እግር ኳስና ዘረኝነት
ሐሙስ፣ ሰኔ 7 2004
በመካሄድ ላይ ባለው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ አንዳንድ እግር ኳስ አፍቃሪዎች የሚፈጽሟቸው ዘረኛ ድርጊቶች በቀላሉ መታለፍ እንደማይገባቸው Farenet በመባል የሚጠራው ድርጅት አስታወቀ ። ዘረኝነትንና አድልዎን የሚቃወሙ ቡድኖችን ያሰባሰበው የ Farenet ሃላፊ እንደሚሉት በአውሮፓ ተደጋግሞ የሚደርሰውን ይህን አስነዋሪ ተግባር ለማስቀረት ከሚወሰዱ የቅጣት እርምጃዎች በተጨማሪ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ትምህርት መሰጠትም ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ ይረዳል ። ። ያነጋገረቻቸው ሂሩት መለሰ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች
በዘንድሮው የአውሮፓ እግር ኳስ ሻምፕዮና ተጫዋቾች በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት በኳስ ሜዳ በግልፅ ዘረኛ ጉንተላዎች ደርሰውባቸዋል ። ከቼክ ሪፐብሊካዊት እናቱና ከኢትዮጵያዊ አባቱ የተወለደው የቼኩ አጥቂ ቴዎዶር ገብረሥላሴ ይህ ካጋጠማቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው ። የቼክ ቡድን ከሩስያ ጋራ ባካሄደው ጨዋታ የተሰለፈውን ቴዎዶር ወይም ቲዮን የሩስያ ደጋፊዎች በጦጣ መሰል ድምፅ
ተንኩሰውታል ። የሆላንድ ቡድን አባላትም ፖላንድ ውስጥ በሥለጠና ላይ ሳሉ ተመሳሳይ ጉንተላ ገጥሟቸዋል ። በእግር ኳስ ሜዳ የሚፈፀሙ እነዚህን መሰል አሳፋሪ ተግባራት የሚከታተለው Farenet የተባለው ድርጅት ሃላፊ ፕያራ ፓወር ይህ ለዚህን መሰሉ ድርጊት በማስረጃነት መያዙን ተናግረዋል ።
« በአሁኑ ጨዋታ ገብረሥላሴ ላይ ዘረኝነትን የሚያንፀባርቅ እኩይ ትንኮሳ መድረሱን ከታዛቢዎቻን አንዱ ተመልክቷል ገብረሥላሴም በቼክ መገናኛ ብዙሃን የጦጣ መሰል ድምፅ መስማቱን አረጋግጧል ። የሩስያ ደጋፊዎች ደግሞ ይህን አስተባብለዋል ። ይህም ለአውሮፓ አገሮች የእግር ኳስ ማህበር UEFA አንድ ማስረጃ ነው ። »
ፓወር የሚመሩት ፌርኔት በእግር ኳስ ሜዳዎች የሚፈፀሙ ዘረኛ ድርጊቶችን መከታተል ከጀመረ 8 ዓመት ይሆነዋል ። እርሳቸው እንደሚሉት በአውሮፓ እግር ኳስ ሜዳዎች ዘረኛ ድርጊቶች መፈፀማቸው አዲስ አይደለምና አያስገርምም ። ግን የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫን በሚያህል ትልቅ ጨዋታ ላይ መድረሱ አሳፋሪ ቢሆንም ጉዳዩ እንዲተኮርበት ደግሞ ጥሩ አጋጣሚ ሆኗል ።
« አስደንጋጭ በጣም አሳዛኝ ነበር ። በዓለም ፊት ትልቁ የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ እየተካሄደ ዓለም ሁሉ በሚከታተልበት ወቅት ነው የተፈፀመው ። እርግጥ ነው በአውሮፓ በደቡብ አሜሪካና በሌሎችም የእግር ኳስ ጨዋታዎች ና ስፖርታዊ ውድድሮች የሚታየው ይህ ትልቅ ችግር ትኩረት እንዲሰጠው ያደርጋል ። »
የፌርኔት ሁለት ነፃ ታዛቢዎች በእያንዳንዱ ጨዋታ እየተገኙ በቴዎዶር ገብረ ሥላሴ ላይ የደረሰውን መሰል ዘረኛ ድርጊቶች በመመዝገብ ጨዋታውን በሃላፊነት ለሚመራው የአውሮፓ አገሮች የእግር ኳስ ማህበር ዘገባ ያቀርባሉ ። ድርጅቱ ከዚህ ሌላ በየሃገሩ የሚታዩትን የውጭ ዜጎች ጥላቻ ብሔረተኝነትን ና የቀኝ አክራሪነት ምልክቶችንም ያሳውቃል ።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በደጋፊዎቹ ስርዓት የጎደለው ድርጊት በሩስያ ፌደሬሽን ልይ የ120 ሺህ ዮሮ ቅጣት ና የነጥብ ቅነሳ እርምጃ ወስዷል ። ሆኖም ፓወር ቅጣት ብቻውን ውጤት አያመጣም ነው የሚሉት ።
«በኛ እምነት ስህተት ከተፈፀመ ጉዳዩ የሚመለከተው ወገን ቅጣት እዳለ ለማሳወቅ እርምጃ መውሰድ አለበት ይህ ይሰራል በረዝም ጊዜ ደግሞ በማስተማር ህዝቡ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ ስፖርት በአውሮፓ ባህል እንደመሆኑ ህዝቡ አውሮፓ የተለያዩ ባህሎች የሚገኙባትክ ክፍለ ዓለም መሆኗን እንዲቀበል መሥራት ያስፈልጋል ። ረዥም ጊዜ ይወስዳል እንጂ ለውጥ ይመጣል »
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሀመድ