋሶን በዛሬው ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ዳዊት አይጠራጠርም። ከዛም አልፎ ከምድቡ ውስጥ ትልቅ ግምት የተሰጠው ናይጄሪያንም፤ « ናይጄሪያ በርግጥ ከምዕራብ አፍሪቃ ቡድኖች ውስጥ ትልቅ ስም አላት። ግን ባሁኑ ካየሁት ጨዋታ አጠቃላይ ቡድኖቹ ተመሳሳይ ብቃት ላይ ናቸው። ናይጄሪያንም ማሸነፍ ይቻላል። ይህ አላማ መሆን አለበት።»

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ